ኦሪት ዘጸአት 15
15
የሙሴ መዝሙር
1ከዚህ በኋላ ሙሴና የእስራኤል ሕዝብ ከዚህ የሚከተለውን መዝሙር ለእግዚአብሔር ዘመሩ፦
“ፈረሱንና ፈረሰኛውን ወደ ባሕር በመጣል፥
ክብር የተሞላው ድል ስለ ተጐናጸፈ፥
ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ። #ራዕ. 15፥3።
2እግዚአብሔር በመዝሙር የማመሰግነው መከላከያ ኀይሌ ነው፤
ከጠላት እጅ ያዳነኝ ታዳጊዬም እርሱ ነው፤
እርሱ አምላኬ ስለ ሆነ አመሰግነዋለሁ፤
የአባቴም አምላክ ስለ ሆነ፥ ስለ ገናናነቱ እዘምራለሁ። #መዝ. 118፥14፤ ኢሳ. 12፥2።
3እግዚአብሔር ብርቱ ጦረኛ ነው፤
ስሙም እግዚአብሔር ነው።
4“የንጉሡን ሠራዊት ከነሠረገላው ወደ ባሕር ጣለ፤
ምርጥ የሆኑት የጦር አዛዦች በቀይ ባሕር ውስጥ ሰጥመው ቀሩ።
5ጥልቁ ባሕር አሰጠማቸው፤
እንደ ድንጋይም አቈልቊለው ወደ ባሕሩ ጥልቀት ወረዱ።
6“አምላክ ሆይ፥ የቀኝ እጅህ ኀይል፥ ባለ ግርማ ነው፤
ጠላትን ሰባብሮ ይጥላል፤
7ግርማ በተሞላው ድል አድራጊነትህ ጠላትህን ገለበጥህ፤
ቊጣህ እንደ እሳት ስለ ነደደ እንደ ገለባ በላቸው።
8በቊጣህ እስትንፋስ፥
ውሃው ወደ ላይ ተቈለለ፤ እንደ ግድግዳም ቀጥ ብሎ ቆመ፤
በጥልቅ ስፍራ ያለውም ውሃ፥ ረግቶ ጠጠረ።
9‘ጠላትማ አሳድጄ እይዛቸዋለሁ፤
ሀብታቸውንም እካፈላለሁ፤
የፈለግኹትንም እወስዳለሁ፤
ሰይፌንም መዝዤ አጠፋቸዋለሁ’ ብሎ ነበር፤
10ነገር ግን አምላክ ሆይ፥
ከአንተ በተገኘው በአንድ ትንፋሽ ግብጻውያን ሁሉ ሰጠሙ፤
በጥልቅ ባሕር ውስጥ እንደ ተጣለ ብረት ሆነው ቀሩ።
11“አምላክ ሆይ፥ ከአማልክት መካከል አንተን የሚመስል ማን ነው?
በቅድስናስ እንደ አንተ ያለ ባለግርማ ማን ነው?
አንተ ያደረግሃቸውን ተአምራትና አስገራሚ ሥራዎች
ሊያደርግ የሚችልስ ማን አለ?
12ቀኝ እጅህን በዘረጋህ ጊዜ ጠላቶቻችንን ምድር ዋጠቻቸው፤
13በማይለወጥ ፍቅርህ ያዳንካቸውን ሕዝብ መራህ፤
በብርታትህም ወደ ተቀደሰችው ምድር እንዲገቡ አደረግህ፤
14አሕዛብ ሁሉ ይህን ሰምተው በፍርሃት ተንቀጠቀጡ፤
ፍልስጥኤማውያንም ተሸበሩ፤
15የኤዶም መሪዎች ተስፋ ቈረጡ፤
የሞአብም ኀያላን ተንቀጠቀጡ፤
የከነዓንም ሕዝብ ወኔ ከዳቸው።
16አምላክ ሆይ፥ ሕዝብህ እስኪያልፍ ድረስ፥
የተቤዠኸው ሕዝብ እስኪያልፍ ድረስ፥
ፍርሀትና ድንጋጤ ወደቀባቸው፤
በሥልጣንህ እንደ ድንጋይ ጸጥ አሉ።
17አምላክ ሆይ፥ ለማደሪያህ ባደረግኸው ስፍራ
እጆችህ ባዘጋጁት መቅደስ፥
ወገኖችህን አንተ ታስገባቸዋለህ፤
በርስትህ ተራራም ትተክላቸዋለህ።
18እግዚአብሔር
ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይነግሣል።
የማርያም መዝሙር
19“እስራኤላውያን በደረቅ ምድር ባሕሩን ተሻገሩ፤ የፈርዖን ፈረሶች፥ ሠረገሎችና ፈረሰኞቹ ሁሉ ወደ ባሕር በገቡ ጊዜ እግዚአብሔር ውሃውን መለሰባቸው።”
20የአሮን እኅት ነቢይቱ ማርያም ከበሮዋን አነሣች፤ ሌሎችም ሴቶች ከበሮዎቻቸውን እየመቱና እየጨፈሩ ይከተሉአት ጀመር፤ 21ማርያምም፥
“ፈረሱንና ፈረሰኛውን ወደ ባሕር በመጣል
ክብር የተመላ ድልን ስለ ተጐናጸፈ፥
ለእግዚአብሔር ዘምሩ” እያለች ዘመረችላቸው።
መራራ ውሃ
22ከዚህ በኋላ ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ ከቀይ ባሕር አሳልፎ ወደ ሱር በረሓ መራቸው፤ ሦስት ቀን ሙሉ በበረሓ ተጓዙ፤ ነገር ግን ምንም ውሃ አላገኙም። 23ከዚህ በኋላ ማራ ወደ ተባለ ስፍራ በደረሱ ጊዜ ውሃው መራራ ስለ ነበረ ሊጠጡት አልቻሉም፤ ማራ ተብሎ የተጠራበትም ምክንያት ይኸው ነበር። 24ሕዝቡም በሙሴ ላይ በማጒረምረም “እንግዲህ ምን ልንጠጣ ነው?” ሲሉ ጠየቁት። 25ሙሴም በብርቱ ጩኸት ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም አንድ እንጨት አሳየው፤ እርሱንም ወስዶ በውሃው ላይ በጣለው ጊዜ፥ ውሃው ወደጣፋጭነት ተለወጠ።
በዚያ ስፍራ እግዚአብሔር የሚተዳደሩበት ደንብና ሥርዓት ሰጣቸው፤ በዚያም ፈተናቸው። 26እንዲህም አላቸው፤ “በጥሞና ትእዛዞቼን ብታዳምጡና በፊቴ መልካም የሆነውን ነገር በታዛዥነት ብታደርጉ፥ ኅጎቼንም ሁሉ ብትጠበቁ፥ በግብጻውያን ላይ ካመጣሁባቸው በሽታዎች በአንዱ እንኳ አልቀጣችሁም፤ ፈዋሻችሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።”
27ከዚህ በኋላ ወደ ኤሊም መጡ፤ በዚያም ስፍራ ዐሥራ ሁለት የውሃ ምንጮችና ሰባ የተምር ዛፎች ነበሩ፤ ሕዝቡም በዚያ ከውሃው አጠገብ ሰፈሩ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘጸአት 15: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997