ትንቢተ ሕዝቅኤል 29
29
በግብጽ ላይ የተነገረ ትንቢት
1በተሰደድን በዐሥረኛው ዓመት፥ በዐሥረኛው ወር፥ ከወሩም በዐሥራ ሁለተኛው ቀን እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረኝ፤ #ኢሳ. 19፥1-25፤ ኤር. 46፥2-26። 2“የሰው ልጅ ሆይ! ፊትህን በግብጽ ንጉሥ ላይ መልሰህ በእርሱና በግብጽ ሕዝብ ላይ ትንቢት ተናገር። 3ልዑል እግዚአብሔር ለግብጽ ንጉሥ እንዲህ ይላል ብለህ ንገረው፤ በወንዝ ውስጥ የተጋደመ አስፈሪ የባሕር አውሬ የምትመስል አንተ! እነሆ፥ እኔ በቊጣ ተነሥቼብሃለሁ፤ ‘የዓባይ ወንዝ የእኔ ነው፤ ይህን ወንዝ የሠራሁት እኔ ነኝ’ ትላለህ። 4በመንጋጋህ መቃጥን አስገባለሁ፤ በወንዝህ ውስጥ ያሉትንም ዓሣዎች በሰውነትህ ላይ እንዲጣበቁ አደርጋለሁ፤ ዓሣዎቹም በአንተ ላይ እንደ ተጣበቁ ከዓባይ ወንዝ ጐትቼ አወጣሃለሁ። 5አንተንና የወንዞችህን ዓሣዎች ሁሉ ወደ በረሓ እወረውራችኋለሁ፤ ሬሳህም ተነሥቶ ሳይቀበር በመሬት ላይ ወድቆ ይቀራል፤ ለወፎችና ለአራዊትም ምግብ እንዲሆን አደርገዋለሁ። 6እናንተ ለእስራኤላውያን እንደ ሸምበቆ በትር ደካሞች ስለ ሆናችሁ በዚያን ጊዜ እናንተ የግብጽ ሕዝብ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ። #ኢሳ. 36፥6። 7በእጆቻችሁ በያዙአችሁ ጊዜ ተሰነጣጥቃችሁ ትከሻቸውን ወጋችሁ፤ በእናንተ ላይ በተደገፉ ጊዜ እናንተ ተሰብራችሁ ወገባቸው ተብረከረከ። 8እንግዲህ እኔ ልዑል እግዚአብሔር የምነግርህ ይህ ነው፥ ‘በሰይፍ አደጋ የሚጥሉብህን ሰዎች አመጣለሁ፤ እነርሱ ሕዝብህንና እንስሶችህን ሁሉ ይፈጃሉ፤ 9ግብጽም ባዶዋን ምድረ በዳ ሆና ትቀራለች። በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንኩ ያውቃሉ።
“ ‘አንተ የዓባይ ወንዝ የእኔ ነው፤ ይህን ወንዝ የሠራሁት እኔ ነኝ’ ብለሃልና። 10እኔ በአንተና በወንዝህ ላይ በቊጣ ተነሥቻለሁ፤ በሰሜን ከሚግዶል ከተማ አንሥቼ በደቡብ እስከ አስዋን ከተማ ድረስ፥ እንዲያውም እስከ ኢትዮጵያ ጠረፍ ድረስ ግብጽን በሙሉ ምድረ በዳ አድርጌ ባዶዋን አስቀራታለሁ። 11ሰውም ሆነ እንስሳ በዚያች ዝር አይልም፤ እስከ አርባ ዓመት ድረስ ምንም ነገር በዚያ አይኖርም፤ 12ግብጽን ባድማ ከሆኑት አገሮች የበለጠ ባድማ እንድትሆን አደርጋታለሁ፤ የግብጽ ከተሞች እስከ አርባ ዓመት ፍርስራሽ ሆነው ይቀራሉ፤ ከተሞችዋም ከፈራረሱ ከተሞች አንድዋ አደርጋታለሁ፤ ግብጻውያንን ስደተኞች አደርጋቸዋለሁ፤ በሌሎች ሕዝቦች መካከልም ተበታትነው እንዲኖሩ አደርጋለሁ።”
13ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ከአርባ ዓመት በኋላ ግብጻውያንን ከበተንኳቸው አገሮች ሁሉ መልሼ አመጣቸዋለሁ፤ 14በቀድሞ መኖሪያቸው በደቡብ ግብጽ በጳጥሮስ እንዲኖሩ እፈቅድላቸዋለሁ፤ በዚያም ደካማ መንግሥት ይሆናሉ፤ 15እንዲያውም ከሁሉ የደከመ መንግሥት ስለሚሆን ዳግመኛ ሌሎች መንግሥታትን የመግዛት ዕድል አይኖረውም፤ ከሁሉ ያነሰ ስለማደርገው ሌላ መንግሥት ማስገበር አይችልም። 16ይልቁንስ እስራኤል ለእርዳታ ወደ ግብጽ በመሄድ የበደለችውን በደል ታስታውስበታለች እንጂ ርዳታ ለማግኘት ዳግመኛ በእነርሱ ላይ አትተማመንም። በዚያን ጊዜ እስራኤላውያን እኔ ልዑል እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ።”
ንጉሥ ናቡከደነፆር ግብጽን ድል እንደሚያደርግ
17በተሰደድን በሃያ ሰባተኛው ዓመት፥ በመጀመሪያው ወር፥ በወሩም በመጀመሪያው ቀን እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረኝ፦ 18“የሰው ልጅ ሆይ! የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በጢሮስ ላይ አደጋ ለመጣል ተነሥቶአል፤ ራሳቸው እስኪመለጥና ትከሻቸው እስኪቈስል ወታደሮቹን ከባድ ሸክም እንዲሸከሙ አድርጎአቸዋል፤ ይሁን እንጂ ንጉሡም ሆነ ሠራዊቱ በዚህ ሁሉ ድካማቸው ምንም ያተረፉት ነገር የለም። 19ስለዚህ እኔ ልዑል እግዚአብሔር የምለው ይህ ነው፦ ‘የግብጽን ምድር ለንጉሥ ናቡከደነፆር አሳልፌ እሰጠዋለሁ፤ እርሱም ለሠራዊቱ እንደ ደመወዝ ይሆንለት ዘንድ በዘረፋና በብዝበዛ የሚያገኘውን ሀብት ሁሉ ይዞ ይሄዳል። 20የእርሱ ሠራዊት እኔን ስላገለገለ ግብጽን የድካሙ ዋጋ አድርጌ እሰጠዋለሁ። እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።’
21“ይህ በሚሆንበት ጊዜ የእስራኤልን ሕዝብ አበረታለሁ፤ አንተም ሕዝቅኤል ሆይ! ሰዎች ሊያደምጡህ በሚችሉበት ቦታ ሁሉ ድምፅህን ከፍ አድርገህ እንድትናገር አደርግሃለሁ፤ በዚህም ሁኔታ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 29: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997