የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መሳፍንት 15

15
1ከጥቂት ጊዜ በኋላ በስንዴ መከር ወራት ሶምሶን ሚስቱን ለመጐብኘት አንድ የፍየል ጠቦት ይዞ ሄደ፤ አባትዋንም “ሚስቴ ወዳለችበት ክፍል መግባት እፈልጋለሁ” አለው።
አባትዋ ግን እንዲገባ አልፈቀደለትም፤ 2ሶምሶንንም “አንተ የጠላሃት ስለ መሰለኝ ሚዜህ ለነበረው ሰው ዳርኳት፤ የሆነ ሆኖ የእርስዋ ታናሽ ይበልጥ ውብ አይደለችምን? እባክህ እርስዋን አግባት” አለው።
3ሶምሶንም “ከእንግዲህ ወዲህ በፍልስጥኤማውያን ላይ ክፉ ነገር ባደርግ አልወቀስበትም!” አለ። 4ሄዶም ሦስት መቶ ቀበሮዎችን በማደን ያዘ፤ ጥንድ ጥንድ አድርጎ ጭራቸውን በማያያዝ በገመድ አሰረ፤ ችቦዎችም አምጥቶ በጭራቸው መካከል አሰረ። 5ከዚያም በኋላ በችቦዎቹ ላይ እሳት በማቀጣጠል ቀበሮዎቹን ገና ወዳልታጨደው ወደ ፍልስጥኤማውያን የስንዴ ሰብል ውስጥ ለቀቃቸው፤ በዚህም ዐይነት ታጭዶ የተከመረውን ብቻ ሳይሆን ገና በማሳ ላይ ያለውን ስንዴ፥ የወይራና የወይን ተክል ጭምር አቃጠለ። 6ፍልስጥኤማውያን ይህን ያደረገው ማን እንደሆን በጠየቁ ጊዜ፥ ሶምሶን መሆኑን ተረዱ፤ የቲምና ተወላጅ የሆነው ዐማቱ የሶምሶንን ሚስት ሚዜው ለነበረ ሌላ ሰው ሰጥቶበት ነበር፤ ስለዚህ ፍልስጥኤማውያን ሄደው ሴቲቱንና አባቷን በእሳት አቃጠሉ።
7ሶምሶንም “እንግዲህ እናንተ ይህን አድርጋችኋል፤ እኔ ደግሞ እናንተን ሳልበቀል አልተዋችሁም!” ብሎ ማለ። 8ወዲያውም ብርቱ አደጋ ጥሎባቸው ከእነርሱ ብዙዎችን ገደለ፤ ከዚህም በኋላ ሄዶ ዔጣም ተብላ በምትጠራ ስፍራ በዋሻ ውስጥ ተቀመጠ።
ሶምሶን ፍልስጥኤማውያንን ድል አደረገ
9ፍልስጥኤማውያን መጥተው በይሁዳ ሰፈሩ፤ ሌሒ ተብላ የምትጠራውንም ከተማ ወረሩአት፤ 10የይሁዳም ሰዎች “በእኛ ላይ አደጋ የምትጥሉት ስለምንድነው?” ሲሉ ጠየቁአቸው።
እነርሱም “እኛ የመጣነው ሶምሶንን ልንይዝና እስረኛ አድርገን ወስደን በእኛ ላይ ያደረገውን ሁሉ በእርሱም ላይ ልንፈጽምበት ነው” ሲሉ መለሱላቸው። 11ስለዚህም ሦስት ሺህ የሚሆኑ የይሁዳ ሰዎች በዔጣም ወዳለው ዋሻ ሄደው “ፍልስጥኤማውያን ገዢዎቻችን እንደ ሆኑ አታውቅምን? ታዲያ ይህ ያደረግህብን ምንድን ነው?” ሲሉ ሶምሶንን ጠየቁት።
እርሱም “እኔ በእነርሱ ላይ ያደረግኹት ልክ እነርሱ በእኔ ላይ ያደረጉትን ነው” አላቸው።
12እነርሱም “እኛ አሁን ወደዚህ የመጣነው አንተን አስረን ለእነርሱ አሳልፈን ልንሰጥህ ነው” አሉት።
ሶምሶንም “እናንተ ራሳችሁ እንደማትገድሉኝ ማሉልኝ” አላቸው።
13እነርሱም “መልካም ነው፤ አንተን በገመድ አስረን ለእነርሱ አሳልፈን እንሰጥሃለን እንጂ እኛስ አንገድልህም” ሲሉ መለሱለት። ከዚህም በኋላ በሁለት አዳዲስ ገመዶች አሰሩትና ከዋሻው አውጥተው ወሰዱት።
14ሶምሶንም ወደ ሌሒ በመጣ ጊዜ ፍልስጥኤማውያን እየደነፉ መጡበት፤ የእግዚአብሔር መንፈስ አበረታው፤ ክንዱ የታሰሩበት ገመዶች እሳት እንደ ነካቸው የሐር ፈትል ከእጁ ላይ ቀልጠው ወደቁ። 15ከዚህ በኋላ በቅርብ ጊዜ የሞተ የአንድ አህያ መንጋጋ አገኘ፤ ጐንበስ ብሎ አንሥቶም አንድ ሺህ ሰው ገደለበት።
16ሶምሶንም፥
“በአህያ መንጋጋ አንድ ሺህ ሰው ገደልኩ፤
በዚህም የአህያ መንጋጋ
ሬሳውን በሬሳ ላይ ከመርሁ” አለ።
17ከዚያም በኋላ ይዞት የነበረውን መንጋጋ ወረወረው፤ ይህም የተፈጸመበት ያ ስፍራ “ራማት ሌሒ” ተብሎ ተጠራ። #15፥17 “ራማት ሌሒ”፦ በዕብራይስጥ “የመንጋጋ ኮረብታ” ማለት ነው።
18ከዚህ በኋላ ሶምሶን በጣም ተጠማ፤ ወደ እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ጮኸ፤ “ይህን ትልቅ ድል ለአገልጋይህ ሰጥተኸኛል፤ ታዲያ፥ እኔ አሁን በውሃ ጥም ልሙትን? ባልተገረዙ ሰዎች እጅም ልውደቅን?” 19እግዚአብሔር በሌሂ ያለው ጐድጓዳ ቦታ ከፈተለት፤ ከእርሱም ውሃ ወጣ፤ በጠጣም ጊዜ መንፈሱ ተመልሶለት ተጠናከረ፤ ስለዚህም ያ ቦታ “ዐይን ሃቆሬ” የተባለ። እርሱም እስከ ዛሬ ድረስ በሌሂ ይገኛል። #15፥19 “ዐይን ሃቆሬ”፦ በዕብራይስጥ “የጠሪው ምንጭ” ማለት ነው።
20ፍልስጥኤማውያን በሀገሩ ላይ ገዢዎች በነበሩበት ዘመን ሶምሶን እስራኤልን ለኻያ ዓመት ሙሉ መራ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ