የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሕዝቅኤል 35

35
በኤዶም ላይ የተነገረ ትንቢት
1እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረኝ፦ 2“የሰው ልጅ ሆይ! ፊትህን ወደ ኤዶም ተራራ መልሰህ በሕዝቡም ላይ ትንቢት ተናገር፤ 3እኔ ልዑል እግዚአብሔር የምለውንም ሁሉ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦
‘የኤዶም ሕዝብ ሆይ!
እነሆ እኔ እናንተን እቃወማለሁ፤
ምድራችሁንም ባድማና ወና ላደርግ በእናንተ ላይ ተነሥቼአለሁ።
4ከተሞቻችሁንም አፈራርሳለሁ፤
ምድራችሁንም ባድማ አደርጋታለሁ፤
ከዚያም በኋላ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንኩ ታውቃላችሁ።
5“ ‘ለብዙ ጊዜ ከቈየው ጥላቻችሁ የተነሣ በኃጢአቱ ምክንያት በደረሰበት የመጨረሻ ቅጣትና በመከራው ጊዜ የእስራኤልን ሕዝብ ለሰይፍ አሳልፋችሁ ሰጣችሁ። 6ስለዚህ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ሕያው እንደ መሆኔ ለግድያ አዘጋጃችኋለሁ፤ ገዳይም ያሳድዳችኋል፤ ደም ማፍሰስን ስላልጠላችሁ ገዳይ ያሳድዳችኋል። 7እኔ የኤዶምን ተራራማ አገር ባድማና ወና አደርጋለሁ፤ በዚያም በኩል ማንም ሰው እንዳያልፍ አደርጋለሁ፤ 8ተራራዎችን ሁሉ በተገደሉ ሰዎች ሬሳ እሸፍናለሁ፤ በጦርነት የተገደለውም ሬሳ ኰረብቶቻችሁና ሸለቆዎቻችሁን ወንዞቻችሁንም ሁሉ ይሸፍናል፤ 9እኔ ለዘለዓለሙ ምድራችሁን ባድማ አደርጋለሁ፤ ዳግመኛም በከተሞቻችሁ የሚኖር አይገኝም፤ በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንኩ ታውቃላችሁ።
10“ ‘እኔ እግዚአብሔር እዚያ ያለሁ ብሆንም እንኳ ሁለቱን ሕዝቦች፥ ማለት ይሁዳንና እስራኤልን፥ እንዲሁም ምድራቸውን ጭምር የእናንተ አድርጋችሁ ለመውረስ አስባችሁ ነበር። 11ስለዚህም እኔ ልዑል እግዚአብሔር ሕያው እንደ መሆኔ በሕዝቤ ላይ ባላችሁ ጥላቻ ምክንያት ያሳያችሁት ቊጣና ምቀኝነት ሁሉ ተገቢውን ቅጣት እሰጣችኋለሁ። እነርሱም እናንተን በምቀጣበት ጊዜ የምቀጣችሁ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን እንዲያውቁ አደርጋለሁ። 12እነርሱ ባድማ የተደረጉ ስለ ሆነ በእኛ ቊጥጥር ሥር እንዲሆኑ ተሰጥተውናል’ ብላችሁ በእስራኤል ተራራዎች ላይ የተናገራችሁትን የንቀት ንግግር እኔ እግዚአብሔር የሰማሁ መሆኔን ወደፊት ታውቃላችሁ። 13በእኔ ላይ መገዳደራችሁንና ያለ ገደብም በእኔ ላይ መናገራችሁን ሰምቼአለሁ።”
14ስለዚህም እኔ ልዑል እግዚአብሔር የምለው ይህ ነው፦ “ዓለም ሁሉ ሲደሰት የእናንተን አገር ግን ባድማ አደርጋታለሁ። 15የእስራኤል ምድር ባድማ በመሆኑ እንደ ተደሰታችሁ እኔም የሴኢርን ተራራና የኤዶምን ግዛት ሁሉ ባድማ አደርጋለሁ፤ ከዚያ በኋላ ሁሉም እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃል።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ