የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘጸአት 35

35
የሰንበት አከባበር ሥርዓት
1ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ በአንድነት ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ትፈጽሙት ዘንድ እግዚአብሔር የሰጣችሁ ትእዛዝ ይህ ነው፤ 2ሥራችሁን ሁሉ የምትሠሩባቸው ስድስት ቀኖች አሉላችሁ፤ ሰባተኛው ቀን ግን ዕረፍት ታደርጉበት ዘንድ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ዕለት ነው፤ በዚህ ቀን ሥራ የሚሠራበት ማንኛውም ሰው በሞት ይቀጣል፤ #ዘፀ. 20፥8-11፤ 23፥12፤ 31፥15፤ 34፥21፤ ዘሌ. 23፥3፤ ዘዳ. 5፥12-14። 3ስለዚህ በሰንበት ቀን በቤታችሁ እሳት እንኳ አታንድዱ።”
ለተቀደሰው ድንኳን ሥራ የሚቀርብ መባ
(ዘፀ. 25፥1-9)
4ሙሴ ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር ያዘዘው ነገር ይህ ነው፤ 5ለእግዚአብሔር መባ አቅርቡ፤ መባ ለማቅረብ የፈለገ ሁሉ እያንዳንዱ ልቡ የፈቀደውን ያኽል የወርቅ፥ የብር፥ ወይም የነሐስ 6ጥሩ ከፈይ ሰማያዊ፥ ሐምራዊና ቀይ ቀለም የተነከረ የበግ ጠጒር፥ ከፍየል ጠጒር የተሠራ ልብስ፥ 7ቀይ ቀለም የተነከረ የአውራ በግ ቆዳ፤ የለፋ ቊርበት፥ የግራር እንጨት፥ 8ለመብራት የሚሆን የወይራ ዘይት፥ ለቅባት ዘይትና ለዕጣን ሽታ የሚሆን ቅመማ ቅመም፥ 9በተቀደሰው ኤፉድና የደረት ኪስ ላይ የሚሆን መረግድና ሌላውንም ጌጠኛ ፈርጥ ያምጣ።
የመገናኛው ድንኳኑ መገልገያ ዕቃዎች
(ዘፀ. 39፥34-43)
10“በመካከላችሁ የሚገኙ የእጅ ጥበብ ዐዋቂዎች ሁሉ እግዚአብሔር ያዘዘውን ማናቸውንም ነገር ለመሥራት ይምጡ፤ 11ይኸውም ድንኳኑን፥ የውስጥና የውጪ መደረቢያዎችን፥ መያዣዎችንና ተራዳዎችን መወርወሪያዎችንና ምሰሶዎችን፥ እግሮቹን፥ 12የኪዳኑን ታቦት፥ መሎጊያዎቹን፥ የስርየት መክደኛውንና የታቦቱ መሸፈኛ የሆነውን መጋረጃ፥ 13ጠረጴዛውን፥ መሎጊያዎቹንና የእርሱንም መገልገያ ዕቃዎች ሁሉ እንዲሁም ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን የተቀደሰ ኅብስት 14ለመብራት ማኖሪያ የሚሆነውን መቅረዝና የእርሱንም መገልገያ ዕቃዎች፥ መብራቶቹም ከዘይታቸው ጋር፥ 15የዕጣን መሠዊያውንና መሎጊያዎቹን፥ የቅባቱን ዘይት፥ ጣፋጭ ሽታ ያለውን ዕጣን፥ የድንኳኑን በር መጋረጃ፥ 16የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበትን መሠዊያ፥ የነሐሱንም መከላከያ መሎጊያዎቹንና የእርሱን መገልገያ ዕቃዎች ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሳሕንና ማስቀመጫውን፥ 17ያደባባዩን መጋረጃዎች፥ ምሰሶዎቹንና እግሮቻቸውን፥ የአደባባዩን በር መጋረጃዎች፥ 18የድንኳኑንና የአደባባዩን ካስማዎች፥ አውታሮችና 19ካህናቱ በተቀደሰው ስፍራ በሚያገለግሉበት ጊዜ የሚለብሱአቸው በጥበብ ያጌጡ ልብሶችን ይኸውም ለካህኑ ለአሮንና ለልጆቹ የተሠሩትን የተቀደሱ ልብሶች ይሥሩ።”
ሕዝቡ ያመጡት ስጦታ
20ከዚህ በኋላም የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ከሙሴ ፊት ወጡ፤ 21ለመሥራት እያንዳንዱ ለመስጠት ልቡ የፈቀደውን ለእግዚአብሔር መባ አመጣ፤ በዚህም ዐይነት እስራኤላውያን ለመንፈሳዊ አገልግሎት ለካህናት ልብስ የሚሆነውን ነገር ሁሉ አመጡ። 22ስጦታ ማቅረብ የፈለገ ሴቱም ወንዱም እያንዳንዱ የደረት ጌጥ፥ የጆሮ ወርቅ፥ የጣት ቀለበት፥ ድሪዎችና የወርቅ ጌጦችን አምጥቶ ለእግዚአብሔር የተለዩ እንዲሆኑ አደረገ። 23ጥሩ በፍታ፥ ሰማያዊ፥ ሐምራዊና ቀይ ከፈይ ከፍየል ጠጒር የተሠራ ልብስ፥ ቀይ ቀለም የተነከረ የአውራ በግ ቆዳ፤ እንዲሁም የለፋ ቊርበት ያለው ሁሉ ይዞ መጣ። 24ብር ወይም ነሐስ ለማቅረብ ችሎታ ያላቸውም ሁሉ ስጦታቸውን ለእግዚአብሔር አመጡ፤ ለማንኛውም አገልግሎት የሚውል የግራር እንጨት ያለውም አመጣ። 25የእጅ ጥበብ ችሎታ ያላቸው ሴቶችም በእጃቸው የሠሩትን ጥሩ በፍታና ሰማያዊ፥ ሐምራዊና ቀይ ከፈይ ይዘው መጡ፤ 26እንዲሁም ስጦታ ለማቅረብ የፈለጉ ሴቶች ከፍየል ጠጒር የተገመደ ክር ሠሩ፤ 27አለቆችም በተቀደሰው ኤፉድና በደረት ኪስ ላይ የሚሆኑ መረግድና ሌሎችም ጌጣጌጦች፥ 28ለመብራትና ለቅባት እንዲሁም ጣፋጭ ሽታ ለሚሰጥ ዕጣን የሚሆን ቅመማ ቅመምና ዘይት አመጡ፤ 29ወንዶችና ሴቶች የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ እግዚአብሔር ሙሴን ላዘዘው ሥራ የሚውል ልባቸው የፈቀደውን ስጦታ ለእግዚአብሔር አመጡ።
የመገኛውን ድንኳን የሚሠሩ የእጅ ጥበብ ዐዋቂዎች
(ዘፀ. 31፥1-11)
30ሙሴ ለእስራኤላውያን እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር ከይሁዳ ወገን የሑር የልጅ ልጅ የሆነውን የኡሪ ልጅ ባጽልኤልን መርጦታል፤ 31እግዚአብሔር እርሱን በመንፈሱ ኀይል እንዲሞላ አድርጎ ማናቸውንም የጥበብ ሥራ መሥራት እንዲችል ብልኀትን፥ ችሎታንና ማስተዋልን ሰጥቶታል። 32ጥበብ የሞላበትን የሥራ ዕቅድ ለማውጣት፥ ያንንም ዕቅድ በወርቅ በብርና በነሐስ ለማስጌጥ፥ 33የዕንቊ ጌጣጌጦችን ለመሥራትና የእንጨት ቅርጾችን ለማውጣት እንዲሁም ሌሎችን የጥበብ ሥራዎች ለማከናወን ችሎታ ሰጥቶታል። 34ለእርሱና ከዳን ወገን የአሒሳማክ ልጅ ለሆነው ኦሆሊአብ የእጅ ጥበብ ዕውቀታቸውን ለሌሎች የማስተማርን ችሎታ ሰጥቶአቸዋል። 35በአንጥረኛ፥ በፕላን አውጪ ባለሞያ፥ ጥሩ በፍታ፥ ሰማያዊ፥ ሐምራዊና ቀይ ቀለም የተነከረ ከፈይ ሌላውንም የልብስ ሥራ በሚያከናውኑ ሸማኔዎች የተሠራውን ነገር ሁሉ ለማስጌጥ የሚችሉበትን ብልኀት ሰጥቶአቸዋል፤ እነርሱ ማናቸውንም የጥበብ ሥራ ለመሥራትና በብልኀት የሚሠራውንም ሁሉ ዕቅድ ለማውጣት የሚችሉ ናቸው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ