የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሕዝቅኤል 30

30
በግብጽ ላይ ስለሚደርስ ችግር
1እግዚአብሔር እንደገና እንዲህ ሲል ተናገረኝ፦ 2“የሰው ልጅ ሆይ! እኔ እግዚአብሔር የምገልጥልህን ሁሉ በማስታወቅ ይህን ትንቢት ተናገር፤
‘ወዮ! ለዚያች ቀን’ ብለህ አልቅስላት።
3የደመና ቀን ቀርቦአል፤
ይህም የእግዚአብሔር የፍርድ ቀን ነው!
እርሱም ለሕዝቦች የመከራ ቀን ይሆናል።
4በግብጽ ጦርነት ይሆናል፤
በኢትዮጵያም አስጨናቂ ሁከት ይደርሳል፤
ብዙዎች በግብጽ ምድር ይገደላሉ፤
አገሪቱም ተመዝብራ መሠረቶችዋ ይናጋሉ።
5“ያም ጦርነት ከኢትዮጵያ፥ ከሊብያ፥ ከልድያ፥ ከሊቢያ፥ ከዐረብ አገር፥ በቃል ኪዳን የእኔ ወገኖች ከሆኑት ሕዝብ መካከል እንኳ ተቀጥረው የመጡትን ሁሉ የሚፈጅ ይሆናል።”
6እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ከሚግዶል ጀምሮ እስከ አስዋን ድረስ የግብጽ ደጋፊዎች በጦርነት ያልቃሉ፤ የግብጽም ዕብሪተኛ ኀይል ይዋረዳል። እኔ ልዑል እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ። 7ምድሪቱ ባድማ ከሆኑ አገሮች የበለጠ ባድማ ትሆናለች፤ ከተሞችዋም ሁሉ ፍርስራሽ ከሆኑት ከተሞች የበለጠ ይፈራርሳሉ። 8ግብጽን የሚያጋይ እሳት በማቀጣጥልበት ጊዜ፥ እንዲሁም የደጋፊዎችዋ ኀይል በተንኰታኰተ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ። 9በዚያን ቀን ‘አንዳች ነገር ይደርስብናል’ ብለው ያልተጠራጠሩትን ኢትዮጵያውያንን ለማስፈራራት መልእክተኞች በእኔ ትእዛዝ ይወጣሉ፤ እነርሱም በግብጽ ላይ በእርግጥ በሚመጣው ጥፋት ምክንያት ይጨነቃሉ።”
10ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የግብጽን ብዙ ሕዝብ ያወድም ዘንድ የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን እልከዋለሁ። 11እርሱም ምሕረት የሌለውን ጨካኝ ሠራዊቱን አስከትሎ ምድሪቱን ለመደምሰስ ይመጣል። እነርሱም ግብጽን በሰይፍ ይመታሉ። አገሪቱም በሬሳ የተሞላች ትሆናለች። 12የዓባይን ወንዝ ውሃ አደርቃለሁ፤ ግብጽም በክፉ ሰዎች ሥልጣን ሥር እንድትወድቅ አደርጋለሁ። ስለዚህም ባዕዳን ሕዝብ አገሪቱን በሞላ ያጠፋሉ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”
13ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በሜምፊስ ያሉትን ጣዖቶችና የሐሰት አማልክት ሁሉ አወድማለሁ፤ በግብጽ ምድር ላይ ገዢ ሆኖ የሚነሣ አይኖርም፤ በሕዝቡም ላይ ፍርሀትን አወርዳለሁ። 14በደቡባዊ ግብጽ ጳጥሮስ የተባለውን ከተማ ባድማ አደርጋለሁ፤ በሰሜን በኩል በምትገኘው በጾዓን ከተማ ላይም እሳት አቀጣጥላለሁ፤ የቴብስንም ከተማ በፍርድ እቀጣለሁ። 15የግብጽ ዋና ምሽግ የሆነችው የፔሉስየም ከተማ የቊጣዬ መዓት እንዲወርድባት አደርጋለሁ፤ የቴብስን ብዙ ሕዝብ ሁሉ እገድላለሁ። 16በግብጽ ላይ እሳት አነዳለሁ፤ ፔሉስየምም በብርቱ ትጨነቃለች፤ የቴብስ የቅጽር ግንቦች ይፈራርሳሉ፤ በሜምፊስም ከተማ ላይ የማያቋርጥ ሥቃይ ይደርስባታል። 17በኦንና በቡባስቲስ ከተሞች የሚገኙ ወጣቶች ሁሉ በጦርነት ያልቃሉ። የከተሞቹዋ ኗሪዎችም ተማርከው ይወሰዳሉ። 18የግብጽን ኀይል በመሰባበር የሚመኩበትን ብርታት በማስወግድበት ጊዜ ጣፍናስ በጨለማ ትጋረዳለች፤ ግብጽ በደመና ትሸፈናለች፤ የከተሞችዋ ኗሪዎችም ተማርከው ይወሰዳሉ። 19ግብጽን በዚህ ዐይነት በምቀጣበት ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንኩ ያውቃሉ።”
የተሰባበረው የግብጽ ንጉሥ ኀይል
20በተሰደድን በዐሥራ አንደኛው ዓመት የመጀመሪያው ወር በገባ በሰባተኛው ቀን እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረኝ፦ 21“የሰው ልጅ ሆይ! እኔ የግብጽን ንጉሥ ክንድ ሰብሬአለሁ፤ በሸምበቆ ጠግኖ በጨርቅ በመጠቅለል መልሶ የሚያድነው ወጌሻ የለም፤ ስለዚህም ከእንግዲህ ወዲህ ብርታት አግኝቶ ሰይፍ ማንሣት አይችልም። 22ከዚህም የተነሣ እኔ ጌታ እግዚአብሔር የምለው ይህ ነው፤ እነሆ፥ እኔ የግብጽን ንጉሥ በቊጣ ተነሥቼበታለሁ፤ ስለዚህም ሁለት እጆቹን፥ ማለትም ከዚህ በፊት የተሰበረውንና ደኅነኛውን ጭምር ልሰብር ተዘጋጅቻለሁ፤ ሰይፉም ከእጁ እንዲወድቅ አደርጋለሁ። 23ግብጻውያንን በሕዝቦችና በተለያዩ አገሮች መካከል እበትናቸዋለሁ። 24በዚህም ዐይነት የባቢሎንን ንጉሥ ኀይል በማጠንከር የእኔን ሰይፍ በእጁ አስይዘዋለሁ። የግብጽን ንጉሥ ኀይል ግን እሰብራለሁ፤ እርሱም ለሞት የሚያደርስ ቊስል እንደ ደረሰበት ሰው በጠላቱ ፊት ይቃትታል። 25የግብጽን ንጉሥ በማዳከም የባቢሎንን ንጉሥ አበረታለሁ። እኔ ለባቢሎን ንጉሥ የምሰጠውንም ሰይፍ ወደ ግብጽ በሚቃጣበት ጊዜ ሰው ሁሉ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃል። 26ግብጻውያንን በሕዝቦችና በተለያዩ አገሮች መካከል እበትናቸዋለሁ፤ ከዚያም በኋላ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ