ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 10
10
ዳዊት ዐሞናውያንንና ሶርያውያንን ድል ማድረጉ
(1ዜ.መ. 19፥1-19)
1ከጥቂት ጊዜ በኋላ የዐሞን ንጉሥ ስለ ሞተ፥ ልጁ ሐኑን በእርሱ እግር ተተክቶ ነገሠ፤ 2ንጉሥ ዳዊትም “አባቱ ናዖስ ለእኔ እንዳደረገልኝ ሁሉ እኔም ለልጁ ለሐኑን ታማኝ ወዳጅ በመሆን ወሮታውን እከፍላለሁ” አለ። ስለዚህም ዳዊት የሐዘን ተካፋይነቱን ለመግለጥ መልእክተኞች ላከ።
መልእክተኞቹም ዐሞን በደረሱ ጊዜ፥ 3የዐሞናውያን መሪዎች ንጉሡን እንዲህ አሉት፤ “ዳዊት እነዚህን ሰዎች የላከው አባትህን በማክበር የሐዘንህ ተካፋይ ለመሆን ይመስልሃልን? ከቶ እንዳይመስልህ! እርሱ እነዚህን መልእክተኞች የላካቸው በከተማይቱ ላይ አደጋ ለመጣል ያመች ዘንድ እንዲሰልሉለት አይደለምን?”
4ሐኑን የዳዊትን መልእክተኞች ይዞ በአንድ በኩል ጺማቸውን ላጨ፤ ልብሳቸውንም በመቊረጥ እስከ ወገባቸው አሳጥሮ አባረራቸው፤ 5እነርሱም ወደ ቤታቸው ለመመለስ አፈሩ፤ ዳዊት ስለ ሆነው ነገር በሰማ ጊዜ መልእክተኞች ልኮ በኢያሪኮ እንዲቈዩና ጺማቸውም እንደገና እስከሚያድግ እንዳይመለሱ ነገራቸው።
6ዐሞናውያን ዳዊትን በገዛ እጃቸው ጠላት እንዳደረጉት ተገነዘቡ፤ ስለዚህም እግረኛ ወታደሮችን ከቤትረሖብና ከጾባ ኻያ ሺህ ሶርያውያንንና ከጦብ ዐሥራ ሁለት ሺህ ሰዎችን፤ እንዲሁም ከንጉሥ ማዕካ አንድ ሺህ ሰዎችን ቀጠሩ፤ 7ዳዊትም ስለዚህ ጉዳይ ሰምቶ ከመላው ሠራዊት ጋር ኢዮአብን በእነርሱ ላይ አዘመተ፤ 8ዐሞናውያን ተሰልፈው ወጥተው የእነርሱ ዋና ከተማቸው በሆነችው በራባ መግቢያ በር አጠገብ ስፍራቸውን ያዙ፤ ሌሎቹ ሶርያውያን፥ ከጦብና ከማዕካ የመጡት ጦረኞች በአንድ ሜዳማ ቦታ ስፍራቸውን ያዙ።
9ኢዮአብ የጠላት ሠራዊት ከፊትና ከኋላ በኩል አደጋ እንደሚጥልበት ተመለከተ፤ ስለዚህ ከእስራኤል ወታደሮች ጀግኖች የሆኑትን መርጦ በሶርያውያን ፊት ለፊት አመች በሆነ ስፍራ መደባቸው፤ 10ከሠራዊቱ ቀሪውን ክፍል በወንድሙ በአቢሳይ ትእዛዝ ሥር አደረገ፤ አቢሳይም እነርሱን በዐሞናውያን ፊት ለፊት አሰለፋቸው፤ 11ኢዮአብም አቢሳይን እንዲህ አለው “ሶርያውያን ድል ሊያደርጉኝ መቃረባቸውን በምታይበት ጊዜ መጥተህ እርዳኝ፤ እኔም ዐሞናውያን አንተን ድል ሊያደርጉህ በሚቃረቡበት ጊዜ መጥቼ እረዳሃለሁ። 12እንግዲህ አይዞህ በርታ! ለሕዝባችንና ለአምላካችን ከተሞች ስንል በርትተን እንዋጋ! እንግዲህ ሁሉ ነገር እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ይሁን!”
13ኢዮአብና ሠራዊቱ አደጋ ለመጣል ወደ ፊት በገሠገሡ ጊዜ ሶርያውያን ሸሹ፤ 14ዐሞናውያንም የሶርያውያንን መሸሽ ባዩ ጊዜ እነርሱም ከአቢሳ ፊት ሸሽተው ወደ ከተማይቱ አፈገፈጉ። ከዚህ በኋላ ኢዮአብ ዐሞናውያንን መውጋት አቁሞ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።
15ሶርያውያን በእስራኤላውያን ድል እንደ ተመቱ በተገነዘቡ ጊዜ ሠራዊታቸውን ሁሉ በአንድነት አሰባሰቡ፤ 16የጾባው ሀዳድዔዜር ከኤፍራጥስ ወንዝ በስተ ምሥራቅ ወደሚገኙት ሶርያውያን መልእክት ላከ፤ እነርሱም የሀዳድዔዜር የሠራዊት አለቃ በሆነው በሾባክ መሪነት ወደ ሔላም መጡ። 17ዳዊትም ይህን በሰማ ጊዜ የእስራኤላውያንን ወታደሮች ሁሉ በአንድነት አሰባስቦ የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻገረ፤ ከዚያም ሶርያውያን ወደ ሰፈሩበት ወደ ሔላም ሄደ፤ ሶርያውያንም በሰልፍ ወጥተው በዳዊት ላይ ጦርነት ከፈቱ፤ 18እስራኤላውያን ሶርያውያንን መልሰው አሳደዱአቸው፤ ዳዊትና ሠራዊቱ ሰባት መቶ የሶርያውያንን ሠረገለኞችንና አርባ ሺህ ፈረሰኞችን ገደሉ፤ እንዲሁም የጠላት ሠራዊት አለቃ የነበረውን ሾባክን መተው አቊስለውት ስለ ነበር እዚያው በጦር ሜዳው ላይ ሞተ። 19በሀዳድዔዜር ሥልጣን ሥር የነበሩት ነገሥታት በእስራኤላውያን ድል መመታታቸውን በተገነዘቡ ጊዜ ከእነርሱ ጋር የሰላም ስምምነት አድርገው የእስራኤላውያን ተገዢዎች ሆኑ፤ ከዚያም በኋላ ሶርያውያን ዳግመኛ ዐሞናውያንን ለመርዳት ፈሩ።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 10: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997