የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሕዝቅኤል 28

28
በጢሮስ ንጉሥ ላይ የተነገረ ትንቢት
1እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረኝ፥ 2“የሰው ልጅ ሆይ! ልዑል እግዚአብሔር ለጢሮስ ንጉሥ እንዲህ ይላል ብለህ ንገረው፦ ‘ልብህ ስለ ታበየ እኔ አምላክ ነኝ በባሕሩ መካከል በአማልክት ዙፋን ላይ እቀመጣለሁ ብለሃል። ምንም እንኳ አንተ በሐሳብህ አምላክ ነኝ ብትል ሰው ነህ እንጂ አምላክ አይደለህም። 3ከዳንኤል ይበልጥ ጥበበኛ የሆንክ ይመስልሃል፤ ምንም ምሥጢር እንደማይሰወርብህም ታስባለህ፤ 4በእርግጥ በጥበብህና በብልኀትህ ብዙ ሀብት አግኝተሃል፤ በግምጃ ቤትህም ብዙ ወርቅና ብር አግበስብሰሃል። 5በንግድ ሥራም ባሳየኸው ታላቅ ብልኀት ብዙ ሀብት አግኝተሃል፤ ከሀብትህም ብዛት የተነሣ ኲራት ተሰምቶሃል።’
6“እንግዲህ እኔ ልዑል እግዚአብሔር የምለው ይህ ነው፤ ‘እንደ አምላክ ጥበበኛ ነኝ ብለህ በማሰብህ ምክንያት፥ 7በአንተ ላይ አደጋ የሚጥሉ ጨካኞች ጠላቶችን አመጣብሃለሁ፤ እነርሱ በጥበብህና በብልኀትህ ያገኘኸውንና ያከማቸኸውን ያማረ ነገር ሁሉ ያጠፋሉ። 8አንተን ወደ ጥልቁ ጒድጓድ ይጥሉሃል፤ በባሕሩም መካከል አሠቃቂ የሆነ ሞት ትሞታለህ። 9ታዲያ ሊገድሉህ በሚመጡበት ጊዜ አሁንም ራስህን እንደ አምላክ ትቈጥር ይሆን? በገዳዮችህ እጅ ወድቀህ ስትገኝ ሰው እንጂ አምላክ ያለመሆንህ ይታወቃል። 10በውጪ አገር ሰዎች እጅ በእግዚአብሔር የማያምኑ ሰዎችን ሞት ትሞታለህ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።’ ”
የጢሮስ ንጉሥ አወዳደቅ
11እግዚአብሔር እንዲህ ሲል እንደገና ተናገረኝ፦ 12“የሰው ልጅ ሆይ! የጢሮስ ንጉሥ ስለሚገጥመው መጥፎ ዕድል ሙሾ አውጣ፤ እኔ ልዑል እግዚአብሔር የምለውንም እንዲህ ብለህ ንገረው፦ ‘በጥበብ የተሞላህና እጅግ መልከ ቀና በመሆንህ የፍጹምነት ምሳሌ ነበርክ። 13የእግዚአብሔር የአትክልት ቦታ በሆነችው በዔደን ውስጥ ትኖር ነበር፤ ሰርድዮን፥ ዐልማዝ፥ ቢረሌ፥ መረግድ፥ ኢያሰጲድ፥ ሰንፔርና በሉር ተብለው በሚጠሩ የከበሩ ድንጋዮች ያጌጠ የወርቅ ልብስ ትለብስ ነበር፤ ከተፈጠርክበት ጊዜ አንሥቶ ይህ ሁሉ ነበረህ። 14አንተን እንደ ጠባቂ ኪሩብ አድርጌ በመሾም በዚያ መደብኩህ፤ በተቀደሰው ተራራዬ ላይ ትኖር ነበር፤ እጅግ በሚያብረቀርቁ የከበሩ ድንጋዮች መካከል ትመላለስ ነበር። 15ከተፈጠርክበት ጊዜ አንሥቶ ክፋት ማድረግ እስከ ጀመርክበት ጊዜ ድረስ አካሄድህ ፍጹም ነበር፤ 16በመግዛትና በመሸጥ ተግባር ትጣደፍ ነበር፤ ይህም ሁሉ ወደ ግፍ ሥራና ወደ ኃጢአት መራህ፤ በዚህም ምክንያት የተቀደሰውን ተራራዬን ለቀህ እንድትወጣ አስገደድኩህ፤ ከነዚያ ከሚያብረቀርቁ የከበሩ ድንጋዮች መካከል ጠባቂው ኪሩብ እያባረረ አስወጣህ። 17መልከ ቀና በመሆንህ እጅግ ታብየህ ነበር፤ ክብር በመፈለግህም ጥበብን አቃለልክ፤ ከዚህም የተነሣ አምዘግዝጌ ወደ መሬት ጣልኩህ፤ ለሌሎች ነገሥታትም የመቀጣጫ ምልክት አደረግሁህ። 18በመግዛትና በመሸጥ ከፈጸምከው በደል የተነሣ የአምልኮ ስፍራዎችህ ሁሉ ረከሱ፤ ስለዚህ በከተማይቱ የሰደድ እሳት እንዲነሣ አድርጌ በሙሉ አቃጠልኳት፤ አሁን ወደ አንተ የሚመለከቱ ሁሉ ዐመድ ብቻ መሆንክን ያያሉ፤ 19እነሆ ጠፋህ! ለዘለዓለምም አትገኝም፤ ያውቁህ የነበሩ አገሮች ሁሉ ተሸብረዋል፤ በአንተ ላይ የደረሰው መጥፎ ዕድል እንዳይገጥማቸውም ፈርተዋል።’ ”
በሲዶና ላይ የተነገረ ትንቢት
20እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ #ኢዩ. 3፥4-8፤ ዘካ. 9፥1-2፤ ማቴ. 11፥21-22፤ ሉቃ. 10፥13-14። 21“የሰው ልጅ ሆይ! ፊትህን ወደ ሲዶና መልሰህ በእርስዋ ላይ ትንቢት ተናገር፤ 22ለሕዝብዋም ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል በላቸው፦ እኔ በእናንተ ላይ ተነሥቼአለሁ፤ በእናንተ ላይ በማደርገው ድርጊት ሕዝቦች ያመሰግኑኛል፤ ፍርዴን ተግባራዊ በማደርግበትና ቅድስናዬን በምገልጥበት ጊዜ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ። 23መቅሠፍቴን በእናንተ ላይ አመጣለሁ፤ በየመንገዱም ደም እንዲፈስስ አደርጋለሁ፤ በየአቅጣጫው በሚነሣባችሁ ጦርነት ምክንያት በመካከላችሁ ሰዎች ይገደላሉ፤ ሕዝቦችም እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ።”
የእስራኤል መባረክ
24እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በንቀት ከሚመለከትዋት፥ በዙሪያዋ ካሉ አገሮች ሁሉ እንደ እሾኽና አሜከላ በመሆን እስራኤልን የሚጐዳ ከእንግዲህ ወዲህ ማንም አይኖርም። እኔም ልዑል እግዚአብሔር እንደ ሆንኩ ያውቃሉ።”
25ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እስራኤላውያን ከተበታተኑበት ከተለያዩ አሕዛብ መካከል በምሰበሰብበት ጊዜና ሌሎች ሕዝቦች እያዩ ቅድስናዬን በሕዝቤ መካከል በምገልጥበት ጊዜ ተመልሰው ለአገልጋዬ ለያዕቆብ በሰጠሁት በገዛ ምድራቸው ይኖራሉ። 26እዚያ ያለ ስጋት ይኖራሉ፤ ቤቶችን ይሠራሉ፤ ወይንም ይተክላሉ፤ በንቀት ይመለከቱአቸው የነበሩትን ጐረቤቶቻቸውን ሁሉ እቀጣለሁ፤ እስራኤላውያን ግን ያለ ስጋት በመተማመን ይኖራሉ፤ በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው እንደ ሆንኩ ያውቃሉ።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ