የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘጸአት 9

9
ሠ. የእንስሶች እልቂት
1እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ወደ ንጉሡ ሄደህ የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይልሃል በለው፦ ‘ያገለግለኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ፤ 2ዳግመኛ እምቢ ብትል ግን፥ 3የእግዚአብሔር እጅ በመስክ የሚገኘውን መንጋህን ማለት ፈረሶችህን፥ አህዮችህን፥ ግመሎችህን፥ የቀንድ ከብቶችህን፥ በጎችህንና ፍየሎችህን በታላቅ መቅሠፍት ይመታል። 4እግዚአብሔር ግን በእስራኤላውያንና በግብጻውያን እንስሶች መካከል ልዩነት ያደርጋል፤ ከእስራኤላውያን እንስሶች አንድ እንኳ አይሞትም። 5እግዚአብሔር ይህን ነገር ነገ አደርጋለሁ ብሎ ጊዜውን ወሰነ።’ ”
6እግዚአብሔርም በተናገረው መሠረት በማግስቱ ይህንኑ አደረገ፤ የግብጻውያን እንስሶች ሁሉ አለቁ፤ ነገር ግን ከእስራኤላውያን እንስሶች አንድ እንኳ አልሞተም። 7ንጉሡ የሆነውን ሁሉ ለማጣራት ሰዎችን በላከ ጊዜ ከእስራኤላውያን እንስሶች አንድ እንኳ አለመሞቱን ተረዳ፤ ይህም ሁሉ ሆኖ ልቡን ስላደነደነ ሕዝቡን አለቀቀም።
ረ. ብጉንጅ የመሰለ ብርቱ ቊስል
8ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ “በእፍኛችሁ እየዘገናችሁ ከምድጃ ጥቂት ዐመድ ውሰዱ፤ እርሱንም ሙሴ በንጉሡ ፊት ወደ አየር ይበትነው፤ 9እርሱም እንደ ደቃቅ ትቢያ ሆኖ በግብጽ ምድር ሁሉ ላይ በሚሠራጭበት ጊዜ በሕዝብና በእንስሶቹ ላይ አሠቃቂ የሆነ ብርቱ ቊስል ያመጣል።” 10እነርሱም ጥቂት ዐመድ ከምድጃ ወስደው በንጉሡ ፊት ቆሙ፤ ሙሴም ወደ አየር በበተነው ጊዜ ሕዝቡና እንስሶቹ በብርቱ ቊስል ተመቱ። #ራዕ. 16፥2። 11እንደማንኛውም ግብጻዊ እነርሱም ቈስለው ስለ ነበረ በዚያን ጊዜ አስማተኞቹ በሙሴ ፊት መቅረብ አልቻሉም፤ 12ነገር ግን አሁንም እግዚአብሔር የንጉሡን ልብ በማደንደን እግዚአብሔር አስቀድሞ ለሙሴ እንደ ተናገረ ንጉሡ ሙሴንና አሮንን አላደመጣቸውም።
ሰ. የበረዶ መዝነብ
13ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ነገ ጠዋት በማለዳ ወደ ንጉሡ ሄደህ በፊቱ ቆመህ ‘የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይልሃል’ ብለህ ንገረው፤ ‘ያገለግለኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ፤ 14ነገር ግን እምቢ ብትል፥ በዓለም ላይ እኔን የመሰለ ሌላ አምላክ እንደሌለ ታውቅ ዘንድ አንተን ራስህን፥ መኳንንትህንና ሕዝብህን በመቅሠፍቴ ኀይል አሁኑኑ እቀጣለሁ። 15አንተንና ሕዝብህን በመቅሠፍት ለመምታት የኀይል ክንዴን አንሥቼ ቢሆን ኖሮ እስከ አሁን ከምድር በተወገዳችሁ ነበር። 16ነገር ግን ስሜ በዓለም ሁሉ ይጠራ ዘንድ ኀይሌን ላሳይህ ስለ ፈለግኹ በሕይወት እንድትቈይ አድርጌአለሁ። #ሮም 9፥17። 17አንተ እስከ አሁንም በሕዝቤ ላይ ታብየሃል፤ እንዲሄዱም አልፈቀድክላቸውም። 18እነሆ፥ ነገ በዚህ ጊዜ በግብጽ ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ከባድ የበረዶ ዝናብ አመጣለሁ፤ 19አሁንም በመስክ የተሰማሩት እንስሶችህና በዚያ ያለው ንብረትህ ሁሉ ወደ መጠለያ እንዲጠጋ ትእዛዝ ስጥ፤ ወደ ቤት ያልገቡ ሰዎችም ሆኑ እንስሶች ቢኖሩ ግን በበረዶው ስለሚመቱ ሁሉም ያልቃሉ።’ ” 20ከንጉሡ ባለሟሎች አንዳንዶቹ እግዚአብሔር ስለ ተናገረው ነገር በፍርሃት ተጨነቁ፤ ስለዚህም አገልጋዮቻቸውና እንስሶቻቸው ወደ ቤት ተሰብስበው እንዲጠለሉ አደረጉ። 21የቀሩት ግን እግዚአብሔር የተናገረውን ቃል ችላ በማለት አገልጋዮቻቸውንና እንስሶቻቸውን በሜዳ ተዉ።
22ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን “እጅህን ወደ ሰማይ ዘርጋ፤ በረዶም በግብጽ ምድር ሁሉ ላይ ይዘንባል፤ ሕዝቡን፥ እንስሶቹ በእርሻ ያለውን ተክል ሁሉ ይመታል” አለው። 23ስለዚህ ሙሴ በትሩን አንሥቶ ወደ ሰማይ ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም ነጐድጓድና በረዶ መብረቅም ወደ ምድር አወረደ፤ በዚህ ዐይነት እግዚአብሔር በግብጽ ምድር ላይ በረዶን አዘነበ። 24እግዚአብሔር በዚህና በዚያ ከሚራወጥ የመብረቅ ብልጭልጭታ ጋር ከባድ የበረዶ ዝናብ አወረደ፤ ይህም ዐይነቱ የበረዶ ዝናብ በግብጽ ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ነበር። #ራዕ. 8፥7፤ 16፥21። 25በረዶው በግብጽ ምድር ሁሉ በሜዳ የተገኘውን ማንኛውንም ነገር ሕዝቡንና እንስሶቹን ጭምር ጨፈጨፈ፤ በሜዳ ላይ ያለውን አትክልት ሁሉ መታ፤ ዛፎችንም ሁሉ ሰባበረ። 26እስራኤላውያን በሚኖሩባት በጌሴም ምድር ብቻ በረዶ አልነበረም።
27ንጉሡም ሙሴንና አሮንን አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “አሁንስ በድዬአለሁ፤ እግዚአብሔር እውነተኛ ነው፤ እኔና ሕዝቤ ግን በደለኞች ነን። 28በረዶውና ነጐድጓዱ እጅግ ስለ በዛብን ወደ እግዚአብሔር ጸልዩልን፤ በእርግጥ እለቃችኋለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ እዚህ የምትቈዩበት ጊዜ አይኖርም።”
29ሙሴም ንጉሡን እንዲህ አለው፤ “ከከተማው እንደ ወጣሁ እጄን ዘርግቼ ወደ እግዚአብሔር እጸልያለሁ፤ ነጐድጓዱም ይቆማል፤ በረዶም ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም፤ በዚህ ዐይነት አንተም ምድር የእግዚአብሔር እንደ ሆነች ታውቃለህ። 30ነገር ግን አንተና መኳንንትህ ገና እግዚአብሔር አምላክን የማትፈሩ መሆናችሁን ዐውቃለሁ።”
31ገብስ ገና እሸት፥ ተልባውም ገና በማበብ ላይ ስለ ነበር አንድም ሳይቀር በሙሉ ተበላሸ። 32ስንዴውና አጃው ግን የሚደርሱት ዘግየት ብለው ስለ ነበር ከመበላሸት ድነዋል።
33ሙሴ ከንጉሡ ፊት በመውጣት ከከተማው ውጪ ሄደ፤ እጁንም ዘርግቶ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ ነጐድጓዱና በረዶው ዝናቡም በአንድ ጊዜ ቆመ። 34ንጉሡ ግን ዝናቡ፥ በረዶውና ነጐድጓዱ እንደ ቆመ ባየ ጊዜ እርሱና መኳንንቱ ልባቸውን በማደንደን እንደገና ኃጢአት ሠሩ። 35እግዚአብሔር አስቀድሞ በሙሴ አማካይነት ተናግሮ እንደ ነበረ ንጉሡ ልቡን አደንድኖ እስራኤላውያንን አለቀቀም።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ