የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሕዝቅኤል 36

36
እግዚአብሔር እስራኤልን መባረኩ
1እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! ለእስራኤል ተራራዎች ትንቢት ተናገር፤ እኔ ጌታ እግዚአብሔር ስለ እነርሱ የምለውን ያዳምጡ ዘንድ ንገራቸው፤ 2ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የእስራኤል ጠላቶች ‘እነሆ፥ እነዚያ የጥንት ተራራዎች የእኛ ሆነዋል!’ በማለት መጓደድ ጀምረዋል።
3“ስለዚህ ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ብለህ ለእስራኤል ተራራዎች ትንቢት ተናገር አለኝ፦ የባዕድ አገር ሕዝቦች በሁሉም አቅጣጫ ምድራችሁን ስላፈራረሱትና በእርግጥም ባድማ ስላደረጉት አገራችሁ ለሌሎች ሕዝቦች ንብረት ሆነ። እናንተም የሰዎች መሳቂያና መሳለቂያ ሆናችኋል። 4ስለዚህ እናንተ የእስራኤል ተራራዎች የልዑል እግዚአብሔርን ቃል አድምጡ፦ ለተራሮችና ለኰረብቶች፥ ለወራጅ ውሃዎችና ለሸለቆዎች፥ ባድማና ወና ሆነው ለተለቀቁትና በአካባቢው ላሉ ሕዝቦች ሁሉ የዘረፋ ምንጮችና የመሳለቂያ ርእስ ለሆኑት ከተሞች ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
5“በኀይለኛ ቅናቴ በሌሎች ሕዝቦች ላይና በመላዋ ኤዶም ላይ እናገራለሁ፤ እነርሱ ደስታን በተመላ ስሜትና በፍጹም ንቀት መሰማሪያዋን ለመውረር ምድሬን ርስታቸው አደረጉት፤ ይላል ልዑል እግዚአብሔር።
6“ስለ እስራኤል ምድር ትንቢት ተናገር፥ ለሕዝቡም እንዲህ በላቸው፦ በተራሮቻችሁ፥ በኰረብቶቻችሁ፥ በወራጅ ውሃዎቻችሁና በሸለቆዎቻችሁ ላይ ሕዝቦች ባደረሱት ውርደት ምክንያት እኔ በኀይለኛ የቊጣ ቅናቴ እናገራለሁ ይላል ልዑል እግዚአብሔር። 7በእናንተ ዙሪያ የሚገኙ የጐረቤት አገሮች ሁሉ እንደሚዋረዱ፥ እኔ ልዑል እግዚአብሔር በፍጹም እምላለሁ። 8ስለ እናንተ ስለ ሕዝቤ እስራኤል ግን የምለው ይህ ነው፤ በእስራኤል ተራራዎች ላይ የሚገኙ ዛፎች ሁሉ እንደገና ይለመልማሉ፤ ፍሬም ይሰጡአችኋል፤ እናንተም በፍጥነት ወደ አገራችሁ ትመለሳላችሁ። 9እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ፤ ምሕረት አደርግላችኋለሁ፤ ምድራችሁ ታርሳ ዘር ይዘራባታል። 10እናንተንም አበዛችኋለሁ፤ ፍርስራሽ ሆኖ የኖረውንም ስፍራ ሁሉ በመገንባት በከተሞች ትኖራላችሁ። 11ሕዝብም ሆነ እንስሳ በቊጥር እንዲበዛ አደርጋለሁ፤ ብዙ ልጆች ወልዳችሁ በቊጥር ትበዛላችሁ፤ እዚያም ጥንት በኖራችሁበት ሁኔታ ትኖራላችሁ፤ ከምንጊዜውም ይልቅ አበለጽጋችኋለሁ፤ በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንኩ ታውቃላችሁ። 12ሕዝቤ እስራኤል ሆይ! እንደገና በምድሪቱ መኖር ትችሉ ዘንድ መልሼ አመጣችኋለሁ፤ ምድሪቱም እንደገና ተመልሳ የራሳችሁ ትሆናለች፤ ዳግመኛም ልጆች አልባ አትሆንም።
13“እኔ ልዑል እግዚአብሔር የምለው ይህ ነው፤ ሕዝቡ ይህችን ምድር ‘ሰው በላ’ ብለው የሚጠሩአትና ሕዝብዋንም ‘ልጆች አልባ’ አድርጋለች የሚሉት ነገር እውነት ነው። 14ከእንግዲህ ወዲህ ግን ምድሪቱ ‘ሰው በላ’ አትሆንም፤ ልጆቻችሁንም አትነጥቅም፤ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ። 15ምድሪቱ ከእንግዲህ ወዲህ የሕዝቦች ማላገጫ አትሆንም፤ በንቀትም አይመለከቱአትም፤ ምድሪቱንም ዳግመኛ ልጅ አልባ የሚያደርጋት አይኖርም። እኔ ጌታ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”
የእስራኤል አዲስ ሕይወት
16እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረኝ፤ 17“የሰው ልጅ ሆይ! የእስራኤል ሕዝብ በዚህች አገር ሲኖሩ በከንቱ አኗኗራቸውና በመጥፎ ሥራቸው ሁሉ ምድሪቱን አርክሰዋት ነበር፤ በፊቴም የነበራቸው አካሄድ፥ ሴት በወር አበባዋ ወቅት እንደ ርኩስ ሆና የምትታይበትን ያኽል ነበር። 18በሀገሪቱ ላይ ስለ ፈጸሙት ግድያና በጣዖት አምልኮም ምድሪቱን በማርከሳቸው ምክንያት ኀይለኛ ቊጣዬን አወረድኩባቸው። 19አኗኗራቸውና ሥራቸው ሁሉ መጥፎ ስለ ነበረ ፈረድኩባቸው፤ በባዕዳን አገሮችም እንዲበተኑ አደረግሁ። 20እነዚህ የእግዚአብሔር ሕዝብ ቢሆኑም እንኳ እርሱ ከሰጣቸው ምድር ወጥተዋል” ብለው የተበታተኑባቸው አገሮች ሕዝቦች ስለሚናገሩ ሕዝቤ ቅዱስ ስሜን አሰድበዋል። 21ነገር ግን የእስራኤል ሕዝብ በሄዱባቸው ሕዝቦች መካከል ቅዱስ ስሜን ማሰደባቸው ያሳስበኛል።
22“እንግዲህ እነሆ፥ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ስለ እነርሱ የምልህን ሁሉ ንገራቸው፤ ከእንግዲህ ወዲህ የማደርግላችሁ ነገር በሄዳችሁበት ስፍራ ሁሉ ስላሰደባችሁት ስለ ቅዱስ ስሜ እንጂ ስለ እናንተ ስለ እስራኤላውያን ብዬ አይደለም። 23በሕዝቦች መካከል ተሰድቦ የነበረውን፥ ማለት እናንተ አሰደባችሁት የነበረውን የታላቁን ስሜን ቅድስና አሳያለሁ፤ ከዚያ በኋላ በእናንተ አማካይነት በእነርሱ ፊት ቅድስናዬን በምገልጥበት ጊዜ ሕዝቦች እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ። 24ከመንግሥቶች ከአገሮች ሁሉ አውጥቼ በመሰብሰብ ወደ ገዛ ምድራችሁ እመልሳችኋለሁ። 25በእናንተ ላይ ንጹሕ ውሃ በመርጨት ከጣዖት አምልኮአችሁና ከርኲሰታችሁ ሁሉ እንድትነጹ አደርጋለሁ። 26አዲስ ልብ እሰጣችኋለሁ፤ አዲስ መንፈስንም በውስጣችሁ አኖራለሁ፤ ከሰውነታችሁ እንደ ድንጋይ የጠጠረ ልብን አውጥቼ እንደ ሥጋ የለሰለሰ ልብን እሰጣችኋለሁ። #ሕዝ. 11፥19-20። 27መንፈሴን አሳድርባችኋለሁ፤ የሰጠኋችሁንም ሕግና ሥርዓት ሁሉ በጥንቃቄ መፈጸም እንድትችሉ አደርጋችኋለሁ። 28ከዚያም በኋላ ለቀድሞ አባቶቻችሁ በሰጠኋት ምድር ትኖራላችሁ፤ እናንተ ሕዝቤ ትሆናላችሁ፤ እኔም አምላካችሁ እሆናለሁ። 29ከርኲሰታችሁ ነገር ሁሉ አድናችኋለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ራብ እንዳይደርስባችሁ እህል እንዲበዛላችሁ አዛለሁ። 30የዛፋችሁና የእርሻችሁ ፍሬ ሁሉ እንዲበዛ አደርጋለሁ፤ ከዚያም በኋላ እናንተን በአሕዛብ መካከል የሚያዋርድ ራብ አይደርስባችሁም። 31መጥፎ ጠባያችሁንና ትፈጽሙት የነበረውንም ክፉ ሥራ ሁሉ ታስታውሳላችሁ፤ በኃጢአታችሁና ትፈጽሙት በነበረው የረከሰ ሥራ ምክንያት ራሳችሁን ትጸየፋላችሁ። 32እኔ የማደርገውን ነገር ሁሉ ለእናንተ ብዬ የማላደርግ መሆኔ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፤ ስለዚህ እስራኤል ሆይ! በአካሄዳችሁ ኀፍረትና ውርደት ይሰማችሁ።” ይህን የተናገረ ልዑል እግዚአብሔር ነው።
33ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እኔ ከኃጢአታችሁ ሁሉ በማነጻችሁ ጊዜ የፈራረሱትን ሁሉ በመገንባት እንደገና በከተሞቻችሁ እንድትኖሩ አደርጋለሁ። 34በእርሻዎቻችሁ በኩል በሚያልፉ ሰዎች ሁሉ ዘንድ ባድማ ሆና ትቈጠር የነበረችው ምድር ትታረሳለች። 35ተመልካችም ሁሉ ‘ጭራሽ ምድረ በዳ ሆና የነበረች ይህች ምድር እንዴት የዔደንን ገነት መሰለች! ቀድሞ ባድማ ወናና የፍርስራሽ ክምር ሆነው የነበሩትስ ከተሞች እንዴት እንደገና ሕዝብ ሊኖርባቸውና የተመሸጉ ሊሆኑ ቻሉ?’ ይላሉ። 36በዚያን ጊዜ ከጥፋት የተረፉት የጐረቤት አገሮች ሕዝብ ሁሉ የፈረሱ ከተሞችን መልሼ የሠራሁና ባድማ የሆነውን ቦታ ያለመለምኩ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ሁሉ እንደምፈጽም ተናግሬአለሁ፤ ደግሞም እፈጽመዋለሁ።”
37ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “እስራኤላውያን ደግመው አንድ ጊዜ ይህን እንዲለምኑኝ አደርጋለሁ፤ ቊጥራቸውንም እንደ በጎች መንጋ አበዛዋለሁ። 38ቀድሞ ኢየሩሳሌም በበዓል ቀን ለመሥዋዕት በሚቀርቡ በጎች ትሞላ እንደ ነበረች የፈራረሱት ከተሞች በሕዝብ የተሞሉ ይሆናሉ፤ በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንኩ ያውቃሉ።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ