የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘጸአት 32

32
የወርቅ ጥጃ ምስል
(ዘዳ. 9፥6-29)
1ሕዝቡ ሙሴ ከተራራው ሳይወርድ እዚያ ብዙ እንደ ዘገየ ባዩ ጊዜ በአንድነት በመሰብሰብ አሮንን ከበው “ያ ከግብጽ ምድር መርቶ ያወጣን ሙሴ ምን እንደ ደረሰበት አናውቅም፤ ስለዚህ በፊት በፊታችን እየሄዱ የሚመሩን አማልክትን ሥራልን” አሉት። #ሐ.ሥ. 7፥40።
2አሮንም “ሚስቶቻችሁ፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ የሚያጌጡበትን የጆሮ ወርቅ ሁሉ ሰብስባችሁ አምጡልኝ” አላቸው።
3ስለዚህ ሁሉም ያላቸውን የወርቅ ጒትቻ ሁሉ አውልቀው ወደ አሮን አመጡለት። 4እርሱም የወርቅ ጒትቻውን ሁሉ ወስዶ በእሳት አቀለጠው፤ የቀለጠውንም ወርቅ በቅርጽ መሥሪያ ውስጥ አግብቶ የወርቅ ጥጃ አድርጎ ሠራው።
እነርሱም “እስራኤል ሆይ! ከግብጽ ምድር መርቶ ያወጣን አምላካችን ይህ ነው!” አሉ። #1ነገ. 12፥28፤ ሐ.ሥ. 7፥41።
5አሮንም ይህን ባየ ጊዜ በወርቁ ጥጃ ፊት መሠዊያ ሠርቶ “ነገ ለእግዚአብሔር ክብር በዓል ይደረጋል” ሲል አስታወቀ። 6በማግስቱ ሰዎቹ ተነሥተው የሚቃጠል መሥዋዕትና የአንድነት መሥዋዕት አቀረቡ፤ እነርሱም ተቀምጠው ከበሉና ከጠጡ በኋላ ከመጠን በላይ ሊፈነጥዙ ተነሡ። #1ቆሮ. 10፥7።
7እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ከግብጽ ምድር መርተህ ያወጣኸው ሕዝብህ ራሱን ስላረከሰ ፈጥነህ ውረድ፤ 8እነርሱ እንዲከተሉት ካዘዝኳቸው መንገድ ወዲያውኑ ወጥተዋል፤ ከቀለጠ ወርቅ ጥጃ ሠርተውም ሰግደውለታል፤ መሥዋዕትም አቅርበውለት ‘ከግብጽ ምድር ያወጣን አምላካችን ይህ ነው’ ብለዋል። 9እነርሱ ምን ያኽል ልበ ደንዳኖች እንደ ሆኑ እኔ ዐውቃለሁ፤ 10አሁንም እነሆ፥ በእነርሱ ላይ እጅግ ተቈጥቼ ላጠፋቸው ስለ ተዘጋጀሁ ተወኝ፤ አንተንም ታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ።”
11ሙሴ ግን እግዚአብሔር አምላኩን በመማለድ እንዲህ አለ፦ “እግዚአብሔር ሆይ፥ በሥልጣንህና በታላቅ ኀይልህ ከግብጽ ምድር ያወጣኸውን ሕዝብህን እስከዚህ የምትቈጣው ስለምነው? #ዘኍ. 14፥13-19። 12ግብጻውያን ‘እግዚአብሔር ከግብጽ ምድር መርቶ ያወጣቸው ለክፉ ነገር፥ ማለት በተራራዎች ላይ ሊገድላቸውና ፈጽሞ ሊያጠፋቸው ነው’ እያሉ መዘባበቻ እንዲያደርጉን ለምን ትፈቅዳለህ? አሁንም ከቊጣህ ወደ ምሕረት ተመለስ፤ ይህንንም ሁሉ ጥፋት በሕዝብህ ላይ አታምጣ። 13አገልጋዮችህን አብርሃምን፥ ይስሐቅንና ያዕቆብን አስብ፤ ዘራቸውን እንደ ሰማይ ከዋክብት ልታበዛውና የተስፋይቱንም ምድር ርስት ለዘለዓለም አድርገህ ልትሰጣቸው በመሐላ የገባህላቸውንም ቃል ኪዳን አስብ።” #ዘፍ. 22፥16-17፤ 17፥18። 14ስለዚህ እግዚአብሔር ከቊጣ ወደ ምሕረት ተመልሶ፥ ሊያመጣባቸው የነበረውን መቅሠፍት እንዲገታ አደረገ።
15ከዚህ በኋላ ሙሴ ተነሥቶ በሁለቱም በኩል ዐሥሩ ትእዛዞች የተጻፉባቸውን ሁለቱን የድንጋይ ጽላቶች በመያዝ ከተራራው ወረደ። 16እነዚህም ጽላቶች የእግዚአብሔር ሥራ ናቸው። በላያቸው ላይ ያሉት ጽሑፎች የተቀረጹት በእግዚአብሔር ነው።
17ኢያሱ የሕዝቡን ጫጫታ ሰምቶ ሙሴን “በሰፈሩ ውስጥ የጦርነት ድምፅ ይሰማል” አለው።
18ሙሴም “ይህ የምሰማው የዘፈን ድምፅ እንጂ የድል አድራጊዎች ድንፋታ ወይም የተሸነፈ ሕዝብ የለቅሶ ጫጫታ አይደለም” አለው።
19ሙሴም ወደ ሰፈሩ ተጠግቶ ጥጃውንና ጭፈራ ባየ ጊዜ እጅግ ተቈጣ፤ ይዞአቸው የመጣውንም ጽላቶች በተራራው ሥር ወርውሮ ሰባበራቸው። 20እነርሱ የሠሩትንም ጥጃ ወስዶ አቀለጠው፤ እስኪልም ድረስ አደቀቀውና ከውሃ ጋር ደባልቆ የእስራኤል ሕዝብ እንዲጠጣው አደረገ። 21አሮንንም “ከቶ ይህ ሕዝብ ምን አድርጎህ ነው ይህን የመሰለ አስከፊ ኃጢአት እንዲሠራ ያደረግኸው?” አለው።
22አሮንም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ጌታዬ በእኔ ላይ አትቈጣ፤ ይህ ሕዝብ ምን ያኽል የክፋት ዝንባሌ እንዳለው አንተ ታውቃለህ 23እነርሱ ‘ያ ከግብጽ መርቶ ያወጣን ሰው፥ ሙሴ ምን እንደ ደረሰበት አናውቅም፤ ስለዚህ በፊታችን እየሄዱ የሚመሩን አማልክት ሥራልን’ አሉኝ። 24እኔ ከወርቅ የተሠሩ ጌጣጌጦቻቸውን አውልቀው እንዲያመጡልኝ ነገርኳቸው፤ እነርሱም ያላቸውን ጌጣጌጥ ሁሉ አመጡልኝ፤ ጌጣጌጦቹንም ወደ እሳት ውስጥ በጣልኳቸው ጊዜ ይህ የጥጃ ምስል ወጣ።”
25አሮን ሕዝቡን በጠላቶቻቸው ፊት መሳለቂያ እስኪሆኑ ድረስ መረን እንደ ለቀቃቸው ሙሴ ተመለከተ። 26ስለዚህ በሰፈሩ ደጃፍ ቆሞ “የእግዚአብሔር ወገን የሆነ ሁሉ ወደ እኔ ይምጣ!” በማለት ድምፁን ከፍ አድርጎ ተናገረ፤ ሌዋውያንም ሁሉ በዙሪያው ተሰበሰቡ፤ 27እንዲህም አላቸው፦ “እያንዳንዳችሁ ሰይፋችሁን መዛችሁ ከዚህ በር እስከ ወዲያኛው በር ድረስ በሰፈሩ ውስጥ በመመላለስ ያለ ምንም ምሕረት ወንድሞቻችሁን፥ ወዳጆቻችሁንና ጐረቤቶቻችሁን እንድትገድሉ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር አዞአችኋል።” 28ሌዋውያንም ለቃሉ ታዛዦች በመሆን በዚያን ቀን ሦስት ሺህ ሰው ገደሉ። 29ሙሴም ሌዋውያንን እንዲህ አለ፤ “ዛሬ ልጆቻችሁንና ወንድሞቻችሁን በመግደል እግዚአብሔርን የምታገለግሉ ካህናት ሆናችሁ ራሳችሁን ቀድሳችኋል፤ እግዚአብሔርም በረከቱን ሰጥቶአችኋል።”
30በማግስቱም ሙሴ ለእስራኤላውያን “አስከፊ የሆነ ታላቅ በደል ሠርታችኋል፤ ነገር ግን እነሆ አሁንም እንደገና እግዚአብሔር ወደሚገለጥበት ተራራ እወጣለሁ፤ ምናልባት ስለ ኃጢአታችሁ ይቅርታ አስገኝላችሁ ይሆናል” አለ። 31ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተመልሶ እንዲህ አለው፤ “ይህ ሕዝብ አስከፊ የሆነ ታላቅ በደል በፊትህ ፈጽሞአል፤ ከወርቅ የሠሩትን ምስል አምላክ አድርገው ሰግደውለታል፤ 32እባክህ ኃጢአታቸውን ይቅር በል፤ ይቅር የማትላቸው ከሆነ ግን የሕዝብህ ስሞች ከተጻፉበት መዝገብ የእኔን ስም ደምስስ።” #መዝ. 69፥28፤ ራዕ. 3፥5።
33እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ስሞቻቸውን ከመዝገቤ የምደመስሰው ኃጢአት በመሥራታቸው ያሳዘኑኝን ሰዎች ነው። 34አሁንም ሂድ፤ ወደነገርኩህ ስፍራ ሕዝቡን ምራ፤ መልአኬም እየመራህ በፊትህ እንደሚሄድ አስታውስ፤ ነገር ግን ይህን ሕዝብ ስለ ኃጢአቱ የምቀጣበት ጊዜ መምጣቱ አይቀርም።”
35የወርቅ ጥጃ ምስል እንዲሠራላቸው አሮንን በማስገደዳቸው እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ከባድ በሽታ ላከ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ