መጽሐፈ መሳፍንት 19
19
አንድ ሌዋዊና የእርሱ ቊባት
1በእስራኤል ገና ንጉሥ ባልነበረበት ጊዜ በኮረብታማው በኤፍሬም አገር ራቅ ብሎ በሚገኝ ስፍራ የሚኖር አንድ ሌዋዊ ነበረ፤ ይህ ሰው በይሁዳ ግዛት ከምትገኘው ከቤተልሔም አንዲት ልጃገረድ ቊባት ወስዶ ነበር፤ 2ነገር ግን ልጅቱ ከእርሱ ጋር ተጣልታ በቤተልሔም ወደሚገኘው ወደ አባቷ ቤት ኮብልላ ሄደች፤ በዚያም አራት ወር ቈየች። #19፥2 ተጣልታ፦ በዕብራይስጡ አመነዘረች ይላል። 3ዘግየት ብሎም ሰውየው ወደ ልጅቱ ለመሄድና በማግባባት መልሶ ሊያመጣት ቊርጥ ውሳኔ አደረገ፤ ሲሄድም አገልጋዩንና ሁለት አህዮች ይዞ ነበር፤ እዚያም በደረሰ ጊዜ ልጅቱ ተቀብላ ወደ ቤት አስገባችው፤ የልጅቱም አባት ሰውየውን ባየው ጊዜ በደስታ ተቀበለው፤ 4እዚያ እንዲቈይ አደረገው፤ እርሱም ሦስት ቀን በዚያ ቈየ፤ እዚያም እየበሉና እየጠጡ ቈዩ። 5በአራተኛው ቀን ጧት በማለዳ ተነሡና ለመሄድ ተዘጋጁ፤ የልጅቱ አባት ግን የልጁን ባል “ብርታት እንድታገኝ መጀመሪያ እህል ቅመስ፤ ከዚያም በኋላ ትሄዳለህ” አለው።
6ስለዚህ ሁለቱ ሰዎች ተቀምጠው አብረው ተመገቡ፤ የሴቲቱም አባት ሌዋዊውን “እባክህ ዛሬ ደስ ብሎህ እዚሁ ዕደር” አለው።
7ሌዋዊው ለመሄድ ተነሣ፤ የልጅቱ አባት ግን እንዲቈይ አግባባውና ያንን ሌሊት በዚያው አሳለፈ፤ 8በአምስተኛው ቀን ጧት በማለዳ ተነሥቶ ጒዞ ጀመረ፤ የልጅቱ አባት ግን “እባክህ እህል ቅመስ፤ ቈየት ብለህ ትሄዳለህ” አለው፤ ስለዚህም ሁለቱ ሰዎች አብረው በሉ።
9ሌዋዊውና ቊባቱ እንዲሁም አገልጋዩ ሆነው እንደገና ጒዞ ሲጀምሩ የልጅቱ አባት እንዲህ አለ፤ “ተመልከቱ! እነሆ ጊዜው መሽቶአል፤ ሌሊቱን እዚሁ ብታሳልፉ ይሻላል፤ አሁን ፈጥኖ ይጨልማል፤ እዚሁ ደስ ብሎአችሁ ዕደሩ፤ ነገ በማለዳ ተነሥታችሁ ጒዞ በመጀመር ወደ ቤታችሁ ትሄዳላችሁ።”
10ሌዋዊው ግን ያንን ሌሊት እዚያ ለማሳለፍ አልፈለገም፤ ስለዚህ እርሱ፥ ቊባቱና አገልጋዩ ተነሥተው ጒዞ ጀመሩ፤ ኮርቻ የተጫኑ ሁለት አህዮችም ነበሩአቸው፤ ቀኑም በመሸ ጊዜ የቡስ ተብላ ትጠራ ወደነበረችው ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ አጠገብ ደረሱ፤ 11ወደ ኢያቡስ በደረሱ ጊዜ መሸባቸው፤ አሽከሩም ጌታውን “ና እባክህ ወደ እዚህ ወደ ኢያቡሳውያን ከተማ እንመለስና እዚያ እንደር” አለው።
12ጌታው ግን “እስራኤላውያን በማይኖሩባት ከተማ አንቆምም፤ ይህን ስፍራ አልፈን ሄደን በጊብዓ እንደር” ብሎ መለሰለት፤ 13አሽከሩንም “ና ከእነዚህ ቦታዎች ወደ አንዱ እንቅረብ፤ በጊብዓ ወይም በራማ እንደር” አለው። 14ስለዚህ ኢየሩሳሌምን አልፈው ጒዞአቸውን ወደፊት ቀጠሉ፤ በብንያም ግዛት በምትገኘው በጊብዓ ሲደርሱ ፀሐይ ጠለቀች፤ 15የሚያድሩበትንም ስፍራ ፈልገው ለማግኘት ከመንገድ ወጣ አሉ፤ ወደ ከተማይቱም ገብተው በአደባባዩ አጠገብ ተቀመጡ፤ ነገር ግን ወደ ቤት ወስዶ የሚያሳድራቸው ማንንም አላገኙም።
16በዚያም ተቀምጠው ሳሉ በእርሻ ቦታ የቀን ሥራውን ፈጽሞ ወደ ቤቱ የሚመለስ አንድ ሽማግሌ በአጠገባቸው አለፈ፤ ይህ ሰው አስቀድሞ ከኮረብታማው ከኤፍሬም አገር የመጣ ሲሆን፥ አሁን ግን የሚኖረው በጊብዓ ነበር፤ በዚያ የሚኖሩት ሌሎቹ ሰዎች ግን ከብንያም ነገድ የተወለዱ ናቸው፤ 17ሽማግሌውም በከተማይቱ አደባባይ የተቀመጠውን ሰው አይቶ “ከየት መጣህ? የምትሄደውስ ወዴት ነው?” ሲል ጠየቀው።
18ሌዋዊውም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “በይሁዳ በምትገኘው በቤተልሔም ነበርን፥ ወደ እግዚአብሔር ቤትና በኮረብታማው በኤፍሬም አገር ራቅ ብሎ ወደሚገኘው ቤታችን ለመድረስ በጒዞ ላይ ነን፤ ወደ ቤቱ ወስዶ የሚያሳድረን እስከ አሁን አላገኘንም፤ 19እኛ ግን ለአህዮቻችን ገፈራና ገለባ፥ ለቊባቴና ለእኔ እንዲሁም ለአገልጋዬ እንጀራና የወይን ጠጅ አለን፤ የሚያስፈልገንን ሁሉ ይዘናል፤ ምንም ያጣነው ነገር የለም” አለው።
20ሽማግሌውም “ሰላም ለአንተ ይሁን! እነሆ ወደ ቤቴ ግባ! እኔ ማደሪያ አዘጋጅልሃለሁ፤ በዚህ አደባባይ ላይ ማደር አይገባህም” አለ። 21ስለዚህ ወደ ቤት ወሰዳቸውና ለአህዮቹ ገፈራ መገበለት፤ እንግዶቹም እግራቸውን ታጥበው ራታቸው በሉም ጠጡ።
22እየተደሰቱ ሳለም ከከተማይቱ የመጡ ጋጠወጦች በድንገት ቤቱን ከበው በሩን መደብደብ ጀመሩ፤ ሽማግሌውንም “ያንን ወደ ቤትህ የገባውን ሰው ግብረ ሰዶም እንድንፈጽምበት አውጣልን!” አሉት።
23ሽማግሌው ግን ወደ ውጪ ወጥቶ እንዲህ አላቸው፦ “አይሆንም ወዳጆቼ ሆይ! እባካችሁ ይህን የመሰለ አስከፊ ነገር አታድርጉ! ይህ ሰው የእኔ እንግዳ ነው፤ 24እነሆ የሰውዬው ቊባትና ድንግል የሆነችውን የእኔንም ሴት ልጅ! አውጥቼ ልስጣችሁ፤ ተጠቀሙባቸው፤ የምትፈልጉትንም ነገር አድርጉባቸው፤ በዚህ ሰው ላይ ግን ክፉ ነገር አታድርጉ!” አላቸው። #ዘፍ. 19፥5-8። 25ሰዎቹ ግን አልሰሙትም፤ ስለዚህ ሰውዬው ቊባቱን ወደ ውጪ አውጥቶ ሰጣቸው፤ ሌሊቱንም ሙሉ በእርስዋ ላይ ተራ በተራ በማመንዘር መጫወቻ አድርገዋት ዐደሩ፤ ሲነጋጋ ግን እንድትሄድ ለቀቁአት።
26ጧትም ጎሕ ሲቀድ ያቺ ሴት መጥታ ባልዋ ባደረበት በሽማግሌው ቤት በር አጠገብ ወደቀች፤ ፀሐይ እስክትወጣም ድረስ በዚያ ነበረች፤ 27በዚያም ጧት ባልየው ጒዞውን ለመቀጠል በሩን ሲከፍት ቊባቱ እጅዋን ወደ በሩ እንደ ዘረጋች በቤቱ ፊት ለፊት ወድቃ አገኛትና፥ 28“ተነሽ እንሂድ!” አላት፤ ነገር ግን ምንም መልስ አላገኘም፤ ከዚህ በኋላ ሬሳዋን በአህያ ላይ ጭኖ ወደ ቤቱ ጒዞውን ቀጠለ፤ 29እዚያም በደረሰ ጊዜ ወደ ቤቱ ገባ፤ ቢላዋም አንሥቶ የቊባቱን ሬሳ ዐሥራ ሁለት ቦታ ቈራረጠው፤ ወደ እስራኤል አገር ሁሉ ለዐሥራ ሁለቱ ነገዶች አንዳንድ ቊራጭ ላከ፤ #1ሳሙ. 11፥7። 30ከዚያ በኋላ የላካቸውን ሰዎች እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፦ “ለእስራኤላውያን ሁሉ እንዲህ በሉአቸው፦ ‘የእስራኤል ሕዝብ ከግብጽ ምድር ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እንዲህ ያለ ነገር ተደርጎ ያውቃልን? አስቡበት፤ ተመካከሩበት ተነጋገሩበትም።’ ” ያዩት ሁሉ “እስከዚህ ጊዜ ድረስ እንዲህ ያለ ነገር ታይቶም አይታወቅ!” አሉ።
Currently Selected:
መጽሐፈ መሳፍንት 19: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997