የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መሳፍንት 10

10
ቶላዕ
1አቤሜሌክ ከሞተ በኋላ የዶዶ የልጅ ልጅ የፑአ ልጅ ቶላዕ እስራኤልን ለማዳን ተነሣ፤ እርሱም ከይሳኮር ነገድ ሲሆን የሚኖረውም በኮረብታማው በኤፍሬም አገር ሻሚር ተብላ በምትጠራ ስፍራ ነበር፤ 2ይህ ሰው ኻያ ሦስት ዓመት የእስራኤል መሪ ሆኖ ከቆየ በኋላ ሞተ፤ በሻሚርም ተቀበረ።
ያኢር
3ከቶላዕ ቀጥሎ ገለዓዳዊው ያኢር ተነሣ፤ እርሱም ኻያ ሁለት ዓመት የእስራኤል መሪ ሆነ፤ 4በሠላሳ አህዮች ላይ ተቀምጠው የሚጋልቡ ሠላሳ ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም በገለዓድ ምድር ሠላሳ ከተሞች ነበሩአቸው፤ እነዚህም ከተሞች እስከ ዛሬ የያኢር መንደሮች ተብለው ይጠራሉ፤ 5ያኢር ሞተ፤ በቃሞንም ተቀበረ።
ዮፍታሔ
6እስራኤላውያን ባዓልና ዐስታሮት የተባሉትን ባዕዳን አማልክት እንዲሁም የሶርያን፥ የሲዶናን፥ የሞአብን፥ የዐሞንንና የፍልስጥኤምን አማልክት በማምለክ እንደገና እግዚአብሔርን በደሉ፤ እርሱንም ማምለክ ተዉ፤ 7ስለዚህ እግዚአብሔር በእስራኤላውያን ላይ ተቈጣ፤ ለፍልስጥኤማውያንና ለዐሞናውያን አሳልፎ ሰጣቸው። 8አሞናውያንና ፍልስጥኤማውያንም ከዮርዳኖስ ማዶ በአሞራውያን ምድር በገለዓድ ውስጥ የሚኖሩትን እስራኤላውያንን ለዐሥራ ስምንት ዓመት አስጨንቀው ገዙአቸው። 9ዐሞናውያን የይሁዳን፥ የብንያምንና የኤፍሬምን ነገዶች ለመውጋት ዮርዳኖስን ተሻገሩ፤ እስራኤላውያንም እጅግ ተጨነቁ።
10ከዚህ በኋላ እስራኤላውያን “አንተን አምላካችንን ትተን በዓል ተብለው የሚጠሩትን ባዕዳን አማልክት በመከተላችን በአንተ ላይ በደል ሠርተናል” በማለት ወደ እግዚአብሔር ጮኹ።
11-12እግዚአብሔር እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ግብጻውያን፥ አሞራውያን፥ ዐሞናውያን፥ ፍልስጥኤማውያን፥ ሲዶናውያን፥ ዐማሌቃውያንና ማዖናውያን ከዚህ በፊት ጨቊነው በገዙአችሁ ጊዜ ወደ እኔ ጮኻችሁ ነበር፤ ታዲያ እኔስ ከእነርሱ ጭቈና በመታደግ አድኛችሁ አልነበረምን? 13እናንተ ግን እስከ አሁን ድረስ እኔን ትታችሁ ለባዕዳን አማልክት ሰገዳችሁ፤ ስለዚህ እኔ እናንተን ዳግመኛ አልታደጋችሁም፤ 14ሂዱ፤ ወደ መረጣችኋቸው ባዕዳን አማልክትም ጩኹ፤ መከራ በሚደርስባችሁ ጊዜም እስቲ እነርሱ ራሳቸው ያድኑአችሁ።”
15የእስራኤል ሕዝብ ግን እግዚአብሔርን “በእርግጥ በድለናል፤ አንተ በእኛ ላይ የፈለግኸውን አድርግብን፤ ብቻ እባክህ የዛሬን አድነን” አሉት። 16ባዕዳን አማልክታቸውንም አስወግደው፥ እግዚአብሔርን አመለኩ፤ እግዚአብሔርም ስለ እስራኤል መከራ እጅግ አዘነ።
17ከዚህ በኋላ የዐሞናውያን ሠራዊት ለጦርነት ተዘጋጅቶ በገለዓድ ሰፈረ፤ የእስራኤልም ሰዎች በአንድነት ተሰብስበው በገለዓድ ምጽጳ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ሰፈሩ፤ 18በዚያም ሕዝቡና በገለዓድ የእስራኤላውያን የነገድ አለቆች ሁሉ “ዐሞናውያንን ስንወጋ መሪ የሚሆነን ማነው? ጦርነቱን የሚከፍት ሰው እርሱ በገለዓድ ለሚኖር ሰው ሁሉ መሪ ይሆናል” ተባባሉ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ