1 ተሰሎንቄ ሰዎች 5
5
የጌታን መምጣት ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ
1ወንድሞች ሆይ! ይህ ነገር ስለሚሆንበት ዘመንና ስለ ጊዜው ምንም እንዲጻፍላችሁ አያስፈልግም። 2የጌታ ቀን የሚመጣው፥ ሌባ በሌሊት እንደሚመጣ ዐይነት መሆኑን እናንተ ራሳችሁ ደኅና አድርጋችሁ ታውቃላችሁ። #ማቴ. 24፥43፤ ሉቃ. 12፥39፤ 1ጴጥ. 3፥10። 3ሰዎች “ሁሉ ነገር ሰላምና የተረጋጋ ነው” ሲሉ እርጉዝ ሴትን ምጥ እንደሚይዛት ዐይነት ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል፤ በምንም ዐይነት አያመልጡም። 4እናንተ ግን ወንድሞች ሆይ፥ በጨለማ ውስጥ አይደላችሁም፤ ስለዚህ ቀኑ እንደ ሌባ አይመጣባችሁም። 5እናንተ ሁላችሁም የብርሃን ሰዎች፥ የቀንም ሰዎች ናችሁ፤ እኛ የሌሊት ወይም የጨለማ ሰዎች አይደለንም። 6ስለዚህ እኛ እንንቃ፤ ራስን በመግዛት በመጠን እንኑር እንጂ እንደ ሌሎቹ አናንቀላፋ። 7የሚያንቀላፉ ሰዎች በሌሊት ያንቀላፋሉ፤ የሚሰክሩም በሌሊት ይሰክራሉ። 8እኛ ግን የብርሃን ሰዎች ስለ ሆንን ራስን በመግዛት በመጠን እንኑር፤ እምነትንና ፍቅርን እንደ ጥሩር እንልበስ፤ የመዳንን ተስፋ እንደ ራስ ቊር እንልበስ፤ #ኢሳ. 59፥17፤ ኤፌ. 6፥13-17። 9እግዚአብሔር የጠራን ለቊጣ ሳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት መዳንን እንድናገኝ ነው። 10ክርስቶስ ስለ እኛ የሞተው በሕይወት ብንሆን ወይም ብንሞት ከእርሱ ጋር እንድንኖር ነው። 11ስለዚህ አሁን በምታደርጉት ዐይነት አንዱ ሌላውን በማነጽ ያበረታታው።
የመጨረሻ ምክርና ሰላምታ
12ወንድሞች ሆይ! በእናንተ መካከል በሥራ የሚደክሙትን፥ በጌታ ኢየሱስ አለቆቻችሁንና መካሪዎቻችሁ የሆኑትን እንድታከብሩአቸው እንለምናችኋለን፤ 13በሥራቸው ምክንያትም ለእነርሱ ታላቅ አክብሮትና ፍቅር ይኑራችሁ፤ እናንተም እርስ በርሳችሁ በሰላም ኑሩ።
14ወንድሞች ሆይ! “ሰነፎችን ገሥጹ፤ ፈሪዎችን አደፋፍሩ፤ ደካሞችን እርዱ፤ ሰውን ሁሉ ታገሡ” ብለን እንመክራችኋለን። 15ማንም ሰው በክፉ ፋንታ ክፉ እንዳይመልስ ተጠንቀቁ፤ ይልቅስ ሁልጊዜ እናንተ ለእርስ በርሳችሁም ሆነ እንዲሁም ለሌሎች ሰዎች ሁሉ መልካም ለማድረግ ትጉ።
16ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ፤ 17ባለማቋረጥ ጸልዩ፤ 18በሁሉ ነገር እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ በኢየሱስ ክርስቶስ ባላችሁ ሕይወት እግዚአብሔር ከእናንተ የሚፈልገው ይህን ነው።
19የመንፈስ ቅዱስን ሥራ አታዳፍኑ፤ 20የትንቢትን ስጦታ አትናቁ፤ 21ሁሉን ነገር ፈትኑ፤ መልካም የሆነውን ያዙ። 22ከማናቸውም ዐይነት ክፉ ነገር ራቁ።
23ራሱ የሰላም አምላክ በሁሉ ነገር ይቀድሳችሁ፤ መንፈሳችሁ፥ ነፍሳችሁ፥ አካላችሁ በሙሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚመጣበት ቀን ያለ ነቀፋ ተጠብቆ ይኑር። 24ያ የሚጠራችሁ ታማኝ ስለ ሆነ ይህን ያደርገዋል።
25ወንድሞች ሆይ! ለእኛም ጸልዩልን።
26ወንድሞችን ሁሉ በተቀደሰ መሳሳም ሰላም በሉአቸው። 27ይህ መልእክት ለአማኞች ሁሉ እንዲነበብ በጌታ ስም ዐደራ እላችኋለሁ።
28የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።
Currently Selected:
1 ተሰሎንቄ ሰዎች 5: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997