የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሕዝቅኤል 24

24
ዝገት የበላው የብረት ድስት
1በተሰደድን በዘጠነኛው ዓመት፥ በዐሥረኛው ወር፥ በዐሥረኛው ቀን፥ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረኝ፦ 2“የሰው ልጅ ሆይ! የባቢሎን ንጉሥ ኢየሩሳሌምን መክበብ የሚጀምርበት ስለ ሆነ ይህን የዛሬውን ዕለት በመዝገብ ጻፈው፤ #2ነገ. 25፥1፤ ኤር. 52፥4። 3እኔ ልዑል እግዚአብሔር ስለ እነርሱ የመሰልኩትን ይህን ምሳሌ ዐመፀኞች ለሆኑት ሕዝቤ ንገራቸው፤
‘ድስት በእሳት ላይ ጥደህ ውሃ አድርግበት፤
4ጭንና ወርች የመሳሰሉትን ጥሩ የሥጋ ብልቶች ቈራርጠህ፥
ምርጥ የሆኑትንም አጥንቶች ሰባብረህ በውስጡ ጨምር።
5ከመንጋው መካከል ምርጥ በግ ውሰድና ዕረድ፤
ከድስቱም ሥር ማገዶ ጨምር፤
ሥጋውንና አጥንቱን እስኪበስል ድረስ ቀቅለው።’ ”
6ልዑል እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፦ “ለነፍሰ ገዳዮች ከተማ ወዮላት! ከዝገቱ እንዳልጠራና ከቶም እንደማይጠራ ብረት ድስት ሆናለች፤ በውስጥዋ ያለውን ቊራጭ ሥጋ ሳትመርጥ አንድ በአንድ አውጣው። 7በከተማይቱ ውስጥ ግድያ ተፈጽሞአል፤ ደሙም የፈሰሰው ትቢያ በሚሸፍነው መሬት ላይ አይደለም፤ ነገር ግን ደሙ የፈሰሰው ምንም በማይሸፍነው ገላጣ አለት ላይ ነው። 8እርስዋ ያፈሰሰችው ደም እንዳይሸፈን በገላጣ አለት ላይ እንዲፈስ ያስደረግኹት ከፍተኛ ቊጣዬን አስነሥቶ በቀል እንድበቀል ነው።”
9ስለዚህ ልዑል እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፦ “ለነፍሰ ገዳዮች ከተማ ወዮላት! ማገዶውን እኔ ራሴ አብዝቼ እጨምራለሁ። 10ብዙ እንጨት አምጣ! እሳቱንም አቀጣጥል፤ ሥጋውን ቀቅል! መረቁን በቅመም አጣፍጠው! አጥንቱን አቃጥለው! 11-12የዝገቱ ብዛት በእሳት እንኳ ስላልለቀቀ ጥረቶች ሁሉ ከንቱ ሆነዋል። ስለዚህ ከነሐስ የተሠራውን ባዶ ብረት ድስት በፋመው ከሰል ላይ ጣደው፤ ፍም እስኪመስል ድረስ ይጋል፤ በዚህ ዐይነት ርኲሰቱ ይቀልጣል፤ ዝገቱም ይጠፋል። 13ኢየሩሳሌም ሆይ! ሴሰኛነትሽ አርክሶሻል፤ እኔ እንኳ ላነጻሽ ብፈቅድ አንቺ ከርኲሰትሽ አልነጻሽም። የቊጣዬ ኀይል እስከሚገለጥብሽ ድረስ ዳግመኛ ንጹሕ አትሆኚም። 14እኔ ልዑል እግዚአብሔር ‘አንድ ነገር የማደርግበት ጊዜ ቀርቦአል፤ አልገታም፤ አልምርም፤ ሐሳቤን አለውጥም፤ እንደ አካሄድሽና እንደ ሥራሽ እፈርድብሻለሁ’ ” ብዬ ተናግሬአለሁ።
የነቢዩ ሚስት መሞት
15እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረኝ፦ 16“የሰው ልጅ ሆይ! የምትወዳትና የዐይንህ መደሰቻ የሆነችው ሚስትህ ተቀሥፋ በድንገት ትሞትብሃለች፤ በዚህም አትዘን፤ እንባህንም በማፍሰስ አታልቅስ፤ 17በሐዘንም መንሰቅሰቅህን ሰው አይስማህ፤ ለሟችዋ አታልቅስ፤ መጠምጠሚያህንም በራስህ ላይ አድርግ፤ ጫማህንም በእግርህ አጥልቅ፤ አፍህን አትሸፍን፤ የእዝን እንጀራ አትብላ።”
18ጠዋት በማለዳም ከሰዎች ጋር እነጋገር ነበር፤ በዚያች ምሽት ሚስቴ ሞተች፤ በሚቀጥለውም ቀን ልክ እንደ ተነገረኝ አደረግሁ። 19ሰዎችም “ይህን ማድረግህ ከእኛ ጋር ምን ግንኙነት አለው” ሲሉ ጠየቁኝ።
20እኔም እንዲህ ስል መለስኩላቸው፦ “እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረኝ፦ 21‘ጌታ እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን እንዲህ በላቸው አለኝ፤ የክብራችሁ ትምክሕት፥ የዐይናችሁ ተስፋና የልባችሁ ደስታ የሆነውን ቤተ መቅደሴን እንዲያረክሱ እተዋቸዋለሁ፤ በኢየሩሳሌም የቀሩት ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ በጦርነት ይገደላሉ። 22በዚያን ጊዜ እኔ ያደረግኹትን ሁሉ ታደርጋላችሁ፤ አፋችሁን አትሸፍኑም፤ የእዝን እንጀራ አትበሉም፤ 23ጥምጥማችሁን አታወልቁም፤ ጫማችሁን አውልቃችሁ በባዶ እግራችሁ አትሄዱም፤ አታዝኑም ወይም አታለቅሱም፤ ከኃጢአታችሁም የተነሣ ትመነምናላችሁ፤ እርስ በርሳችሁ በመወያየት ትቃትታላችሁ። 24በዚህም ዐይነት ሕዝቅኤል ለእናንተ ምልክት ይሆናል፤ እርሱ እንዳደረገውም ታደርጋላችሁ፤’ ይህ በሚፈጸምበት ጊዜ እኔ ልዑል እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ።”
25እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “አሁንም የሰው ልጅ ሆይ! ዘወትር ሊያዩትና ሊጐበኙት የሚወዱትን፥ የሚመኩበትንና የሚደሰቱበትን እጅግ ጽኑ የሆነውን ቤተ መቅደስ ከእነርሱ እወስድባቸዋለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውንም እወስዳለሁ። 26እኔ ይህን በማደርግበት ቀን ከጥፋት ያመለጠ ሰው መጥቶ ስለዚህ ሁሉ ድርጊት ይነግርሃል። 27በዚያኑ ቀን ከዚህ በፊት አጥተኸው የነበረውን የመናገር ችሎታ መልሰህ ታገኛለህ፤ ከእርሱም ጋር ትነጋገራለህ ለሕዝቡም ምልክት ትሆናለህ፤ እነርሱም እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ