የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሕዝቅኤል 33

33
የማስተማር ኀላፊነት
(ሕዝ. 3፥16-21)
1እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረኝ፦ 2“የሰው ልጅ ሆይ! ለሕዝብህ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘በአንድ አገር ላይ ጦርነትን ባመጣ ሕዝቡም በመካከሉ ጠባቂ ቢመድብ፥ 3ጠባቂውም ጠላት ሲመጣ ቢያይና ከአደጋ መጠንቀቅ የሚያስችል የመለከት ድምፅ ለሰዎች ሁሉ ቢያሰማ፥ 4ማንም ሰው ይህን የማስጠንቀቂያ ድምፅ ሰምቶ ባለማጤኑ ምክንያት ጠላት አደጋ ጥሎበት ቢሞት ጥፋቱ የራሱ ነው፤ 5ማስጠንቀቂያውን ባለማጤኑ ለሞት ያበቃው የራሱ ስሕተት ነው፤ ማስጠንቀቂያውን ቢያጤንማ ኖሮ ከጥፋት ባመለጠ ነበር፤ 6ነገር ግን ጠባቂው ጠላት ሲመጣ እያየ ከአደጋ ማስጠንቀቂያውን ድምፅ ሳያሰማ ቢቀር፥ ጠላት መጥቶ ከእነዚያ መካከል አንዱን ቢገድል ያ ሰው የሞተው በኀጢአቱ ነው፤ እኔ ግን ስለ እርሱ ለደሙ ኀላፊ አድርጌ የምጠይቀው ጠባቂውን ነው።’
7“አሁንም የሰው ልጅ ሆይ! እነሆ፥ እኔ አንተን ለእስራኤል ሕዝብ ጠባቂ አድርጌሃለሁ፤ እኔ የምሰጥህን ማስጠንቀቂያ ሁሉ ለእነርሱ ማስተላለፍ አለብህ፤ 8ኃጢአተኛውን ሰው ‘ኃጢአተኛ ሆይ! በእርግጥ ትሞታለህ’ በምለው ጊዜ አንተ ከክፉ ሥራው እንዲመለስ ባታስጠነቅቀው፥ ያ ሰው ኃጢአተኛ እንደ ሆነ በኃጢአቱ ይሞታል፤ ስለ እርሱም ሞት አንተን ራስህን በኀላፊነት ተጠያቂ አደርግሃለሁ። 9ኃጢአተኛውን ሰው ከክፉ ሥራው እንዲመለስ ካስጠነቀቅኸው በኋላ፥ ከክፉ ሥራው ሳይመለስ በኃጢአቱ ጸንቶ ቢሞት ግን፥ አንተ ራስህን ከኀላፊነት ነጻ ታደርጋለህ።”
ሰው ሁልጊዜ በንስሓ መኖር እንደሚገባው
10የሰው ልጅ ሆይ! ለእስራኤላውያን እንዲህ በላቸው፦ “እናንተ በደላችንና ኃጢአታችን ከብደውናል፤ በእነርሱም ምክንያት እየመነመንን ነው፥ ታዲያ እንዴት መኖር እንችላለን ብላችኋል። 11እኔ ልዑል እግዚአብሔር ሕያው እንደ መሆኔ ኃጢአተኛ ሰው፥ ኃጢአት መሥራቱን ትቶ በሕይወት እንዲኖር እንጂ በኃጢአቱ እንዲሞት አልፈቅድም፤ ስለዚህ እስራኤል ሆይ! ክፉ ሥራችሁን ተዉ፤ መሞትን ለምን ትፈልጋላችሁ? ብለህ ንገራቸው።
12“አሁንም የሰው ልጅ ሆይ! ጻድቅ የነበረ ሰው ኃጢአት መሥራትን ቢጀምር፥ ቀድሞ የፈጸመው መልካም ሥራ አያድነውም፤ ክፉ ሰውም ክፉ መሥራቱን ካቆመ የቀድሞ ክፉ ሥራው እንቅፋት አይሆንበትም፤ ጻድቅ ሰውም ኃጢአት መሥራት ቢጀምር፥ የቀድሞ ጽድቁ ከሞት ሊያድነው አይችልም። 13ጻድቅ ሰው በእርግጥ በሕይወት ትኖራለህ ብለውም እርሱ ግን ‘የቀድሞ የጽድቅ ሥራዬ ይበቃኛል’ ብሎ ኃጢአት መሥራት ቢጀምር፥ ከቀድሞ መልካም ሥራው አንዱንም እንኳ አላስታውስለትም፤ ስለዚህም በኃጢአቱ ምክንያት ይሞታል። 14አንድን ክፉ ሰው በእርግጥ እንደሚሞት ባስታውቀውና እርሱ ግን ኃጢአት መሥራቱን ትቶ ሕጋዊና ትክክለኛ የሆነውን ነገር ቢያደርግ፥ 15ይህም ማለት፥ ስለ ብድር በመያዣ ስም የያዘውን ወይም የሰረቀውን ንብረት ቢመልስ፥ ኃጢአት መሥራትን ትቶ ሕይወትን የሚሰጡ ሕጎችን ቢጠብቅ፥ በእርግጥ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም፤ 16የሠራውን ኃጢአት ሁሉ ይቅር እልለታለሁ፤ እውነተኛና ትክክለኛ የሆነውን ሥራ በመሥራቱ በእርግጥ በሕይወት ይኖራል።
17“የአንተ ሕዝብ ግን እኔ የማደርገው ነገር ትክክል አይደለም ይላሉ፤ ይልቅስ ትክክል ያልሆነው የእነርሱ መንገድ ነው። 18ጻድቅ ሰው የጽድቅ ሥራውን ትቶ ክፉ መሥራትን ቢጀምር፥ ስለ ክፉ ሥራው ይሞታል፤ 19ክፉም ሰው ኃጢአት መሥራትን ትቶ እውነተኛና ትክክለኛ የሆነውን ነገር ቢያደርግ በእርሱ ይኖራል። 20እናንተ እስራኤላውያን ግን እኔ እግዚአብሔር የማደርገው ሁሉ ትክክል አይደለም ትላላችሁ፤ ሆኖም እያንዳንዳችሁን እንደየአካሄዳችሁ እፈርድባችኋለሁ።”
የኢየሩሳሌምን መውደቅ የሚገልጥ ዜና
21በተሰደድን በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት፥ ዐሥረኛው ወር በገባ በአምስተኛው ቀን ከኢየሩሳሌም አምልጦ የመጣ አንድ ሰው ከተማይቱ በጠላት እጅ መውደቋን ነገረኝ። #2ነገ. 25፥3-10፤ ኤር. 39፥2-8፤ 52፥4-14። 22አምልጦ የመጣው ሰው እኔ ዘንድ ከመድረሱ ከአንድ ቀን በፊት በምሽቱ የእግዚአብሔር ኀይል ወደ እኔ መጣ፤ በማግስቱ ጠዋት ሰውዬው ወደ እኔ ከመምጣቱ በፊት እግዚአብሔር አንደበቴን ከፈተልኝ፤ ስለዚህ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መናገር አልተሳነኝም።
የእስራኤል ሕዝብ በደል
23እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረኝ፦ 24“የሰው ልጅ ሆይ! በእስራኤል ምድር በፈራረሱ ከተሞች የሚኖሩ ሕዝብ እንዲህ ይላሉ፦ ‘አብርሃም ብቸኛ የሆነ አንድ ሰው ነበረ፤ ምድሪቱ በሞላ ለእርሱ ተሰጠች፤ እኛ ግን እነሆ፥ ብዙዎች ነን፤ ምድሪቱም በእርግጥ በርስትነት ተሰጥታናለች።’
25“እኔ ልዑል እግዚአብሔር ስለ እነርሱ የምለውን እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘ሥጋ ከነደሙ ትበላላችሁ፤ ጣዖት ታመልካላችሁ፤ ግድያ ትፈጽማላችሁ፤ ታዲያ፥ ይህን ሁሉ እያደረጋችሁ እንዴት ምድሪቱ የእኛ ርስት ናት ትላላችሁ? 26በሰይፋችሁ ትተማመናላችሁ፤ አጸያፊ ነገር ትፈጽማላችሁ፤ እያንዳንዱ ሰው ከሌላ ሰው ሚስት ጋር ዝሙት ይፈጽማል፤ ታዲያ፥ ምድሪቱ እንዴት የእኛ ርስት ናት ትላላችሁ?’
27“እንግዲህ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ሕያው እንደ መሆኔ በፈራረሱ ከተሞች የሚኖሩ ሕዝብ ሁሉ በእርግጥ ይገደላሉ ብዬ ያስጠነቀቅኋቸው መሆኑን ገልጠህ ንገራቸው፤ በገጠር የሚኖሩ የአራዊት ምግብ ይሆናሉ፤ በየተራራውና በየዋሻው ተደብቀው ያሉትም በመቅሠፍት ያልቃሉ፤ 28ምድሪቱንም ባድማና ወና አደርጋታለሁ፤ ዕብሪተኛ ኀይልዋም ያበቃል፤ የእስራኤል ተራራዎች ማንም በዚያ በኩል የማያልፍባቸው ባዶ ይሆናሉ። 29እነርሱ በፈጸሙአቸው አጸያፊ ነገሮች ሁሉ ምክንያት ምድሪቱን ባድማና ወና በማደርግበት ጊዜ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ።”
የነቢዩ መልእክት ያስገኘው ውጤት
30እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! ሕዝቡ በከተማይቱ ቅጽር አጠገብና በየቤታቸው ደጃፍ የሚወያዩት ስለ አንተ ነው፤ እርስ በርሳቸውም ‘ኑና ከእግዚአብሔር ምን ቃል እንደ መጣ ሲነገር እንስማ’ ይላሉ። 31ስለዚህም ሌሎች ሕዝቦች እንደሚያደርጉት ሕዝቤ አንተ ምን እንደምትናገር ለማዳመጥ ብቻ ይሰበሰባሉ፤ ነገር ግን የምትነግራቸውን ሁሉ አይፈጽሙም፤ የምትናገረውን ቃል የሚወዱት መስለው ይታያሉ፤ ነገር ግን ከበዝባዥነታቸው አይመለሱም፤ 32አንተ በእነርሱ ዘንድ ጥሩ ድምፅ እንዳለውና ደኅና አድርጎ የሙዚቃ መሣሪያን እንደሚጫወት እንደ ፍቅር ዘፈን አቀንቃኝ ነህ፤ አንተ የምትለውን ይሰማሉ እንጂ፤ አይፈጽሙትም። 33ነገር ግን አንተ የተናገርካቸው ቃላት በእርግጥ ይፈጽማሉ፤ እውን ሆነው በሚፈጸሙበትም ጊዜ በመካከላቸው ነቢይ መኖሩን ያውቃሉ።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ