አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 16
16
ዳዊት ለንጉሥነት መቀባቱ
1እግዚአብሔር ሳሙኤልን እንዲህ አለው፤ “ከንጉሥነት ስለ ሻርኩት ለሳኦል የምታለቅስለት እስከ መቼ ድረስ ነው? እኔ እርሱ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ሆኖ ይኖር ዘንድ አልፈልገውም። ይልቅስ የወይራ ዘይት በቀንድ ሞልተህ በመያዝ በቤተልሔም ወደሚኖረው እሴይ ተብሎ ወደሚጠራው ሰው ዘንድ ሂድ፤ እኔ ከእርሱ ልጆች መካከል አንዱን ንጉሥ እንዲሆን መርጬአለሁ።”
2ሳሙኤልም “ይህን ለማድረግ እንዴት ይቻለኛል? ሳኦል ይህን ቢሰማ ይገድለኛል!” ሲል ጠየቀ።
እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ ‘ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ለማቅረብ መጥቻለሁ’ ብለህ ጊደር ይዘህ ሂድ፤ 3እሴይንም ወደ መሥዋዕቱ እንዲመጣ ጥራው፤ እኔም የምታደርገውን ነገር እነግርሃለሁ፤ እኔ የምነግርህንም ሰው ቀብተህ ታነግሣለህ።”
4ሳሙኤልም እግዚአብሔር ያዘዘውን ለማድረግ ወደ ቤተልሔም ሄደ፤ እዚያም እንደ ደረሰ የከተማይቱ መሪዎች በፍርሃት እየተንቀጠቀጡ ወደ ሳሙኤል ቀርበው “አመጣጥህ ለሰላም ነውን?” ሲሉ ጠየቁት።
5እርሱም “አዎ! ለሰላም ነው፤ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀርብ ዘንድ መጥቻለሁ፤ ራሳችሁን በማንጻት ወደ እኔ ኑ” ሲል መለሰላቸው። እሴይና ልጆቹም ራሳቸውን እንዲያነጹ በመንገር ወደ መሥዋዕቱ እንዲመጡ ጠራቸው።
6እዚያም በደረሱ ጊዜ ሳሙኤል ኤሊአብ ተብሎ የሚጠራውን የእሴይን ልጅ አይቶ “በእግዚአብሔር ፊት የቆመው ይህ ሰው በእርግጥ ለንጉሥነት የተመረጠ ነው” ሲል አሰበ። 7እግዚአብሔር ግን “የኤሊአብን ቁመት መርዘምና መልከ ቀናነቱን አትይ፤ እኔ እርሱን አልፈለግሁትም፤ እኔ የምፈርደው ሰዎች እንደሚፈርዱት አይደለም፤ ሰው የውጪ መልክን ያያል፤ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል” አለው።
8ከዚህ በኋላ እሴይ አቢናዳብ ተብሎ የሚጠራውን ልጁን ወደ ሳሙኤል አመጣለት፤ ሳሙኤል ግን “እግዚአብሔር ይህኛውንም አልመረጠውም” አለ። 9ቀጥሎም እሴይ ሻማ ተብሎ የሚጠራውን ልጁን አመጣ፤ ሳሙኤል ግን “እግዚአብሔር ይህኛውንም አልመረጠም” አለ። 10በዚህም ዐይነት እሴይ ሰባቱንም ልጆቹን አቅርቦ በሳሙኤል ፊት አሰለፋቸው፤ ሳሙኤልም እሴይን “እነሆ፥ ከእነዚህ መካከል እግዚአብሔር አንዱንም አልመረጠም” አለው። 11“ታዲያ ሌሎች ልጆች የሉህምን?” ሲል ጠየቀው።
እሴይም “የሁሉ ታናሽ የሆነ አንድ ልጅ አለ፤ እርሱ ግን ወደ በግ እረኝነት ሄዶአል” ሲል መለሰለት።
ሳሙኤልም “እርሱን አስጠርተህ አምጣው፤ እርሱ ሳይመጣ መሥዋዕት አናቀርብም” አለው። 12ስለዚህም እሴይ ልኮ አስጠራው፤ እርሱ ቀይ፥ መልከ መልካምና ዐይኖቹ የሚያበሩ ጤናማ ወጣት ነበር፤ እግዚአብሔርም ሳሙኤልን “የመረጥኩት ሰው ይህ ነውና ተነሥተህ እርሱን ቀባው!” አለው። 13ሳሙኤልም በወይራ ዘይት የተሞላውን ቀንድ ወስዶ ዳዊትን በወንድሞቹ ፊት ቀባው፤ ወዲያውኑ የእግዚአብሔር መንፈስ በዳዊት አደረበት፤ ከዚያም ቀን ጀምሮ ከእርሱ አልተለየም፤ ከዚህም በኋላ ሳሙኤል ወደ ራማ ተመለሰ።
ዳዊት በሳኦል ቤተ መንግሥት
14የእግዚአብሔር መንፈስ ከሳኦል ስለ ተለየ ከእግዚአብሔር የተላከ ክፉ መንፈስ ያሠቃየው ነበር፤ 15አገልጋዮቹም እንዲህ አሉት፤ “እነሆ ከእግዚአብሔር የተላከ ክፉ መንፈስ ያሠቃይሃል፤ 16ስለዚህ ንጉሥ ሆይ! በገና መደርደር የሚያውቅ ሰው ፈልገን እንድናመጣልህ እዘዘን፤ ከዚያም በኋላ ክፉ መንፈስ በሚመጣብህ ጊዜ ያ ሰው በገና ይደረድርልሃል፤ አንተም እንደገና ጤናማ ትሆናለህ።”
17ሳኦልም “በገና በመደርደር የታወቀ ሰው ፈልጋችሁ አምጡልኝ” አላቸው።
18ከአገልጋዮቹም አንዱ “የቤተልሔም ከተማ ነዋሪ የሆነው እሴይ በገና መደርደር የሚችል ልጅ እንዳለው አይቼአለሁ ይህም ብቻ ሳይሆን ጀግና፥ መልከ ቀና፥ ብርቱ ወታደርና ንግግር ዐዋቂ ነው፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነው” አለው።
19ስለዚህም ሳኦል ወደ እሴይ መልእክተኞች ልኮ “የበጎች እረኛ የሆነውን ልጅህን ዳዊትን ላክልኝ” አለው። 20እሴይም ዳዊትን አንድ ትንሽ የፍየል ጠቦት አስይዞ፥ እንጀራና የወይን ጠጅ የተሞላበት አቁማዳ ከተጫነ አንድ አህያ ጋር ወደ ሳኦል ላከው። 21ዳዊትም ወደ ሳኦል መጥቶ ሥራውን ጀመረ፤ ሳኦልም በጣም ስለ ወደደው የእርሱ መሣሪያ ያዥ ጋሻጃግሬ አደረገው። 22ከዚያም በኋላ ሳኦል ወደ እሴይ መልእክት ልኮ “ዳዊትን ወድጄዋለሁ፤ ስለዚህ እዚህ በመቈየት ያገልግለኝ” አለው። 23ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ከእግዚአብሔር የተላከ ክፉ መንፈስ በሳኦል ላይ በሚመጣበት ጊዜ ሁሉ ዳዊት በገናውን አንሥቶ ይደረድራል፤ ክፉውም መንፈስ ለቆት ስለሚሄድ ሳኦል እየተሻለው እንደገና ጤናማ ይሆናል።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 16: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997