ትንቢተ ሕዝቅኤል 9
9
የኢየሩሳሌም መቀጣት
1ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ድምፁን ከፍ አድርጎ “ከተማይቱን የምትቀጡ እናንተ ወደዚህ ቅረቡ፤ ለማጥፋት የተዘጋጀ የጦር መሣሪያዎቻችሁንም ይዛችሁ ኑ!” ብሎ ሲናገር ሰማሁ። 2ስድስት ሰዎችም የመግደያ መሣሪያዎቻቸውን ይዘው ወደ ሰሜን ከሚመለከተው ከላይኛው በር መጡ፤ ከእነርሱም መካከል በፍታ የለበሰና የጽሕፈት ዕቃ ማኅደር በጐኑ የያዘ አንድ ሰው ነበር። ስድስቱም ሰዎች ገብተው በነሐሱ መሠዊያ አጠገብ ቆሙ።
3ከዚህ በኋላ የእስራኤልን አምላክ ክብር የሚገልጥ ነጸብራቅ ቀድሞ ካረፈበት ከኪሩብ ላይ ተነሥቶ ወደ ቤተ መቅደሱ መግቢያ በር ሄደ፤ እግዚአብሔርም በፍታ የለበሰውንና የጽሕፈት ዕቃ ማኅደር የያዘውን ሰው፥ ጠራው፤ 4“በመላዋ ኢየሩሳሌም ከተማ ተዘዋወር፤ በከተማይቱ ከተፈጸመውም አጸያፊና አሳፋሪ ነገር የተነሣ በመሠቀቅ ባዘኑት ሰዎች ግንባር ላይ ምልክት አድርግባቸው!” አለው። #ራዕ. 7፥3፤ 9፥4፤ 14፥1።
5እንደገናም እግዚአብሔር ሌሎቹን ሰዎች እንዲህ ሲላቸው ሰማሁ፦ “በሉ እናንተም እርሱን ተከትላችሁ በከተማይቱ ውስጥ በመዘዋወር ሁሉን ግደሉ፤ ለማንም በመራራት ምሕረት አታድርጉ። 6ሽማግሌ ሆነ ወጣት ወንዶችና ሴቶች፥ ሕፃናትንና ሴቶችን ሁሉ ግደሉ፤ ነገር ግን በግንባሩ ላይ ምልክት ያለበትን ማንንም አትንኩ፤ ግድያውንም ከዚሁ ከቤተ መቅደሴ ጀምሩ፤” ስለዚህ እዚያ በቤተ መቅደስ ከቆሙት መሪዎች አንሥተው ግድያውን ማካሄድ ጀመሩ።
7እግዚአብሔርም “ሂዱና ቤተ መቅደሱን አርክሱ! አደባባዩንም በሬሳ የተሞላ አድርጉ!” አላቸው፤ እነርሱም ወጥተው በከተማይቱ ውስጥ ያሉትን ሰዎች ገደሉ።
8ግድያውም በሚፈጸምበት ጊዜ እኔ ብቻዬን ቀርቼ ሳለሁ በግንባሬም ወደ መሬት ተደፍቼ በመጮኽ “ልዑል እግዚአብሔር ሆይ! ወዮ! በእስራኤል የተረፉትን ሁሉ እስክትፈጅ ድረስ በኢየሩሳሌም ላይ ይህን ያህል ትቈጣለህን?” አልኩ።
9እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል መልስ ሰጠ፦ “የእስራኤልና የይሁዳ ሕዝብ እጅግ የከፋ ኃጢአት በመሥራት በድለዋል፤ በምድሪቱ ሁሉ ላይ ግድያ ፈጽመዋል፤ ከተማይቱንም በዐመፅ የተሞላች አድርገዋታል፤ ‘እግዚአብሔር አገራችንን ትቶአታል፤ እኛንም አይመለከተንም’ ይላሉ፤ 10ስለዚህ አልራራላቸውም፤ ምሕረትም አላደርግላቸውም፤ እነርሱ በሌሎች ላይ ያደረጉትን ሁሉ በእነርሱ ላይ መልሼ አደርግባቸዋለሁ።”
11ከዚህ በኋላ ያ በፍታ የለበሰውና የጽሕፈት ዕቃ ማኅደር የያዘው ሰው ተመልሶ መጥቶ “ያዘዝከኝን ሁሉ ፈጽሜአለሁ” ብሎ ለእግዚአብሔር ተናገረ።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 9: አማ05
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997