ትንቢተ ዳንኤል 11
11
1“ሜዶናዊው ዳርዮስ በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት እኔ እርሱን ለማገዝና ለማበረታታት በአጠገቡ ቆሜ ነበር። 2እኔም አሁን የምነግርህ ነገር እውነት ነው።”
የግብጽና የአሦር መንግሥታት አነሣሥ
ያም ሰው የሚመስለው መልአክ እንዲህ ሲል ንግግሩን ቀጠለ፦ “ሌሎች ሦስት ነገሥታት በፋርስ ላይ ይነግሣሉ፤ ከእነርሱ የሚከተለው አራተኛው ንጉሥ ከሌሎቹ ይልቅ በሀብት የከበረ ይሆናል፥ ከሀብቱም የተነሣ ኀይሉ በበረታ ጊዜ ሌሎቹን መንግሥታት በማስተባበር በግሪክ መንግሥት ላይ ይነሣል።
3“ከዚያን በኋላ ጦረኛ የሆነ አንድ ብርቱ ንጉሥ ይነሣል፤ የመንግሥቱ ግዛት ታላቅ ይሆናል፤ የፈለገውንም ሁሉ ያደርጋል። 4ነገር ግን ኀይሉ በገነነ ጊዜ መንግሥቱ ይፈርስና በአራት የዓለም ማእዘን ይከፈላል፤ በቦታውም የእርሱ ዘሮች ያልሆኑ ነገሥታት ይተካሉ፤ ይሁን እንጂ ከእነርሱ አንዱ እንኳ የእርሱን ያኽል ኀይል አይኖረውም፤ ይህም የሚሆነው ያ መንግሥት ፈርሶ እንደገና ለሌሎችም ስለሚከፋፈል ነው።
5“የደቡብ ንጉሥ ማለትም የግብጽ ንጉሥ እጅግ ብርቱ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ከጦር አዛዦቹ አንዱ ከእርሱ ይልቅ የበረታ ሆኖ እጅግ ታላቅ ለሆነ መንግሥት መሪ ይሆናል። 6ከጥቂት ዓመቶች በኋላ የግብጽ ንጉሥ ከሶርያ ንጉሥ ጋር የወዳጅነት ቃል ኪዳን ይመሠርታል፤ ሴት ልጁንም ለሶርያ ንጉሥ ይድርለታል፤ ነገር ግን እርስዋ ኀይልዋን ለማጠናከር ካለመቻልዋ የተነሣ የንጉሡ ኀይል ስለማይጸና የወዳጅነቱም ውል ጸንቶ አይኖርም፤ ስለዚህም እርስዋ ከደጋፊዎችዋ፥ ከልጆችዋና ከአገልጋዮችዋ ጋር ትገደላለች። 7ወዲያውኑ የእርስዋ ዘመድ የሆነ አንድ ሰው ይነግሣል፤ ከሶርያ ንጉሥ ሠራዊት ጋር ጦርነት ይገጥማል፤ ምሽጋቸውንም ሰብሮ በመግባት ድል ይነሣቸዋል። 8የአማልክታቸውንም ምስሎች ከወርቅና ከብር ዕቃዎች ጋር ማርኮ ወደ ግብጽ ይወስዳል፤ ለጥቂት ዓመቶችም የግብጹ ንጉሥ የሶርያን ንጉሥ በጦርነት ለማጥቃት አይነሣም። 9ከዚያ በኋላ የሶርያ ንጉሥ የግብጽን ንጉሥ ግዛት ለመውረር ይመጣል፤ ነገር ግን በመጣበት እግሩ ወደ አገሩ እንዲመለስ ይገደዳል።
10“የሶርያ ንጉሥ ወንዶች ልጆች ለጦርነት በመዘጋጀት ታላቅ ሠራዊት ያደራጃሉ፤ ከእነርሱ አንዱ ጠራርጎ እንደሚወስድ እንደ ኀይለኛ ጐርፍ ሆኖ በማለፍ በጠላት ምሽግ ላይ አደጋ ይጥላል። 11በዚያን ጊዜ የግብጽ ንጉሥ እጅግ ተቈጥቶ የሶርያን ንጉሥ ለመውጋት ይነሣሉ፤ የሶርያ ንጉሥ ያሰለፈውንም ታላቅ ሠራዊት ያሸንፋል። 12ብዙ ተዋጊዎችን ስለሚማርክ ልቡ ይታበያል፤ ከዚያም በብዙ ሺህ የሚቈጠሩትን ይፈጃል፤ ይሁን እንጂ በድል አድራጊነቱ ጸንቶ አይኖርም።
13“የሶርያም ንጉሥ ወደ አገሩ ተመልሶ ከበፊቱ የበለጠ የጦር ሠራዊት ያደራጃል፤ ከጥቂት ዓመቶችም በኋላ ሠራዊቱን ከተሟላ ትጥቅ ጋር አሰልፎ ይመጣል። 14ከዚያ በኋላ ብዙ ሰዎች በግብጽ ንጉሥ ላይ ያምፃሉ፤ ዳንኤል ሆይ! በዚህ ራእይ የታየው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ከአንተም ወገኖች አንዳንድ የዐመፅ ሰዎች ሁከት ያስነሣሉ፤ ነገር ግን አይሳካላቸውም። 15ስለዚህ የሶርያ ንጉሥ በአንዲት በተመሸገች ከተማ ላይ ከበባ አድርጎ ይይዛታል፤ የግብጽም ወታደሮች እርሱን መቋቋም ይሳናቸዋል፤ ከእነርሱ ምርጥ የሆኑት እንኳ እርሱን ለመቋቋም በቂ ኀይል አይኖራቸውም። 16ከወደ ሰሜን የሚመጣው ወራሪ የፈለገውን ያደርጋል፤ እርሱን ቆሞ የሚመክት አይኖርም፤ እርሱ የተቀደሰችውን አገር እንኳ ሳይቀር ወሮ ይይዛታል።
17“የሶርያ ንጉሥ መላ ሠራዊቱን ሰብስቦ ለመዝመት ያቅዳል፤ የጠላትን መንግሥት ለመደምሰስ ሴት ልጁን በመዳር ከጠላት ንጉሥ ጋር የትብብር ስምምነት ይዋዋላል፤ ይሁን እንጂ ዕቅዱ አይሳካለትም። 18ከዚያ በኋላ በባሕር ጠረፍ ባሉት አገሮች ላይ አደጋ ጥሎ ከእነርሱ ብዙዎቹን ይይዛል፤ ነገር ግን አንድ የጦር መሪ ድል ስለሚነሣው የትዕቢቱ ፍጻሜ ይሆናል፤ በእርግጥም በትዕቢት የተናገረው ስድብ ሁሉ በእርሱ ላይ ይፈጸማል። 19ከዚያ በኋላ ንጉሡ ወደ ገዛ አገሩ ምሽጎች ይመለሳል፤ ነገር ግን ተሰናክሎ ስለሚወድቅ ዳግመኛ አይታይም።
20“ሌላም ንጉሥ በእርሱ ቦታ ይተካል፤ ይህ ንጉሥ የመንግሥቱን ክብር ለመጠበቅ አንድ ግብር አስገባሪ ይሾማል፤ ይሁን እንጂ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ያ ንጉሥ ይገደላል፤ ቢሆንም የሚገደለው በሕዝብ ዐመፅ ወይም በጦርነት አይደለም።”
ጨካኙ የሶርያ ንጉሥ
21ራእዩን ያብራራልኝ የነበረውም መልአክ እንዲህ አለ፦ “ከእርሱ በኋላ አንድ የተናቀ ሰው ይነሣል፤ የንጉሥነት ክብር ግን አልተሰጠውም፤ ነገር ግን በድንገት መጥቶ በተንኰል የመንግሥቱን ሥልጣን ይይዛል። 22የእግዚአብሔር ሊቀ ካህናት ሳይቀር እርሱን የሚቃወም ሠራዊት ሁሉ ከፊቱ ተጠራርጎ ይጠፋል። 23በተንኰል የሰላም ውል በመደራደር ሌሎችን ያታልላል፤ የእርሱ ተከታዮች ጥቂቶች ቢሆኑም እየበረታ ይሄዳል። 24እጅግ ሀብታም የሆነ አንድ ክፍለ ሀገር በድንገት ይይዛል፤ ከቀድሞ አባቶቹ አንዱ እንኳ ያላደረገውን ነገር ሁሉ ያደርጋል፤ በጦርነት የማረከውንም ዕቃና ንብረት ሁሉ ለጭፍሮቹ ያከፋፍላል፤ በምሽጎች ላይ አደጋ ለመጣል ዕቅድ ያወጣል፤ ነገር ግን ለጥቂት ጊዜ ነው።
25“ትልቅ የጦር ኀይል አደራጅቶ በድፍረት በግብጽ ንጉሥ ላይ ይዘምታል፤ የግብጽ ንጉሥም በበኩሉ እጅግ ታላቅ የሆነ የጦር ኀይል አዘጋጅቶ የመጣበትን ጦር ይመክታል፤ ነገር ግን የግብጹ ንጉሥ ሤራ ስለሚደረግበት አይሳካለትም። 26አብረውት የሚመገቡ የቅርብ ወዳጆቹ ያጠፉታል። ሠራዊቱም ይደመሰሳል፤ ብዙዎችም በጦርነት ይሞታሉ። 27ከዚያን በኋላ ሁለቱ ነገሥታት በልባቸው ተንኰል እንደ ያዙ አብረው ለመመገብ በአንድ ገበታ ይቀመጣሉ፤ አንዱ ሌላውን ለማታለል የሐሰት ቃላት ይለዋወጣሉ፤ ሆኖም የተወሰነው ጊዜ ገና ስለ ሆነ እንዳሰቡት አይከናወንላቸውም። 28የሶርያ ንጉሥ የማረከውን ሀብት ሁሉ ይዞ ይመለሳል፤ ልቡ ግን የተቀደሰውን ቃል ኪዳን ለማጥፋት ነው፤ የፈለገውን ሁሉ ካደረገ በኋላ ወደ አገሩ ይሄዳል።
29“ከተወሰነው ጊዜ በኋላ ግብጽን እንደገና ይወራል፤ ይሁን እንጂ እንደ በፊቱ አይሳካለትም። 30ሮማውያን በመርከብ መጥተው ስለሚወጉት በብርቱ ይደነግጣል፤ ወደ ኋላውም አፈግፍጎ በታላቅ ቊጣ ለአይሁድ የተሰጠውን የተቀደሰ ቃል ኪዳን ያረክሳል፤ ተመልሶም ሃይማኖታቸውን ከካዱት ሰዎች ጋር ይወዳጃል። 31ሠራዊቱም ቤተ መቅደሱንና አካባቢውን ያረክሳሉ፤ የዘወትር መሥዋዕትም እንዳይቀርብ ያደርጋሉ፤ አጸያፊ የሆነ ርኩስ ነገር በማቆም ጥፋትን ያመጣሉ። #ዳን. 9፥27፤ 12፥11፤ ማቴ. 24፥15፤ ማር. 13፥14። 32ንጉሡ ቀደም ብለው የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን የካዱትን ሁሉ በማታለል የእነርሱን ድጋፍ ያገኛል፤ እግዚአብሔርን በሚገባ የሚያውቁ ሰዎች ግን ይበረታሉ፤ ንጉሡንም አጥብቀው ይቃወሙታል። 33በሕዝቡ መካከል ያሉ ጠቢባን ሕዝቡን በማስተማር ዕውቀት እንዲያገኝ ያደርጋሉ፤ ነገር ግን ለጥቂት ጊዜ ለእሳት ቃጠሎና ለሰይፍ ስለት የተጋለጡ ይሆናሉ፤ ሀብታቸውንም ተዘርፈው ይታሰራሉ። 34ይህ ከባድ ችግር በወደቀባቸው ጊዜ አንዳንድ ሰዎች መጠነኛ ርዳታ ያደርጉላቸዋል፤ ብዙዎች በታማኝነት ሳይሆን በአስመሳይነት ከእነርሱ ጋር ይተባበራሉ። 35ከጠቢባን አንዳንዶቹ ከባድ መከራ ይደርስባቸዋል፤ ይሁን እንጂ በዚህ ምክንያት ነጥረውና ጠርተው በመውጣት እንከን የሌለባቸው ይሆናሉ፤ ይህም ሁኔታ የሚዘልቀው እግዚአብሔር ያቀደው መጨረሻ ጊዜ እስከሚደርስ ነው።
36“የሶርያ ንጉሥ የፈለገውን ሁሉ ይፈጽማል፤ ራሱንም ከአማልክት ሁሉ በላይ ከፍ ከፍ ያደርጋል፤ ከአማልክት ሁሉ በላይ ባለው አምላክ ላይ ከዚህ በፊት ተሰምቶ የማይታወቅ የስድብ ቃል ይናገራል፤ የታቀደው ሁሉ መደረግ ስላለበት የእግዚአብሔር የቊጣው ቀን እስኪደርስ ድረስ ይሳካለታል። #2ተሰ. 2፥3-4፤ ራዕ. 13፥5-6። 37ንጉሡ የቀድሞ አባቶቹን አማልክት ያቃልላል፤ ሴቶች የሚወዱአቸውንም አማልክት ይንቃል፤ እርሱ ራሱን ከሁሉ በላይ አድርጎ ስለሚቈጥር አማልክትን ሁሉ ችላ ይላል። 38ከነዚህ ይልቅ፥ ምሽጎችን የሚጠብቅ ባዕድ አምላክን ያከብራል፤ በቀድሞ አባቶቹ ላልታወቀ አምላክ ወርቅ፥ ብር፥ ጌጣጌጥ የከበሩ ድንጋዮችንና ሌሎችንም ውድ ስጦታዎች በማቅረብ ያከብራል። 39ምሽጎቹን ይጠብቁለት ዘንድ ባዕድ አምላክን የሚያመልኩ ሰዎችን ይመድባል፤ መሪነቱን የሚያውቁለትን ሁሉ ታላቅ ክብር በመስጠት በሕዝብ ላይ ይሾማቸዋል፤ ለዋሉለትም ውለታ ርስት ያካፍላቸዋል።
40“ጊዜው ሲደርስ የግብጽ ንጉሥ በሶርያ ንጉሥ ላይ አደጋ ይጥልበታል፤ ሆኖም የሶርያ ንጉሥ በሠረገሎች፥ በፈረሶችና በመርከቦች በመጠቀም በብርቱ ጦርነት ይቋቋመዋል፤ እንደ ጐርፍ ውሃ በመጠራረግ ብዙ አገሮችን ይወራል። 41ውብ የሆነችውንም የተስፋይቱን ምድር ይወራል፤ ብዙ አገሮችም በእርሱ እጅ ይወድቃሉ፤ ነገር ግን የኤዶም፤ የሞአብና የዐሞን አገሮች ከወረራው ያመልጣሉ። 42ሥልጣኑን በብዙ አገሮች ላይ በሚያንሰራፋበትም ጊዜ ግብጽም ራስዋ አታመልጥም። 43የግብጽን ወርቅ፤ ብርና ሌላውንም የከበረ ነገር ሁሉ ከተደበቀበት ቦታ ይወስዳል፤ ሊቢያንና ኢትዮጵያንም ድል ያደርጋል፤ 44ከዚያን በኋላ ከምሥራቅና ከሰሜን የሚመጣው ወሬ ያስደነግጠዋል፤ በታላቅ ቊጣ ተነሣሥቶ ብዙ ሰዎችን በማጥፋት እንዳልነበሩ ያደርጋል። 45በባሕሩና ቤተ መቅደሱ በተሠራበት ውብ ኮረብታ መካከል ባለው ስፍራ ታላላቅ ንጉሣዊ ድንኳኖችን ይተክላል፤ ይህም ሁሉ ሆኖ በመጨረሻው ራሱ ይጠፋል፤ የሚረዳውም አያገኝም።”
Currently Selected:
ትንቢተ ዳንኤል 11: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997