የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘጸአት 33

33
እስራኤላውያን ከሲና ተነሥተው ጒዞ እንዲቀጥሉ እግዚአብሔር ማዘዙ
1እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “አንተና ከግብጽ ምድር መርተህ ያወጣኻቸው ሕዝብ ሁሉ ከዚህ ሰፈር ተነሥታችሁ፥ ለአብርሃም ለይስሐቅና ለያዕቆብ ለተወላጆቻቸው ጭምር ልሰጣቸው ቃል ወደገባሁላቸው ምድር ሂዱ። #ዘፍ. 12፥7፤ 26፥3፤ 28፥13። 2ፊት ፊትህ እየሄደ የሚመራህ መልአክ እልካለሁ፤ ከነዓናውያንን፥ አሞራውያንን፥ ሒታውያንን፥ ፈሪዛውያንን፥ ሒዋውያንንና ኢያቡሳውያንን ከፊትህ አባርራለሁ። 3የምትሄዱት በማርና በወተት ወደበለጸገች ለም ምድር ነው፤ ነገር ግን እናንተ እልኸኞች ስለ ሆናችሁ በመንገድ እንዳላጠፋችሁ አብሬአችሁ አልሄድም።”
4ሰዎቹም ይህን የሚያሳዝን ቃል በሰሙ ጊዜ ምርር ብለው አለቀሱ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ምንም ዐይነት ጌጣጌጥ ማድረግ አልፈለጉም። 5እግዚአብሔርም ለሕዝቡ እንዲህ ብሎ እንዲነግረው ሙሴን አዞት ነበር፦ “እናንተ እልኸኞች ስለ ሆናችሁ ለአንድ አፍታ እንኳ አብሬአችሁ ብሄድ ፈጽሞ እደመስሳችኋለሁ፤ አሁንም ጌጣጌጦቻችሁን አስወግዱ፤ ስለ እናንተ የማደርገውንም እወስናለሁ።” 6ስለዚህ የሲናን ተራራ ለቀው ከሄዱ በኋላ የእስራኤል ሕዝብ ምንም ዐይነት ጌጣጌጥ ማድረግ አልፈለጉም።
የመገናኛው ድንኳን
7የእስራኤል ሕዝብ በሰፈሩበት ቦታ ሁሉ ሙሴ ድንኳኑን ከሰፈሩ ራቅ ባለ ቦታ ይተክለው ነበር፤ እርሱም “ድንኳን” ተብሎ ተጠራ፤ እግዚአብሔርን መጠየቅ የሚፈልግ ሁሉ ወደዚያ ይሄድ ነበር። 8ሙሴ ወደዚያ በሄደ ቊጥር ሕዝቡ በየድንኳናቸው ደጃፍ ቆመው ሙሴ ወደ ድንኳን እስኪገባ ድረስ ይመለከቱታል። 9ሙሴም ወደዚያ ከገባ በኋላ የደመናው ዐምድ ወርዶ በድንኳኑ ደጃፍ ይቆማል፤ እግዚአብሔርም በደመናው ውስጥ ሆኖ ሙሴን ያነጋግረው ነበር። 10ሕዝቡ የደመናውን ዐምድ በድንኳኑ ደጃፍ ሲያዩ በየድንኳናቸው ደጃፍ ተንበርክከው ይሰግዱ ነበር። 11ሰው ከባልንጀራው ጋር እንደሚነጋገር እግዚአብሔር ሙሴን ፊት ለፊት ያነጋግረው ነበር፤ ከዚያም በኋላ ሙሴ ወደ ሰፈሩ ይመለሳል፤ የእርሱ ረዳት የነበረው ወጣት የነዌ ልጅ ኢያሱ ግን ከድንኳኑ አይለይም ነበር።
እግዚአብሔር ከሕዝቡ እንደማይለይ እንደገና የሰጠው ተስፋ
12ሙሴም እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፦ “ይህን ሕዝብ ወደዚያች ምድር መርቼ እንድወስድ አዝዘኸኛል፤ ነገር ግን ከእኔ ጋር ማንን እንደምትልክ አልነገርከኝም፤ እኔን እንደምታውቀኝና በእኔም ደስ እንደሚልህ ገልጠህልኛል፤ 13አሁንም በፊትህ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆነ ዐውቅ ዘንድ እንዳገለግልህና አንተን በማስደሰት እንድቀጥል እባክህ መንገድህን አሳየኝ፤ ይህም ሕዝብ ሕዝብህ እንደ ሆነ ተመልከት።”
14እግዚአብሔርም “እኔ ከአንተ ጋር እሄዳለሁ፤ ሰላምም እሰጥሃለሁ።” አሳርፍህማለሁ አለው።
15ሙሴም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ከእኛ ጋር የማትወጣ ከሆንክ፥ እኛንም ከዚህ ስፍራ አታውጣን፤ 16ከእኛ ጋር የማትወጣ ከሆነ በሕዝብህም ሆነ በእኔና በሕዝብህ ደስ መሰኘትህን ሰዎች ሁሉ እንዴት ሊያውቁ ይችላሉ? እኛን በምድር ላይ ካሉት ከሌሎች ሕዝቦች ሁሉ የተለየ የሚያደርገን የአንተ ከእኔና ከሕዝብህ ጋር መሆን አይደለምን?”
17እግዚአብሔርም ሙሴን “እኔ አንተን በሚገባ በትክክል ስለማውቅህና በአንተም ደስ ስለምሰኝ የምትለውን ሁሉ አደርጋለሁ” አለው።
18ሙሴም እግዚአብሔርን “እባክህን ክብርህን አሳየኝ” አለው።
19እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ደግነቴን ሁሉ በፊትህ አሳልፋለሁ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ስሜን በፊትህ ዐውጃለሁ፤ የምምረውን እምራለሁ፤ የምራራለትንም እራራለታለሁ፤ #ሮም 9፥15። 20ፊቴን አይቶ ለመኖር የሚችል ሰው ስለሌለ ፊቴን ለማየት አትችልም። 21ነገር ግን እዚህ በአጠገቤ በአለት ላይ የምትቆምበት ስፍራ አለ። 22የእኔ ክብር በዚያ ሲያልፍ በአለቱ ስንጣቂ አቈይሃለሁ፤ እስካልፍ ድረስ በእጄ እጋርድሃለሁ፤ 23ከዚያም በኋላ እጄን አነሣለሁ፤ አንተም ፊቴን ሳይሆን ጀርባዬን ታያለህ።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ