ትንቢተ አሞጽ 2

2
ሞአብ
1እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የሞአብ ሕዝብ ደጋግመው ስለ ሠሩት ኃጢአት ያለ ጥርጥር እቀጣቸዋለሁ፤ እነርሱ የኤዶምን ንጉሥ ዐፅም ዐመድ እስኪሆን አቃጥለዋል፤ #ኢሳ. 15፥1—16፥14፤ 25፥10-12፤ ኤር. 48፥1-47፤ ሕዝ. 25፥8-11፤ ሶፎ. 2፥8-11። 2ስለዚህ በሞአብ ምድር እሳት እለቅበታለሁ፤ የቂሪዮትንም ምሽጎች ያቃጥላል፤ ጦረኞች ድንፋታ፥ ጩኸትና የመለከት ድምፅ እያሰሙ የሞአብን ሕዝብ ይጨርሳሉ። 3የሞአብን ገዢና የአገሪቱንም ሹማምንት አጠፋለሁ።”
ይሁዳ
4እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የይሁዳ ሕዝብ ደጋግመው ስለ ሠሩት ኃጢአት ያለ ጥርጥር እቀጣቸዋለሁ፤ እነርሱ ሕጌን ጥሰዋል፤ ትእዛዜንም አልጠበቁም፤ አባቶቻቸው ይከተሉአቸው የነበሩት የሐሰት አማልክት እነርሱንም አስተዋቸዋል፤ 5ስለዚህ በይሁዳ ምድር ላይ እሳት እለቅበታለሁ፤ የኢየሩሳሌምንም ምሽጎች ያቃጥላል።”
የእግዚአብሔር ፍርድ በእስራኤል ላይ
6እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የእስራኤል ሕዝብ ደጋግመው ስለ ሠሩት ኃጢአት ያለ ጥርጥር እቀጣቸዋለሁ፤ እነርሱ ንጹሓንን በብር፥ ድኾችን በጫማ ይሸጡ ነበር። 7ደካሞችንና ረዳት የሌላቸውን በትቢያ ላይ ጥለው ራስ ራሳቸውን ይረግጣሉ፤ የተዋረዱ ምስኪኖችንም ገፍትረው ከመንገድ ያስወጣሉ፤ አባትና ልጅ ሁለቱም ከአንዲት ሴት ጋር ያመነዝራሉ፤ በዚህም ሥራቸው የተቀደሰውን ስሜን ያረክሳሉ። 8ዕዳቸውን መክፈል ከማይችሉ ድኾች ላይ ልብሳቸውን መያዣ አድርገው ይወስዳሉ፤ መሥዋዕት በሚያቀርቡበትም ቦታ ሁሉ ይተኙበታል፤ ከባለ ዕዳዎች በመቀጫ ስም የወሰዱትን የወይን ጠጅ በአምላካቸው ቤተ መቅደስ ውስጥ ይጠጣሉ።
9“እኔ ግን ለእናንተ ስል ቁመታቸው እንደ ሊባኖስ ዛፍ፥ ብርታታቸው እንደ ዋርካ ዛፍ የነበረውን አሞራውያንን ከነሥር መሠረታቸው ነቃቅዬ አጠፋሁላችሁ፤ #ዘዳ. 3፥8-11። 10ከግብጽ ምድር አውጥቼ አርባ ዓመት ሙሉ በበረሓ መራኋችሁ፤ የአሞራውያንንም ምድር ርስት አድርጌ ሰጠኋችሁ። 11ከወንዶች ልጆቻችሁ መካከል አንዳንዶቹን ነቢያት፥ ከወጣቶቻችሁም መካከል አንዳንዶቹን ናዝራውያን አድርጌ አስነሣሁላችሁ፤ የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! ታዲያ ይህ እውነት አይደለምን? እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ። #2፥11 ናዝራውያን ለተወሰነ ጊዜ የወይን ጠጅ ወይም ማንኛውንም የሚያሰክር መጠጥ ላለመጠጣት፥ ጠጒራቸውን ላለመላጨት፥ ሬሳም ላለመንካት ስእለት በማድረግ ለእግዚአብሔር የተለዩ እስራኤላውያን ናቸው። #ዘኍ. 6፥1-8። 12እናንተ ግን ናዝራውያንን የወይን ጠጅ በማጠጣት አሳታችሁ፤ ነቢያትንም ትንቢት እንዳይናገሩ ከለከላችሁ። 13ስለዚህ ከመጠን በላይ እህል የተጫነ ሠረገላ በሥሩ ያለውን ነገር እንደሚጨፈልቅ እናንተንም እጨፈልቃችኋለሁ። 14ፈጣኑ ሯጭ መፍጠን ያቅተዋል፤ ብርቱ ሰዎችንም ኀይላቸው ይከዳቸዋል፤ ጦረኞችም ራሳቸውን ማዳን አይችሉም። 15ቀስት ወርዋሪዎች ቆመው አይመክቱም፤ ፈጣን ሯጮችም ሮጠው አያመልጡም፤ ፈረሰኞችም ሕይወታቸውን ማዳን አይችሉም። 16በዚያን ቀን እጅግ ብርቱ የሆኑ ጦረኞች እንኳ የጦር መሣሪያቸውን እየጣሉ ይሸሻሉ፤” እግዚአብሔር ይህን ተናግሮአል።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ