ትንቢተ ሕዝቅኤል 13
13
በሐሰተኞች ነቢያት ላይ የተነገረ ትንቢት
1እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ 2“የሰው ልጅ ሆይ! ከራሳቸው ሐሳብ አፍልቀው ትንቢት በሚናገሩ የእስራኤል ነቢያት ላይ ትንቢት ተናገር፤ ይልቅስ የእግዚአብሔርን ቃል እንዲሰሙ ንገራቸው።”
3ልዑል እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፦ “ከአሳባቸው አፍልቀው ትንቢት ለሚናገሩና ራእይ ሳያዩ ‘ራእይ አይተናል’ ለሚሉ ለእነዚህ ለሞኞች ነቢያት ወዮላቸው! 4የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! ነቢዮቻችሁ በፍርስራሽ ቦታዎች መካከል እንደሚኖሩ ቀበሮዎች ናቸው። 5በእግዚአብሔር ቀን ጦርነቱን ለመቋቋም ይቻል ዘንድ ወደ ፍርስራሹ አልወጣችሁም፤ ወይም የእስራኤልን ቅጥር አልጠገናችሁም። 6ራእያቸው ሐሰት ነው፤ ሟርታቸውም ውሸት ነው፤ እግዚአብሔር ሳይልካቸው እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ይላሉ፤ ይህም ሆኖ ቃላቸው ተፈጻሚነት እንደሚኖረው ይገምታሉ። 7እኔ ያልተናገርኩትን ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል’ ብላችሁ በምትናገሩበት ጊዜ ሐሰተኛ ራእይን ያያችሁና ሟርትን ያሟረታችሁ አይደለምን?”
8ስለዚህ ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላቸዋል፦ “ሐሰትን ስለ ተናገራችሁና ራእያችሁም ውሸት ስለ ሆነ እኔ በእናንተ ላይ እነሣለሁ። ይህንን የተናገርኩ እኔ ጌታ እግዚአብሔር ነኝ። 9ሐሰተኛ ራእይ በሚያዩና ሟርትን በሚያሟርቱ ነቢያት ላይ እጄን አነሣለሁ፤ እነርሱ በሕዝቤ ማኅበር ውስጥ አይገኙም፤ እንዲያውም በእስራኤል ሕዝብ መዝገብ ውስጥ አይመዘገቡም፤ ወደ እስራኤል ምድርም አይገቡም፤ በዚያን ጊዜ እኔ ልዑል እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ።
10“እነዚህ ነቢያት የማይታመኑ ሆኑ፤ ሰላም በሌለበት ሰላም አለ ብለው ለሕዝቤ ይናገራሉ፤ የዘመመ ግድግዳን ቀለም በመቀባት ያደሱ የሚመስላቸው ሠራተኞችን ይመስላሉ። #ኤር. 6፥14፤ 8፥11። 11ዶፍ ዝናብ ይዘንባል ታላቅ የበረዶ ድንጋዮች ይወርዳሉ፤ ዐውሎ ነፋስም ይነሣል፤ ስለዚህ ግድግዳውን ቀለም ለቀቡ ሰዎች ግድግዳው ይወድቃል በላቸው። 12ግድግዳው በሚፈርስበት ጊዜ የቀባችሁት ቀለም የት አለ ብለው ሰዎች አይጠይቁአችሁምን?”
13ስለዚህ ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የኢየሩሳሌምን ቅጽር ለማጥፋት በቊጣዬ ዐውሎ ነፋስ እንዲነሣ አደርጋለሁ። ዶፍ ዝናብና የበረዶ ናዳ ይወርዳል። 14መሠረት ተጋልጦ ከምድር ወለል ጋር እስኪስተካከል ድረስ በቀለም የቀባችሁትን ግድግዳ አፍርሼ እጥለዋለሁ፤ ግድግዳው በሚወድቅበት ጊዜ እናንተም በውስጡ ትጠፋላችሁ፤ በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ።
15“በቅጥሩ ላይና ቅጥሩን ቀለም በቀቡበት ላይ ኀይለኛ ቊጣዬን አወርዳለሁ፤ ከዚያም በኋላ ቅጥሩም ሆነ ቅጥሩን ቀለም የቀቡት አይኖሩም እላችኋለሁ። 16እነርሱም ስለ ኢየሩሳሌም ትንቢት የተናገሩና ራእይ ያዩ ሰላም ሳይኖር ‘ሰላም አለ’ ያሉ የእስራኤል ነቢያት ናቸው፤ ይህን የተናገርኩ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ነኝ።”
ሐሰተኞች በሆኑ ሴቶች ነቢያት ላይ የተነገረ ትንቢት
17እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “አሁንም የሰው ልጅ ሆይ! በሕዝብህ መካከል ከአሳባቸው አፍልቀው ትንቢት በሚናገሩት ሴቶች ላይ አተኲረህ ትንቢት ተናገርባቸው፤ 18ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ንገራቸው፦ በጡንቻ ላይ የሚደረግ አሸን ክታብን ለሚሰፉ፥ የሰውንም ሕይወት ለማጥመድ በተለያየ ቁመት የራስ መሸፈኛ ሻሽ ለሚያዘጋጁ ሴቶች ወዮላቸው! ከእኔ ሕዝብ መካከል ሰዎችን አጥምዳችሁ እናንተ በሕይወት ትኖራላችሁን? 19እፍኝ ገብስ እና ቊራሽ እንጀራ ለማግኘት ብላችሁ ሐሰትን ለሚያዳምጡ ለሕዝቤ ሐሰትን እየተናገራችሁ መሞት የማይገባቸውን ሰዎች በመግደልና መኖር የማይገባቸውን ሰዎች እንዲኖሩ በማድረግ ስሜ በሕዝቤ ዘንድ እንዲሰደብ አድርጋችኋል።”
20ስለዚህ ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሕዝቡን የምታጠምዱባቸውን አሸን ክታቦቻችሁን እጠላለሁ፤ አሸንክታባችሁን ከጡንቻዎቻችሁ ላይ በጣጥሼ በመጣል እንደ ወፎች የምታጠምዱአቸውን ነፍሳት ነጻ አወጣለሁ። 21መሸፈኛ ሻሻችሁን ቀድጄ ሕዝቤን ከእጃችሁ አድናለሁ፤ ዳግመኛ በእናንተ እጅ አይወድቁም፤ እናንተም እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ።
22“እኔ ተስፋ ያላስቈረጥኳቸውን ጻድቃንን ሐሰት በመናገር ተስፋ አስቈርጣችኋል፤ ክፉዎች ሕይወታቸውን ለማዳን ከኃጢአታቸው እንዳይመለሱ አደፋፍራችኋል። 23ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲያ ሐሰተኛ ራእይ አታዩም፤ የሟርተኝነትንም ሥራ አትሠሩም፤ ሕዝቤን ከእጃችሁ አድናለሁ፤ በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 13: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997