ትንቢተ ኢሳይያስ 22
22
ስለ ኢየሩሳሌም የተነገረ ቃል
1“የራእይ ሸለቆ” ተብሎ ስለሚጠራው ቦታ የተነገረ ቃል ይህ ነው፤ በየቤታችሁ ሰገነት ላይ ሆናችሁ በዓል የምታከብሩት በምን ምክንያት ነው? 2በሁካታና በጩኸት የተሞላሽ አንቺ ከተማ ሆይ! ሰክረው በመንገዶችሽ ላይ የወደቁት ሰዎች በሰይፍ የተገደሉ ወይም በጦርነት የሞቱ አይደሉም። 3መሪዎችሽ በሙሉ አንዲት ፍላጻ ሳይወረውሩ በሽሽት ላይ እንዳሉ ተማረኩ። 4ስለ ሞቱት ሕዝቦቼ በመረረ ሁኔታ አለቅስላቸው ዘንድ ተዉኝ፤ አታጽናኑኝ። 5ይህ በራእይ ሸለቆ የጭንቅ፥ የመረገጥ፥ የሽብር ጊዜ ነው፤ ይህ ሁሉ በእኛ ላይ እንዲፈጸም የፈቀደው የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ነው፤ የከተማችን ቅጽሮች ፈራርሰው ወድቀዋል፤ ርዳታ ለማግኘት የሚደረገውም ጩኸት እስከ ተራራዎች በማስተጋባት ላይ ነው።
6የዔላም አገር ወታደሮች በሠረገላና በፈረስ ተቀምጠው ቀስትና ፍላጻ አንግበው መጡ፤ የቂር ወታደሮች ጋሻቸውን አዘጋጅተዋል። 7የይሁዳ ለምለም ሸለቆዎች በሠረገሎች የተሞሉ ሆነዋል። ፈረሰኞች በኢየሩሳሌም ቅጽር በር ፊት ለፊት ቆመዋል። 8የይሁዳ ምሽጎች ሁሉ ተደምስሰዋል፤ በዚያን ጊዜ በጦር ግምጃ ቤት ውስጥ የተከማቸውን የጦር መሣሪያ ወሰዳችሁ። 9የዳዊት ከተማ ብዙ ፍርስራሾች መብዛታቸውን ተመልክታችኋል፤ ከታችኛውም ኩሬ ውሃ አጠራቀማችሁ። 10በኢየሩሳሌም ያሉትን ቤቶች ሁሉ እየተዘዋወራችሁ ቈጠራችሁ፤ ቅጥሩን ለማደስ አንዳንዶቹን ቤቶች አፈረሳችሁ። 11ከጥንቱ ኲሬ የሚወርደውን ውሃ ለመመለስ በከተማይቱ ውስጥ ግድብ ሠራችሁ፤ ነገር ግን ይህን ሁሉ በመጀመሪያ ዐቅዶ ያደረገው እግዚአብሔር መሆኑ ትዝ አላላችሁም።
12በዚያን ጊዜ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ጠጒራችሁን ተላጭታችሁ፥ ማቅም ለብሳችሁ እንድታዝኑና እንድታለቅሱ ጠርቶአችሁ ነበር፤ 13እናንተ ግን ጥሪውን በመቀበል ፈንታ በዓል አደረጋችሁ፤ የምትበሉትንም በግና በሬ ዐረዳችሁ፤ ወይን ጠጅም ጠጥታችሁ “ነገ እንሞታለን ዛሬ እንብላ እንጠጣ!” አላችሁ። #1ቆሮ. 15፥32።
14የሠራዊት አምላክ እንዲህ ብሎ ነግሮኛል፦ “በሕይወት እስካሉ ድረስ ይህ ክፉ በደል አይሰረይላቸውም፤ እኔ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”
ለሼብና የተሰጠ ማስጠንቀቂያ
15የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር በንጉሡ ቤተ መንግሥት መጋቢ ሆኖ ወደ ተሾመው ወደ ሼብና ሄደህ እንዲህ በለው አለኝ፤ 16“ሼብና ሆይ! በኰረብታ ላይ መቃብርህን፥ በአለቱም መኖሪያህን ድንጋይ ጠርበህ ለመሥራት ማን መብት ሰጠህ? 17‘እኔ ኀያል ሰው ነኝ’ ትል ይሆናል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር አንሥቶ ይወረውርሃል። 18እርሱም ወደምትሞትበትና ሠረገሎችህም ቆመው ወደሚቀሩበት ቦታ እንደ ኳስ ጠቅልሎ ወደ ሰፊው ሜዳ ይወረውርሃል፤ ለጌቶችህም ኀፍረት ትሆናለህ። 19እግዚአብሔር አንተን ከደረጃህ ዝቅ ያደርግሃል፤ ከሥራህም ያባርርሃል።
20“በዚያን ጊዜ አገልጋዬን የሕልቂያን ልጅ ኤልያቄምን አስጠራዋለሁ፤ 21የአንተ የነበረውን የማዕርግ ልብስ አለብሰዋለሁ፤ መታጠቂያህንም እሰጠዋለሁ፤ የአንተ የነበረውንም ሥልጣን ሁሉ ለእርሱ አስረክባለሁ፤ እርሱ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ሕዝቦች እንደ አባት ይሆናል። 22የዳዊትን ቤት የቊልፍ መክፈቻ እሰጠዋለሁ፤ እርሱ የሚከፍተውን መዝጋት፥ የሚዘጋውንም መክፈት የሚችል አይኖርም። #ራዕ. 3፥7። 23እኔ እርሱን ኲላብ ተብሎ እንደሚጠራ እንደ ጠንካራ የዕቃ መስቀያ አደርገዋለሁ፤ ለቤተሰቡ ሁሉ የክብር መገኛ ይሆናል።
24“ነገር ግን ቤተ ዘመዶቹና የሩቅ ዘመዶቹ የሆኑ ሁሉ እንደ ከባድ ሸክም ይሆኑበታል፤ ከሲኒ አንሥቶ እስከ እንስራ ያሉት የቤት ዕቃዎች ሁሉ በኲላብ ላይ እንደሚሰቀሉ እነርሱም በእርሱ ላይ የሚንጠለጠሉ ይሆናሉ። 25በዚያም ቀን የሠራዊት አምላክ እንዲህ ይላል፦ ‘ይህ ሁሉ ነገር በሚፈጸምበት ጊዜ ግን ጠንካራው የዕቃ መስቀያ ኲላብ ተነቅሎ ይወድቃል፤ በኲላቡም ላይ ተሰቅሎ የነበረው ዕቃ ሁሉ ተሰባብሮ ይወድቃል።’ ” ይህን የተናገረ እግዚአብሔር ነው።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 22: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997