የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘጸአት 10

10
ሸ. የአንበጣ መንጋ
1ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “እነሆ እንደገና ወደ ፈርዖን ተመልሰህ ግባ፤ እኔ የእርሱንና የመኳንንቱን ልብ ያደነደንኩት በመካከላቸው እነዚህን ተአምራት ለማድረግ ዐቅጄ ነው፤ 2እንዲሁም እነዚህን ተአምራት ባደረግሁ ጊዜ ግብጻውያንን እንዴት እንደቀጣሁ ለልጆቻችሁና ለልጅ ልጆቻችሁ መንገር ትችሉ ዘንድ ነው፤ በዚህም ዐይነት ሁላችሁም እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ።”
3ስለዚህ ሙሴና አሮን ወደ ንጉሡ ሄደው እንዲህ አሉት፤ “የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ለእኔ መታዘዝን እምቢ የምትለው እስከ መቼ ነው? አሁንም ያገለግለኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ፤ 4በእምቢተኛነትህ ብትጸና ግን እነሆ፥ በነገው ቀን የአንበጣ መንጋ በአገርህ ላይ እንዲመጣ አደርጋለሁ። 5የአንበጣውም መንጋ እጅግ ብዙ ከመሆኑ የተነሣ ምድሪቱን በመላ ይሸፍናል፤ ከበረዶው የተረፈውን ነገር፥ ዛፉን ሁሉ ምንም ሳይቀር ይበላዋል። 6ቤተ መንግሥትህን፥ የመኳንንትህንና የሕዝብህን ቤቶች ሁሉ የአንበጣ መንጋ ይሞላዋል፤ ይህም ሁኔታ ከቀድሞ አባቶችህ ዘመን እስከ አሁን ከታየው መከራ ሁሉ የከፋ ይሆናል።’ ”
ሙሴም ከፈርዖን ፊት ወጥቶ ሄደ።
7መኳንንቱም ንጉሡን እንዲህ አሉት፤ “ይህ ሰው ለእኛ ወጥመድ ሆኖ የሚያስቸግረን እስከ መቼ ነው? አምላካቸውን እግዚአብሔርን ያገለግሉ ዘንድ ከእስራኤላውያን ወገን ወንዶቹ ይሂዱ፤ አገሪቱ በመጥፋት ላይ መሆንዋ አይታወቅህምን?”
8ስለዚህ ሙሴና አሮን ተጠርተው ወደ ንጉሡ ቀረቡ፤ ንጉሡም “ሄዳችሁ እግዚአብሔር አምላካችሁን ማገልገል ትችላላችሁ፤ ነገር ግን መሄድ የሚገባቸው የትኞቹ ናቸው?” አላቸው።
9ሙሴም “ሕፃን ልጆቻችንና ሽማግሌዎቻችን ሳይቀሩ ሁላችንም እንሄዳለን፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችንን፥ በጎቻችንንና ፍየሎቻችንን፥ የቀንድ ከብቶቻችንንም ሁሉ እንወስዳለን፤ በምንሄድበት ስፍራ ለእግዚአብሔር በዓል እናደርጋለን” ሲል መለሰ።
10ንጉሡም እንዲህ አለ፦ “እስቲ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን፤ የዐመፅ ሤራ ማቀዳችሁ ግልጥ ስለ ሆነ ሴቶቻችሁንና ልጆቻችሁን ይዛችሁ እንድትሄዱ አልፈቅድላችሁም! 11እንግዲህ እግዚአብሔርን ማገልገል ከፈለጋችሁ ወንዶቹ ብቻ መሄድ ትችላላችሁ”። ከዚህም በኋላ ሙሴና አሮን ተባረው ወጡ።
12እግዚአብሔርም ሙሴን “አንበጦችን ለማምጣት እጅህን በግብጽ ምድር ላይ ዘርጋ፤ እነርሱም መጥተው ቡቃያውን ሁሉና ከበረዶ የተረፈውን ተክል ሁሉ ይበላሉ” አለው። 13ስለዚህ ሙሴ በግብጽ ምድር ላይ እጁን ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም በዚያን ቀንና ሌሊት የምሥራቅ ነፋስ አስነሣ፤ በነጋም ጊዜ ያ የምሥራቅ ነፋስ አንበጦችን አመጣ። 14እነርሱም በመርመስመስ መጥተው አገሪቱን ወረሩ፤ ይህን ያኽል ብዛት ያለው የአንበጣ መንጋ ከዚያ በፊት ታይቶ አይታወቅም፤ ወደ ፊትም ሊታይ አይችልም። 15አገሪቱ ጠቊራ ጨለማ እስክትመስል ድረስ የአንበጣ መንጋ ሸፈናት፤ አንድም ነገር ሳያስቀር ከበረዶ የተረፈውን በየዛፉ ላይ የሚገኘውን ፍሬና ሌላውንም ተክል ሁሉ ግጦ በላው፤ በግብጽ ምድር ከሚገኘው ከማንኛውም ዛፍና ተክል ለምለም የሆነውን ቅጠል ሁሉ መድምዶ በላ። #ራዕ. 9፥2-3።
16ንጉሡም ሙሴንና አሮንን በፍጥነት አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “አምላካችሁን እግዚአብሔርንና እናንተን በድያለሁ፤ 17እንግዲህስ እነሆ፥ አንድ ጊዜ ብቻ በደሌን ይቅር እንድትሉኝ እለምናችኋለሁ፤ ይህን ከባድ ቅጣት ከእኔ እንዲያስወግድም አምላካችሁን እግዚአብሔርን ለምኑልኝ።” 18ሙሴም ከንጉሡ ፊት ወጥቶ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። 19እግዚአብሔርም የምሥራቁን ነፋስ የሚቋቋምና አንበጦቹንም ጠራርጎ ወደ ቀይ ባሕር የሚነዳ ብርቱ ነፋስ ከምዕራብ በኩል አስነሣ፤ በዚህ ዐይነት በመላው የግብጽ ምድር አንድ አንበጣ እንኳ አልቀረም። 20ነገር ግን እግዚአብሔር የንጉሡን ልብ ስላደነደነ አሁንም እስራኤላውያንን አለቀቀም።
ቀ. ጨለማ
21ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን “እጅህን ወደ ሰማይ ዘርጋው፤ በእጅ እስከሚዳሰስ ድረስ ጥቅጥቅ ያለ ጨለማ የግብጽን ምድር ይሸፍናል” አለው። 22ሙሴም እጁን ወደ ሰማይ ዘረጋ፤ በመላውም የግብጽ ምድር ለሦስት ቀን ጨለማ ሆነ። #መዝ. 105፥28፤ ራዕ. 16፥10። 23ግብጻውያን እርስ በርሳቸው ስለማይተያዩ ማንም ሰው እስከ ሦስት ቀን ከቤቱ መውጣት አልቻለም ነበር፤ እስራኤላውያን በሚኖሩበት ስፍራ ግን ብርሃን ነበር።
24ንጉሡም ሙሴን ጠርቶ “ሄዳችሁ እግዚአብሔርን አገልግሉ፤ ሴቶቻችሁና ልጆቻችሁም ከእናንተ ጋር መሄድ ይችላሉ፤ ነገር ግን በጎቻችሁና ፍየሎቻችሁ የቀንድ ከብቶቻችሁም እዚህ መቅረት ይኖርባቸዋል።”
25ሙሴም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “እንዲህ ከሆነማ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕትና ሌላም መሥዋዕት የምናቀርባቸው እንስሶች አንተ ትሰጠናለህ ማለት ነዋ? 26ከቶ ይህ ሊሆን አይችልም፤ እንስሶቻችንን ሁሉ እንወስዳለን፤ አንዲት ሰኮና እንኳ ወደ ኋላ አትቀርም፤ አምላካችንን እግዚአብሔርን የምናገለግልባቸውን እንስሶች መርጠን ማቅረብ ያለብን እኛው ራሳችን ነን፤ እዚያም ከመድረሳችን በፊት ለእርሱ የምንሠዋቸው እንስሶች ምን ዐይነት እንደ ሆኑ ማወቅ አንችልም።”
27እግዚአብሔርም የንጉሡን ልብ ስላደነደነ ሕዝቡን መልቀቅ አልፈለገም፤ 28ስለዚህ ሙሴን “ዳግመኛ እንዳላይህ ከፊቴ ወዲያ ሂድ! እኔን በምታይበት ጊዜ እንደምትሞት ዕወቅ!” አለው።
29ሙሴም “እውነት ነው፤ አንተ እንዳልከው ዳግመኛ አላይህም” አለው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ