ኦሪት ዘጸአት 29
29
ስለ ክህነት ሥልጣን ለአሮንና ለልጆቹ የተሰጠ መመሪያ
(ዘሌ. 8፥1-36)
1“አሮንና ልጆቹ ካህናት ሆነው በፊቴ ያገለግሉኝ ዘንድ ለመለየት የምታደርገው ይህ ነው፤ ምንም ነውር የሌለባቸውን አንድ ወይፈንና ሁለት የበግ አውራዎችን ውሰድ፤ 2እርሾ ያልነካው ምርጥ የሆነ የስንዴ ዱቄት ወስደህ የወይራ ዘይት በመጨመር ቂጣ አዘጋጅ፤ እንዲሁም ዘይት ያልገባበት ሌላ ቂጣ አዘጋጅ፤ ሌላ ስስ ቂጣም ጋግረህ ዘይት ቀባው፤ 3ሁሉንም በመሶብ አኑረህ ኰርማና ሁለቱን የበግ አውራዎች በምትሠዋበት ጊዜ ለእኔ መባ አድርገህ አቅርብልኝ።
4“አሮንንና ልጆቹን እኔ ወደምመለክበት ድንኳን ደጃፍ አምጥተህ በውሃ እንዲታጠቡ ንገራቸው። 5ከዚህ በኋላ አሮንን የክህነት ልብስ አልብሰው፤ ሸሚዙን፥ ኤፉዱን፥ የኤፉዱን መደረቢያ ቀሚስ፥ የደረት ኪሱን አልብሰው፤ መታጠቂያውን አስታጥቀው፤ #29፥5 ኤፉድ፦ ሊቀ ካህናቱ የሚለብሰው ቀሚስና ወይም የደረት ልብስ ነው፤ በደረት ኪሱም ኡሪምና ቱሚም የተባሉት የእግዚአብሔር ፈቃድ መጠየቂያ የሆኑ ዕቃዎች ይቀመጣሉ። 6በራሱም ላይ መጠምጠሚያውን አኑር፤ በመጠምጠሚያውም ላይ የተቀደሰውን አክሊል አድርግለት። 7የቅባት ዘይቱንም ወስደህ በራሱ ላይ በማፍሰስ ቀባው፤
8“ልጆቹንም አቅርበህ ሸሚዝ አልብሳቸው፤ 9ለወገባቸውም መታጠቂያ አድርግላቸው፤ በራሳቸውም ላይ ቆብ ድፋላቸው፤ ክህነታቸው ለዘለዓለም ቋሚ ሥርዓት ይሆናል፤ በዚህም ዐይነት አሮንንና ልጆቹን ትሾማለህ።
10“ኰርማውን ወደ ድንኳኑ ፊት ለፊት አምጥተህ፥ አሮንና ልጆቹ እጃቸውን በራሱ ላይ እንዲጭኑበት አድርግ። 11ኰርማውን በድንኳኑ ደጃፍ በእኔ በእግዚአብሔር ፊት ዕረደው። 12ከኰርማው ደም ጣትህን ነክረህ የመሠዊያውን ጒጦች ቀባ፤ የተረፈውንም ደም በመሠዊያው ሥር አፍስሰው። 13ከዚህ በኋላ የሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ሞራ እንደ መረብ ሆኖ ጉበቱን የሚሸፍነውን ሞራ ሁለቱን ኲላሊቶቹንና እነርሱን የሚሸፍነውን ሞራ ወስደህ በመሠዊያው ላይ አቃጥለው። 14የኰርማውን ሥጋ፥ ቆዳውን፥ አንጀቱን ሁሉ ወስደህ ከሰፈር ውጪ አቃጥለው፤ ይህ የኃጢአት መሥዋዕት ነው።
15“ከሁለቱ የበግ አውራዎች አንዱን ወስደህ አሮንና ልጆቹ እጃቸውን በራሱ ላይ እንዲጭኑ አድርግ። 16እርሱንም ዐርደህ ደሙን በመሠዊያው ጐን በአራቱም ማእዘን እርጨው፤ 17ሥጋውን በየብልቱ ቈራርጠው፤ የውስጥ ዕቃውንና የኋላ እግሮቹን በውሃ አጥበህ ከራሱና ከሌሎቹ የሥጋ ብልቶች ጋር አኑር፤ 18ከዚያም በኋላ የአውራውን በግ ሥጋ በሙሉ ለእኔ ለእግዚአብሔር የምግብ መሥዋዕት አድርገህ አቃጥለው፤ ይህም መባ ሽታው እኔን ደስ የሚያሰኝ ይሆናል። #ኤፌ. 5፥2፤ ፊል. 4፥18።
19“ለክህነት ሥርዓት የተመደበውን ሌላውንም አውራ በግ ወስደህ አሮንና ልጆቹ እጃቸውን በራሱ ላይ እንዲጭኑበት ንገራቸው፤ 20እርሱንም ዕረድና ከደሙ ጥቂት ወስደህ የአሮንንና የልጆቹን ቀኝ ጆሮዎች ጫፍ፥ የቀኝ እጃቸውንና የቀኝ እግራቸውን አውራ ጣት ትቀባለህ፤ የተረፈውንም ደም በመሠዊያው ጐን በአራቱም ማእዘን ርጨው። 21በመሠዊያው ላይ ካለው ደም ጥቂት፥ ከቅባቱም ዘይት ጥቂት ወስደህ በአሮንና በልብሱ ላይ በአሮን ልጆችና በልብሶቻቸው ላይ ርጨው፤ በዚህ ዐይነት እርሱና ልጆቹ ከነልብሶቻቸው ለእኔ የተለዩ ይሆናሉ።
22“የሚካኑበት ስለ ሆነ የአውራውን በግ ሞራ ላቱን፥ የውስጥ ዕቃውን የሚሸፍነውን ሞራ፥ እንደ መረብ ሆኖ ጉበቱን ከሚሸፍነው ሞራ የተሻለውን ክፍል፥ ሁለቱን ኲላሊቶቹን፥ እነርሱን የሚሸፍነውን ሞራና በቀኝ በኩል ያለውን የኋላ እግር ቈርጠህ ለያቸው። 23በመሶብ ሆኖ ለእኔ ለእግዚአብሔር ከቀረበው ቂጣ ከየአንዳንዱ ዐይነት አንድ ሙልሙል ውሰድ፤ ይኸውም ዘይት ተጨምሮበት ከተጋገረው አንድ፥ ዘይት ካልገባበትም አንድ፥ እንዲሁም ሌላ አንድ ስስ ቂጣ ጨምረህ ትወስዳለህ ማለት ነው። 24ይህን ሁሉ ምግብ በአሮንና በልጆቹ እጅ ላይ አኑር፤ እርሱንም ወዝውዘው ለእኔ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ መሥዋዕት አድርገው ያቅርቡት። 25ከእነርሱም በመቀበል ለእኔ የምግብ መባ አድርገህ ታቀርበው ዘንድ በሚቃጠለው መሥዋዕት ጫፍ ላይ አኑረህ በመሠዊያው ላይ አቃጥለው፤ ይህም መባ መዓዛው እኔን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ይሆናል።
26“ለአሮን ክህነት ሥርዓት ከታረደው የበግ አውራ ፍርምባውን ወስደህ ለእኔ ለእግዚአብሔር በመወዝወዝ የሚቀርብ መባ አድርገህ አንሣ፤ ይህም ለእናንተው የሚመደብ ድርሻ ይሆናል።
27“አሮንና ልጆቹ ከሚካኑበት አውራ በግ ተወስዶ ለመሥዋዕት የተወዘወዘውን ፍርምባና የተነሣውን ወርች ትቀድሳለህ። እርሱም ተመልሶ ለካህናቱ የሚመደብ ድርሻ ይሆናል። 28ሕዝቤ የአንድነት መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ የእንስሳው ፍርምባና በቀኝ በኩል ያለውን የኋላ እግር ለአሮንና ለልጆቹ ድርሻ ሆኖ እንዲመደብ ወስኛለሁ፤ ውሳኔውም ቋሚ ሥርዓት ይሆናል፤ ይህ እንግዲህ ሕዝቡ ለእኔ ለእግዚአብሔር የሚያቀርበው መባ ነው።
29“አሮን በሚሞትበት ጊዜ የክህነት ልብሶቹ ለልጆቹ ይተላለፉ፤ እነርሱም ተቀብተው የክህነት ሥልጣን በሚቀበሉበት ጊዜ ይልበሱት። 30የክህነቱ ሥልጣን ወራሽ በመሆን በተቀደሰው ስፍራ እኔን ለማገልገል ካህን ሆኖ ወደ ቅዱሱ ድንኳኔ የሚገባው የአሮን ልጅ እነዚህን ልብሶች ለሰባት ቀን ይልበስ።
31“አሮንና ልጆቹ የክህነት ሥልጣን በሚቀበሉበት ጊዜ የታረደውን የአውራ በግ ሥጋ ወስደህ በተቀደሰ ስፍራ ቀቅለው። 32ይህንንም ሥጋ በመሶብ ውስጥ ተርፎ ከቀረው ቂጣ ጋር በቅዱሱ ድንኳኔ ደጃፍ ሆነው ይብሉት። 33የክህነት ሥልጣን ሲቀበሉ ስለ ኃጢአት ይቅርታ የተሠዋውንም ይብሉ። ይህ ምግብ የተቀደሰ ስለ ሆነ ካህናት ብቻ ይብሉት። 34ከሥጋውም ሆነ ከኅብስቱ ሳይበላ ተርፎ ያደረ ቢኖር በእሳት ይቃጠል፤ የተቀደሰ ስለ ሆነም መበላት የለበትም።
35“አሮንና ልጆቹ የክህነት ሥልጣን የሚቀበሉበትን ሥርዓት ልክ እኔ ባዘዝኩህ መሠረት ለሰባት ቀን ፈጽም። 36ስለ ኃጢአትም ይቅርታ በእያንዳንዱ ቀን አንድ ኰርማ መሥዋዕት አድርገህ አቅርብ፤ ይህም መሠዊያውን ያነጻል፤ የተቀደሰም ይሆን ዘንድ የወይራ ዘይት ቀባው። 37ይህንንም ለሰባት ቀን በየዕለቱ አድርግ፤ በዚህም ዐይነት መሠዊያው ፍጹም የተቀደሰ ይሆናል፤ የተቀደሰም ስለ ሆነ፥ ሰውም ሆነ ሌላ ነገር እርሱን ቢነካ በቅድስናው ኀይል ቅሥፈት ይደርስበታል።
የሠርክ መሥዋዕት
(ዘኍ. 28፥1-8)
38“በሚመጡት ዘመናት ሁሉ በየዕለቱ አንድ ዓመት የሆናቸው ሁለት ጠቦቶች መሥዋዕት አድርገህ በመሠዊያው ላይ ታቀርባለህ፤ 39ከጠቦቶቹ አንዱን ጠዋት ሌላውን ማታ ትሠዋለህ። 40ከመጀመሪያው ጠቦት ጋር አንድ ኪሎ ግራም ምርጥ የሆነ የስንዴ ዱቄት ከአንድ ሊትር ተጨምቆ የተጠለለ የወይራ ዘይት ጋር ለውሰህ አቅርብ፤ አንድ ሊትር የወይን ጠጅም መባ አድርገህ አፍስስበት። 41ሁለተኛውንም ጠቦት በምሽት ጊዜ መሥዋዕት አድርገህ አቅርብ፤ በማለዳው መሥዋዕት ባቀረብከውም መጠን ተመሳሳይ ዱቄት፥ ዘይትና ወይን ጠጅ አቅርብ፤ ይህ ለእኔ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ የምግብ መባ ነው፤ መዓዛውም እኔን ደስ የሚያሰኝ ይሆናል። 42ለሚመጡት ዘመናት ሁሉ ይህ የሚቃጠል መሥዋዕት በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ መቅረብ አለበት፤ እኔ ሕዝቤን የምገናኘውና አንተንም የማነጋግርበት ስፍራ ይኸው ነው። 43በዚህም ከሕዝቤ ከእስራኤል ጋር እገናኛለሁ፤ ክብሬም ይህን ስፍራ የተቀደሰ ያደርገዋል። 44እኔ መሠዊያውንና ድንኳኑን እቀድሳለሁ፤ በክህነት ያገለግሉኝም ዘንድ አሮንንና ልጆቹን እለያለሁ። 45በእስራኤል ሕዝብ መካከል እኖራለሁ፤ አምላካቸውም እሆናለሁ፤ 46በመካከላቸው እኖር ዘንድ ከግብጽ ምድር መርቼ ያወጣኋቸው እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው መሆኔን ያውቃሉ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው ነኝ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘጸአት 29: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997