ትንቢተ ሕዝቅኤል 11
11
በኢየሩሳሌም ላይ የተላለፈ ፍርድ
1የእግዚአብሔር መንፈስ ከምድር ወደ ላይ አንሥቶ በምሥራቅ ትይዩ ወደ ሆነው በእግዚአብሔር ቤት ወደ አለው ወደ ምሥራቁ በር አመጣኝ፤ እዚያም በቅጽር በሩ አጠገብ ኻያ አምስት ሰዎችን አየሁ፤ በእነርሱም መካከል የሕዝብ መሪዎች የሆኑት የዐዙር ልጅ አዛንያና የበናያ ልጅ ፈላጥያ ይገኙባቸዋል።
2እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! እነዚህ ሰዎች መጥፎ ዕቅድ ያወጣሉ፤ በዚህችም ከተማ ክፉ ምክር ይመክራሉ፤ 3‘እንደገና መልሰን ቤቶችን የምንሠራበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፤ ከተማይቱ እንደ ሥጋ መቀቀያ ሰታቴ ስትሆን፥ እኛ ደግሞ በውስጥዋ እንደ ሥጋ ሆነናል’ ብለዋል። 4ስለዚህ የሰው ልጅ ሆይ፥ በእነርሱ ላይ ትንቢት ተናገርባቸው፤ ትንቢት ተናገር።”
5ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ወረደ፤ እንዲህም አለኝ፦ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ተናገር፦ የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! ይህን ነገር ተናግራችኋል፤ እኔም በሐሳባችሁ ያለውን ነገር ዐውቃለሁ። 6በዚህች ከተማ ብዙ ሰው ገድላችኋል፤ መንገዶችዋንም በሬሳ ሞላችኋቸው።
7“ስለዚህ እኔ ልዑል እግዚአብሔር የምላችሁ ይህ ነው፦ ‘በሰታቴው ውስጥ ያለው ሥጋ እናንተ የገደላችኋቸው ሰዎች ናቸው፤ ይህችም ከተማ ሰታቴዋ ነች፤ እናንተ ግን ከከተማይቱ ትወገዳላችሁ። 8እናንተ ጦርነትን ፈርታችኋል፤ እኔ ግን ጦርነትን አመጣባችኋለሁ እኔ ጌታ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ። 9እናንተን ከከተማይቱ አስወጥቼ ለባዕዳን ሕዝቦች አሳልፌ በመስጠት እፈርድባችኋለሁ። 10ስለዚህም በገዛ አገራችሁ ድንበር ላይ በጦርነት ትገደላላችሁ፤ በእስራኤል ድንበር ላይ እፈርድባችኋለሁ፤ በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ። 11ይህች ከተማ ለእናንተ ሰታቴ አትሆንላችሁም፤ እናንተም በውስጥዋ እንደ ሥጋ አትሆኑም፤ በእስራኤል ድንበር ላይ እፈርድባችኋለሁ። 12የእኔን ሕግና ሥርዓት በመሻር በጐረቤት ያሉ ሕዝቦችን ሥርዓት በመፈጸማችሁ የፈረድኩባችሁ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ።’ ”
13እኔም ትንቢት በምናገርበት ጊዜ የበናያ ልጅ ፈላጥያ ወድቆ ሞተ፤ እኔም በግንባሬ ወደ መሬት ተደፍቼ በመጮኽ “ልዑል እግዚአብሔር ሆይ! በእስራኤል የተረፉትን ሁሉ ልትፈጅ ነውን?” አልኩ።
እግዚአብሔር ለስደተኞች የሰጠው ተስፋ
14እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ 15“የሰው ልጅ ሆይ! የኢየሩሳሌም ኗሪዎች ስለ ሥጋ ዘመዶችህ፥ ስለ ተሰደዱት ወገኖችህ፥ በአጠቃላይ ስለ መላው የእስራኤል ሕዝብ በመነጋገር ላይ ናቸው፤ ‘እነርሱ ከእግዚአብሔር ርቀው ስለ ሄዱ እግዚአብሔር ምድሪቱን ለእኛ ርስት አድርጎ ሰጥቶናል’ ይላሉ”።
16ስለዚህ ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሩቅ አገር በሚኖሩ ሕዝቦች መካከል እንዲኖሩ ባደርጋቸውና በተለያዩ አገሮች ብበትናቸውም እንኳ ለጥቂት ጊዜ ግን መገናኛቸው ቤተ መቅደስ እሆንላቸዋለሁ።
17“ስለዚህ እኔ እግዚአብሔር የምለውን ሁሉ ንገራቸው፤ እነሆ፥ ከሕዝቦች መካከልና ከተበታተናችሁባቸው አገሮች እሰበስባችኋለሁ፤ የእስራኤልንም ምድር እንደገና እሰጣችኋለሁ። 18በሚመለሱበት ጊዜ የሚያገኙአቸውን አጸያፊና ርኩስ የሆኑ ጣዖቶችን ወዲያ ያስወግዳሉ። 19አንድ ልብ እሰጣቸዋለሁ አዲስ መንፈስንም በውስጣቸው አኖራለሁ፤ ከሰውነታቸው እንደ ድንጋይ የጠጠረ ልብን አውጥቼ እንደ ሥጋ የለሰለሰ ልብን እሰጣቸዋለሁ። #ሕዝ. 36፥28። 20በዚያን ጊዜ ሕጌን ይፈጽማሉ፤ ሥርዓቴንም ሁሉ ያከብራሉ፤ እነርሱ ሕዝቤ ይሆናሉ፤ እኔም አምላካቸው እሆናለሁ። 21ልባቸው ርኩስና አጸያፊ የሆኑ ጣዖቶችን የሚከተሉትን ግን እንደ ሥራቸው እከፍላቸዋለሁ፤” ይህን የተናገረ ልዑል እግዚአብሔር ነው።
የእግዚአብሔር ክብር ከኢየሩሳሌም መለየት
22በዚህ ጊዜ ኪሩቤል ክንፎቻቸውን ዘርግተው መብረር ጀመሩ፤ መንኰራኲሮቹም ከጐናቸው ነበሩ፤ የእስራኤል አምላክ አንጸባራቂ ክብር ከበላያቸው ነበር፤ 23የእግዚአብሔርም አንጸባራቂ ክብር ከከተማይቱ ውስጥ ተነሥቶ ከከተማይቱ በስተ ምሥራቅ ወዳለው ተራራ ላይ ቆመ። #ሕዝ. 43፥2-5። 24በራእይም የእግዚአብሔር መንፈስ ከምድር ወደ ላይ አንሥቶ በባቢሎን ወዳሉት ስደተኞች አመጣኝ፤ ከዚህ በኋላ ራእዩ ከእኔ ተለየ። 25እኔም እግዚአብሔር ያሳየኝን ሁሉ ለስደተኞቹ ነገርኳቸው።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 11: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997