የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘጸአት 36

36
1“ባጽልኤልና ኦሆሊአብ እንዲሁም ለተቀደሰው ድንኳን ዝግጅት እግዚአብሔር ማናቸውንም ሥራ ለመሥራት ችሎታንና ዕውቀትን የሰጣቸው ሌሎች ሰዎች እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ይሠራሉ።”
የሕዝቡ ስጦታ ብዛት
2ሙሴም ባጽልኤልንና ኦሆሊአብን፥ እንዲሁም እግዚአብሔር ልዩ ችሎታ የሰጣቸውንና ለመርዳት ፈቃደኞች የነበሩትን ሌሎችን ጥበበኞች ሁሉ ጠርቶ ሥራውን እንዲጀምሩ ነገራቸው። 3እነርሱም እስራኤላውያን ለተቀደሰው ድንኳን መሥሪያ እንዲውል ያመጡትን ስጦታ ከሙሴ እጅ ተቀበሉ፤ የእስራኤል ሕዝብ ግን በየማለዳው ስጦታቸውን ለሙሴ ከማምጣት አልተቈጠቡም። 4ከዚህም በኋላ ሥራውን የሚያከናውኑት ጥበበኞች ሁሉ ሥራቸውን ትተው ወደ ሙሴ በመሄድ፥ 5“ሕዝቡ እግዚአብሔር ላዘዘው ሥራ ከሚያስፈልገው በላይ እጅግ ብዙ ስጦታ በማምጣት ላይ ናቸው” አሉት።
6ስለዚህ ሙሴ ለተቀደሰው ድንኳን መሥሪያ የሚሆን ስጦታ ከእንግዲህ ወዲህ እንዳያመጡ በሰፈሩ ሁሉ ትእዛዝ አስተላለፈ፤ ከዚያም በኋላ ሕዝቡ ስጦታ ማምጣቱን አቆመ፤ 7የቀረበውም ስጦታ ሥራውን ሁሉ ለማከናወን በቅቶ የሚተርፍ ነበር።
የመገናኛው ድንኳን አሠራር
(ዘፀ. 26፥1-37)
8ሥራውን ከሚያከናውኑት መካከል እጅግ ጥበበኞች የነበሩት የተቀደሰውን ድንኳን ሠሩ፤ እነርሱም ድንኳኑን ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊና ከቀይ ከፈይ ከተፈተሉ፥ የኪሩቤል ሥዕል ከተጠለፈባቸው ዐሥር የበፍታ መጋረጃዎች ሠሩት። 9የእያንዳንዱም መጋረጃ መጠን ተመሳሳይ ሆኖ ርዝመቱ ዐሥራ ሁለት ሜትር፥ የጐኑ ስፋት ሁለት ሜትር ነበር። 10እነርሱንም አምስቱን በአንድ በኩል፥ ሌሎቹንም አምስቱን በሌላ በኩል አገጣጥመው ሰፉ። 11ከተገጣጠሙት መጋረጃዎች በአንደኛው ክፍል ጠርዝ ላይ ከሰማያዊ ግምጃ የተሠሩ ቀለበቶችን አደረጉ፤ በሌላም በኩል ተገጣጥመው ከተሰፉት መጋረጃዎችም በአንደኛው ጠርዝ ላይ እንዲሁ አደረጉ፤ 12በመጀመሪያው ክፍል የመጀመሪያ መጋረጃ ላይ ኀምሳ ቀለበቶች፥ እንዲሁም በሁለተኛው ክፍል መጨረሻ መጋረጃ ላይ ከሌሎቹ ቀለበቶች ፊት ለፊት የሚሆኑ ኀምሳ ቀለበቶች አደረጉ። 13በሁለቱም በኩል ያሉትን መጋረጃዎች አገጣጥሞ አንድ ለማድረግ ኀምሳ የወርቅ መያዣዎች ሠሩላቸው።
14ለድንኳኑ መክደኛ የሚሆኑ ዐሥራ አንድ መጋረጃዎችንም ከፍየል ጠጒር የተፈተለ ጨርቅ አዘጋጁ። 15የሁሉም መጠን እኩል ሆኖ የእያንዳንዱ መጋረጃ ርዝመት ዐሥራ ሦስት ሜትር፥ የጐኑም ስፋት ሁለት ሜትር ነበር። 16አምስቱን በአንድ በኩል፥ ስድስቱንም በሌላ በኩል በማድረግ አገጣጥመው ሰፉአቸው። 17በአንደኛው ክፍል የመጨረሻ መጋረጃ ዘርፍ ላይ ኀምሳ ቀለበቶች፥ በሁለተኛው ክፍል የመጨረሻ መጋረጃ ዘርፍ ላይ ኀምሳ ቀለበቶች አስገቡ። 18በሁለቱም በኩል ያሉትን መጋረጃዎች አገጣጥመው አንድ መክደኛ ለማበጀት ኀምሳ የነሐስ መያዣዎችን ሠሩ። 19ከውጪ በኩል መክደኛ ይሆኑ ዘንድ አንደኛውን ቀይ ቀለም ከተነከረ የአውራ በግ ቆዳ፥ ሌላውንም ከለፋ ቊርበት ሌሎች ሁለት መጋረጃዎችን ሠሩ።
20ለድንኳኑም መደገፊያ ቀጥተኛ የሆኑ ተራዳዎች ከግራር እንጨት ሠሩ፤ 21እያንዳንዱ ተራዳ ቁመቱ አራት ሜትር የጐኑም ስፋት ሥልሳ ስድስት ሳንቲ ሜትር ሲሆን፥ 22የተራዳው ሁለት ሳንቃዎች መገጣጠም ይችሉ ዘንድ ማያያዣዎች ነበሩአቸው፤ ለማደሪያው ተራዳዎች ሁሉ እንዲሁ አደረጉ። 23በድንኳኑም በደቡብ በኩል ኻያ ተራዳዎች አደረጉ፤ 24ከኻያውም ተራዳዎች በታች ሁለት ማገጣጠሚያ ጒጦች ባሉት በእያንዳንዱ ተራዳ ሥር ሁለት ሁለት በማኖር አርባ የብር እግሮችን አደረጉ። 25ከድንኳኑ በስተ ሰሜን በኩል ኻያ ተራዳዎችን አደረጉ፤ 26በእያንዳንዱም ተራዳ ሥር ሁለት ሁለት በማኖር አርባ የብር እግሮችን አደረጉ፤ 27ከድንኳኑ በስተጀርባ በምዕራብ በኩል ስድስት ተራዳዎችን አደረጉ፤ 28በስተጀርባ ማእዘኖቹም ሁለት ሁለት ተራዳዎች ሠሩ። 29እነዚህ በማእዘኖቹ ያሉት ተራዳዎች በግርጌ በኩል ተገጣጥመው እስከ ላይ አንደኛው ዋልታ ድረስ የተያያዙ ነበሩ፤ በሁለቱ ማእዘኖች ላይ የተደረጉት ሁለቱ ተራዳዎች የተሠሩት በዚህ ዐይነት ነበር። 30ስለዚህ እያንዳንዱ ተራዳ በሥሩ ሁለት እግሮች እንዲኖሩት በማድረግ ስምንት ተራዳዎችና ከብር የተሠሩ ዐሥራ ስድስት እግሮች ነበሩ።
31ዐሥራ አምስት መወርወሪያዎችንም ከግራር እንጨት ሠሩ፤ በዚህ ዐይነት አምስቱ ከድንኳኑ በአንድ በኩል ላሉት ተራዳዎች ሲሆኑ፥ 32አምስቱ ደግሞ በሌላ በኩል ላሉት ተራዳዎች ሆኑ፤ እንዲሁም አምስቱ ከድንኳኑ በስተጀርባ በምዕራብ በኩል እንዲሆኑ ተደረገ። 33ከተራዳዎቹ በጐን በኩል በመካከል ያለው መወርወሪያ ከድንኳኑ ከአንድ ጫፍ መጨረሻ ተያይዞ እስከ ሌላው ጫፍ ይደርስ ነበር። 34ተራዳዎቹንም በወርቅ ለበጡአቸው፤ ዋልታዎቻቸውንም የመወርወሪያው መተላለፊያ ይሆኑ ዘንድ ከወርቅ ሠሩ፤ መወርወሪያዎቹም በወርቅ የተለበጡ ነበሩ።
35መጋረጃዎችንም ከጥሩ በፍታ ሠሩ፤ እርሱም ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊና ከቀይ ከፈይ የተፈተለ ሲሆን የኪሩቤል ሥዕል ተጠልፎበት ነበር። 36መጋረጃዎቹን የሚያያይዙ አራት ምሰሶዎችንም ከግራር እንጨት ሠርተው በወርቅ ለበጡአቸው፤ ኩላቦቻቸውንም ከወርቅ ሠሩ፤ ምሰሶዎቹ የሚቆሙባቸውን አራት እግሮችንም ከብር ሠሩ፤ 37ለድንኳኑም ደጃፍ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊና ቀይ ከፈይ በጥልፍ የተጌጠ መጋረጃ ሠሩ፤ 38ለዚህም መጋረጃ ኩላቦች ያሉአቸው አምስት ምሰሶዎችን ሠሩ፤ የእነርሱንም ጒልላቶችና ዘንጎቹን በወርቅ ለበጡ፤ ለምሰሶዎቹም ማቆሚያ አምስት የነሐስ እግሮች ሠሩ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ