ኦሪት ዘጸአት 28

28
ልብሰ ተክህኖ
(ዘፀ. 39፥1-7)
1“ወንድምህን አሮንንና ልጆቹን ናዳብን፥ አቢሁን፥ አልዓዛርንና ኢታማርን ወደ አንተ አቅርብ፤ ካህናት ሆነው ያገለግሉኝም ዘንድ ከእስራኤል ሕዝብ መካከል ለያቸው። 2ለክብርና ለውበት ይሆነው ዘንድ ለወንድምህ ለአሮን የክህነት ልብስ ሥራለት። 3እኔ ልዩ ችሎታ እንዲኖራቸው ያደረግኋቸውን የእጅ ጥበብ ዐዋቂዎችን ጠርተህ ለአሮን ልብስ እንዲሠሩለት ንገራቸው፤ በዚህ ዐይነት አሮን ካህን በመሆን ያገለግለኝ ዘንድ ለእኔ የተለየ ይሆናል። 4በዐይነት የሚሠሩአቸውም ልብሶች እነዚህ ናቸው፤ የደረት ኪስ፥ ኤፉድ፥ ቀሚስ፥ በጥልፍ ያጌጠ ሸሚዝ፥ ጥምጥምና መታጠቂያ፤ ወንድምህ አሮንና ልጆቹ ካህናት ሆነው ያገለግሉኝ ዘንድ እነዚህን የተቀደሱ ልብሶች ይሥሩላቸው። 5ጥበበኞቹም ልብሶቹን ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊ፥ ከቀይ ከፈይ ከወርቅ ምዝምዝና ከጥሩ በፍታ በጥልፍ አስጊጠው ይሥሩ።
6“ኤፉድንም ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊ ከቀይ ከፈይ ከወርቅ ምዝምዝና ከጥሩ በፍታ በጥልፍ አስጊጠው ይሥሩ። 7ሁለቱ ወገን አንድ እንዲሆን በሁለቱ ትከሻ ላይ የሚጋጠም የጥብጣብ ዐይነት ማንገቻ ይኑር። 8ኤፉዱ ከተሠራባቸው ተመሳሳይ ነገሮች በብልኀት የተጠለፈ መታጠቂያ አንድ ላይ እንደ ተሠራ ሆኖ ከኤፉዱ ጋር ይጣበቅ። 9ሁለትም የመረግድ ድንጋይ ወስደህ የዐሥራ ሁለቱን የያዕቆብ ልጆች ስም ቅረጽባቸው፤ 10ይኸውም የልደታቸውን ቅደም ተከተል ሳታፋልስ ስድስቱን በአንድ ድንጋይ ላይ፥ ስድስቱንም በሌላ ድንጋይ ላይ ጻፍ። 11በሁለቱ ድንጋዮች ላይ የዐሥራ ሁለቱን የያዕቆብ ልጆች ስሞች ለመቅረጽም ችሎታ ያለው ብልኅ ሰው አግኝ፤ ድንጋዮቹንም ከወርቅ በተሠራ ፈርጥ ላይ አኑራቸው። 12ለዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች መታሰቢያ ይሆኑ ዘንድ ሁለቱን ዕንቆች በትከሻ ላይ በሚያልፉት የኤፉድ ማንገቻዎች ላይ ታደርጋቸዋለህ። በዚህ ዐይነት እኔ እግዚአብሔር ዘወትር ሕዝቤን አስታውስ ዘንድ አሮን የእነርሱን ስሞች በትከሻው ይሸከማል። 13ሁለት የወርቅ ፈርጦች ሥራ፤ 14እንደ ገመድ ተጐንጒነው ከንጹሕ ወርቅ የተሠሩ ሁለት ድሪዎችንም አበጅተህ ከሁለቱ ፈርጦች ጋር እንዲያያዙ አድርግ።
የደረት ኪስ
(ዘፀ. 39፥8-21)
15“የእግዚአብሔር ፈቃድ የሚጠየቅበትን የደረት ኪስ ለሊቀ ካህናቱ ሥራ፤ አሠራሩ እንደ ኤፉድ ሆኖ በተመሳሳይ ጥልፍ ያጌጠ ይሁን። 16ርዝመቱ ኻያ ሁለት ሳንቲ ሜትር የጐኑም ስፋት ኻያ ሁለት ሳንቲ ሜትር ሆኖ ታጥፎ የተደረበ ትክክል አራት ማእዘን ይሁን። 17አራት ረድፍ የሆነ የዕንቊ ፈርጥ አድርግበት፤ በመጀመሪያው ረድፍ ሰርድዮን፥ ቶጳዝዮንና፥ የሚያብረቀርቅ ዕንቊ፥ 18 18በሁለተኛው ረድፍ በሉር፥ ሰንፔርና መረግድ፤ 19በሦስተኛው ረድፍ ያክንት፥ ኬልቄዶንና አሜቲስጦስ፥ 20በአራተኛው ረድፍ ቢረሌ፥ መረግድና ኢያስጲድ በወርቅ ፈርጥ ላይ ይቀመጣሉ። 21ለእስራኤል ነገዶች መታሰቢያ ይሆኑ ዘንድ ከእነዚህ ዐሥራ ሁለት የዕንቊ ድንጋዮች በእያንዳንዱ ላይ ከያዕቆብ ልጆች የአንዱ ስም ይቀረጽበታል። 22ለደረት ኪሱም እንደ ገመድ የተጐነጐነ ድሪ ከንጹሕ ወርቅ ሥራ። 23ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ሠርተህ በደረት ኪሱ ከላይኛው ማእዘን በኩል እንዲጋጠሙ አድርግ። 24ሁለቱን የወርቅ ድሪዎች ከሁለቱ ቀለበቶች ጋር አያይዛቸው። 25በሌላ በኩል ያሉትንም የሁለቱን ድሪዎች ጫፎች ከሁለቱ ፈርጦች ጋር አገናኛቸው፤ በዚህም ዐይነት ከፊት ለፊት በኩል በትከሻ ላይ ከሚወርዱት ከኤፉዱ ማንገቻዎች ጋር ታያይዛቸዋለህ፤ 26እንደገናም ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ሠርተህ በውስጥ በኩል ከኤፉዱ ቀጥሎ ባለው የደረት ኪስ ከታችኛዎቹ ማእዘኖች ጋር እንዲገጣጠሙ አድርግ። 27ከነዚህም ሌላ ሁለት ተጨማሪ የወርቅ ቀለበቶች ሠርተህ ከፊት ለፊት በኩል በትከሻ ላይ ከሚወርዱት ከኤፉዱ ማንገቻዎች ጋር ከታች በኩል ታያይዘዋለህ፤ መያያዝ ያለበትም በስፌቱ መጋጠሚያ አጠገብና በብልኀት ከተጠለፈው መታጠቂያ በላይ በኩል ነው። 28በደረት ኪሱ ላይ ያሉትን ቀለበቶች በኤፉዱ ላይ ካሉት ቀለበቶች ጋር በሰማያዊ ድሪ እሰራቸው፤ በዚህ ዐይነት የደረት ኪሱ ከመታጠቂያው በላይ ስለሚሆን ልል አይሆንም።
29“አሮን ወደ ተቀደሰው ስፍራ ሲገባ የእስራኤል ነገዶች ስሞች የተቀረጹበትን ይህን የደረት ኪስ ይለብሳል፤ በዚህ ዐይነት እኔ እግዚአብሔር ሁልጊዜ ሕዝቤን አስታውሳለሁ። 30ዑሪምና ቱሚም የተባሉትን ነገሮች በደረት ኪሱ ውስጥ ታስገባቸዋለህ፤ አሮንም ወደ ቅዱሱ ድንኳን ሲገባ በደረት ኪሱ ተሸክሞአቸው ይግባ፤ የእኔን ፈቃድ ለእስራኤል ሕዝብ ማስታወቅ ይችል ዘንድ በፊቴ ለማገልገል በሚገባበት ጊዜ ሁሉ በደረት ኪሱ ያድርጋቸው። #28፥30 ዑሪምና ቱሚም የአይሁድ ካህን በሚለብሰው ኤፉድ ኪስ የሚከተቱት የእግዚአብሔርን ፈቃድ መጠየቂያ ሁለት ዕቃዎች ናቸው፤ ይሁንና እንዴት ወይም ከምን እንደ ተሠራ አይታወቅም። #ዘኍ. 27፥21፤ ዘዳ. 33፥8፤ ዕዝ. 2፥63፤ ነህ. 7፥65።
ሌሎች የክህነት አልባሳት
(ዘፀ. 39፥22-31)
31“በኤፉዱ መደረቢያ ቀሚስ ሙሉ በሙሉ ከሰማያዊ በፍታ የተሠራ ይሁን፤ 32የራስ ማጥለቂያ አንገትጌም ይኑረው፤ ይህም አንገትጌ እንዳይተረተር ወደ ውስጥ ታጥፎ በእጅ ሥራ የተቀመቀመ ይሁን። 33በታችኛው ዘርፍ ዙሪያ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊና ከቀይ ከፈይ የተሠሩ የሮማን ፍሬ ቅርጽ አድርግበት፤ በፍሬዎቹ መካከል ጣልቃ የሚገቡ ከወርቅ የተሠሩ ትናንሽ ቃጭሎች አድርግበት። 34ሮማን የመሰለውና የወርቅ መርገፍ በቀሚሱ ዘርፍ ዙሪያውን ተከታትለው ይደረጋሉ። 35አሮን በክህነት በሚያገለግልበት ጊዜ ይህን ቀሚስ ይልበስ፤ በተቀደሰው ስፍራ በፊቴ በተገኘ ጊዜ ወይም ከዚያ በሚወጣበት ጊዜ የመርገፉ ድምፅ ስለሚሰማ ከመሞት ይድናል።
36“ከንጹሕ ወርቅ አንድ ጌጥ ሥራና በላዩ ላይ ‘ለእግዚአብሔር የተለየ’ የሚል ቃል ቅረጽበት። 37በመጠምጠሚያውም ፊት በሰማያዊ ድሪ እንዲንጠለጠል አድርግ፤ 38አሮንም በግንባሩ ላይ ያድርገው፤ በዚህ ዐይነት ባቀራረብ እንኳ ስሕተት ቢፈጽሙ እስራኤላውያን የሚያቀርቡልኝን መባ ሁሉ እኔ እግዚአብሔር እቀበላቸዋለሁ።
39“የአሮንን ሸሚዝና መጠምጠሚያ ከጥሩ በፍታ ሥራው፤ መታጠቂያውም ከጥሩ በፍታ ተሠርቶ በጥልፍ ጥበብ ያጌጠ ይሁን።
40“ለአሮንም ልጆች ክብርና ውበት ይሆንላቸው ዘንድ ሸሚዞችን፥ መታጠቂያዎችንና ቆቦችን ሥራላቸው። 41እንግዲህ እነዚህን ልብሶች ለወንድምህ ለአሮንና ለልጆቹ አልብሳቸው፤ በክህነት ያገለግሉኝም ዘንድ የወይራ ዘይት በመቀባት የክህነትን ማዕርግ ትሰጣቸዋለህ፤ ትቀድሳቸዋለህም፤ 42የውስጥ ሰውነታቸው እንዳይጋለጥ ከጥሩ በፍታ፥ ከወገባቸው እስከ ጭናቸው የሚደርስ ቊምጣ ሱሪ ትሠራላቸዋለህ፤ 43አሮንና ልጆቹ ዘወትር ወደ ድንኳን ሲገቡ ወይም በተቀደሰው ስፍራ በክህነት ለማገልገል ወደ መሠዊያው ሲቀርቡ ይለብሱታል፥ በዚህ ዐይነት የውስጥ ሰውነታቸው ስለማይጋለጥ ከሞት ይድናሉ፤ ይህ እንግዲህ ለአሮንና ለትውልዱ ሁሉ ጸንቶ የሚኖር ሥርዓት ነው።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ