ትንቢተ ሕዝቅኤል 8
8
ለሕዝቅኤል የተገለጠለት ሁለተኛ ራእይ
(8፥1—10፥22)
ባዕድ አምልኮ በኢየሩሳሌም
1በተሰደድን በስድስተኛው ዓመት፥ በስድስተኛው ወር፥ በአምስተኛው ቀን፥ ከይሁዳ የተሰደዱት ሕዝብ መሪዎች በቤቴ ከእኔ ጋር አብረው ተቀምጠው ሳሉ፥ የልዑል እግዚአብሔር ኀይል ድንገት በእኔ ላይ ወረደ። 2ቀና ብዬ ስመለከት መልኩ እንደ እሳት ነበልባል የሚያበራ የሰው አምሳያ አየሁ፤ ያም የሰው አምሳያ ከወገቡ በታች እሳት፥ ከወገቡ በላይ የሚያንጸባርቅ የጋለ ብረት ይመስል ነበር። #ሕዝ. 1፥28። 3እርሱም የሰው እጅ የሚመስል ነገር ወደ እኔ ዘርግቶ የራስ ጠጒሬን ያዘ፤ በዚሁ ራእይ የእግዚአብሔር መንፈስ ከምድር ወደ ሰማይ አነሣኝና ወደ ኢየሩሳሌም አደረሰኝ። በሰሜን በኩል ወደ ውስጠኛው አደባባይ በሚያስገባው ቅጽር በር አሳልፎ የእግዚአብሔርን ቅናት የሚቀሰቅስን የጣዖት ምስል ወዳለበት ስፍራ አደረሰኝ።
4በዚያም የእስራኤል አምላክ ክብር ነበር፤ ይህም በኬባር ወንዝ ያየሁት ዐይነት ራእይ ነበር። 5እግዚአብሔርም፦ “የሰው ልጅ ሆይ! በስተ ሰሜን በኩል ተመልከት!” አለኝ፤ በተመለከትኩም ጊዜ በቅጽር በሩ ፊት ለፊት ባለው መሠዊያ አጠገብ የእግዚአብሔርን ቅናት የሚቀሰቅስ ምስል ነበር።
6እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! የሆነውን ነገር ሁሉ ታያለህን? የእስራኤል ሕዝብ በዚህ ስፍራ የሚፈጽሙትን አጸያፊ ነገር ተመልከት፤ በዚህ አድራጎታቸው ከተቀደሰው ስፍራዬ እንድርቅ አድርገውኛል፤ ከዚህም የበለጠ እጅግ አስነዋሪ የሆነ ነገር ገና ታያለህ።”
7በውጪ በኩል ወዳለው አደባባይ መግቢያ በር ወሰደኝ፤ በቅጽሩ ግንብ ላይ አንድ ቀዳዳ ነበር፤ 8“የሰው ልጅ ሆይ! በዚህ በኩል ግንቡን ሸንቊረው” አለኝ፤ በሸነቈርኩትም ጊዜ አንድ በር አገኘሁ፤ 9እርሱም “ወደ ውስጥ ግባና በዚያ የሚያደርጉትን ክፉና አጸያፊ ነገር ተመልከት!” አለኝ። 10እኔም ወደ ውስጥ ገብቼ ተመለከትኩ፤ በግንቡ ዙሪያ በደረታቸው የሚሳቡ ንጹሕ ያልሆኑ እንስሶችና የእስራኤል ሕዝብ ጣዖቶች ተስሎበት ነበር። 11የሻፋንን ልጅ አዛንያን ጨምሮ ሰባ የእስራኤላውያን መሪዎች በዚያ ነበሩ፤ እያንዳንዱም ጥና ይዞ ነበር፤ ከጥናውም መልካም መዓዛ ያለው የዕጣን ጢስ ይወጣ ነበር፤ 12እርሱም እንዲህ አለኝ፦ “የእስራኤል መሪዎች በየራሳቸው ጣዖት ቤት በጨለማ ሆነው እግዚአብሔር አያየንም! ምድሪቱንም ትቶአታል በማለት የሚያደርጉትን ታያለህን?” አለኝ።
13እርሱም እንደገና “ከዚህም እንኳ የሚበልጥ አጸያፊ ነገር ሲያደርጉ ታያቸዋለህ” አለኝ፤ 14ስለዚህ በስተሰሜን በኩል ወዳለው ወደ ቤተ መቅደሱ ቅጽር በር ወሰደኝ፤ ተሙዝ ለተባለው ጣዖታቸው ሴቶች ሲያለቅሱለት አሳየኝ።
15እርሱም “የሰው ልጅ ሆይ! ይህን ታያለህን? ገና ከዚህ የባሰ አጸያፊ ነገር ታያለህ” አለኝ። 16ስለዚህ በውስጥ በኩል ወዳለው ወደ ቤተ መቅደሱ አደባባይ ወሰደኝ፤ እዚያም ወደ መቅደሱ መግቢያ አጠገብ በመሠዊያውና በመተላለፊያው መካከል ኻያ አምስት ያኽል ሰዎች ነበሩ፤ እነርሱም ጀርባቸውን ወደ መቅደሱ አድርገው የምትወጣዋን ፀሐይ በማምለክ ወደ ምሥራቅ ተንበርክከው ይሰግዱ ነበር።
17ቀጥሎም እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! ይህን ታያለህን? እነዚህ የይሁዳ ሕዝቦች በዚህ ስፍራ ያየኸውን አጸያፊ ነገር ሁሉ በመሥራትና በአገሪቱም ላይ ዐመፅ ማስፋፋቱ አልበቃ ብሎአቸው ወደዚህ ወደ ቤተ መቅደስ እንኳ ሳይቀር በቀጥታ መጥተው ይህን ሁሉ በማድረግ እኔን እንደገና ማስቈጣት ይፈልጋሉ፤ እንዴት እንደሚሰድቡኝና እኔን ለማስቈጣት የተቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ተመልከት! 18ስለዚህ ቊጣዬን አወርድባቸዋለሁ፤ ራርቼም አልተዋቸውም፤ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ወደ እኔ ቢጮኹም አላደምጣቸውም።”
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 8: አማ05
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapistaging.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997