መጽሐፈ መሳፍንት 18
18
ሚካና የዳን ነገድ
1በዚያም ዘመን በእስራኤል ንጉሥ አልነበረም፤ በእስራኤል ነገዶች መካከል የራሳቸው የሆነ የርስት ድርሻ ገና ያላገኙ ስለ ነበሩ የዳን ነገድ ተወላጆች የሚሰፍሩበትን ርስት ለማግኘት በመፈለግ ላይ ነበሩ። 2ስለዚህ የዳን ሕዝብ ከነገዱ ቤተሰቦች መካከል ብርታት ያላቸውን አምስት ሰዎች መረጡ፤ ምድሪቱንም አጥንተው እንዲመለሱ መመሪያ በመስጠት ከጾርዓና ከኤሽታኦል ከተሞች ላኩአቸው፤ እነርሱም ኮረብታማ ወደ ሆነው ወደ ኤፍሬም አገር በደረሱ ጊዜ በሚካ ቤት አደሩ፤ 3እዚያም በነበሩበት ጊዜ ወጣቱን ሌዋዊ በአነጋገሩ ሁኔታ ከየት እንደ ሆነ ለይተው ዐወቁት፤ ወደ እርሱም ቀርበው “እዚህ ምን ትሠራለህ፤ ወደዚህ ያመጣህስ ማነው?” ሲሉ ጠየቁት።
4እርሱም “ደሞዝ እየከፈለኝ ካህን ሆኜ ላገለግለው ከሚካ ጋር ተስማምቻለሁ” ሲል መለሰላቸው።
5እነርሱም “ጒዞአችን ይሳካልን እንደ ሆነ እባክህ እግዚአብሔርን ጠይቅልን” አሉት።
6ካህኑም፦ “ሂዱ በጒዞአችሁ ምንም ችግር አይገጥማችሁም፥ እግዚአብሔር ይጠብቃችኋል” ሲል መለሰላቸው።
7ከዚህ በኋላ አምስቱ ሰዎች ከዚያ ሄደው ወደ ላዪሽ ደረሱ፤ በዚያም የነበሩት ኗሪዎች ልክ እንደ ሲዶናውያን በሰላም የሚኖሩ መሆናቸውን ተመለከቱ፤ ሕዝቡም ከማንም ጋር ሳይጋጩ ጸጥ ባለ መንፈስ የሚኖሩ ሰላም ወዳዶች ነበሩ፤ ከዚህም ጋር ከሚያስፈልጋቸው ነገር ሁሉ ምንም የሚጐድላቸው አልነበረም፤ ከዚህም የተነሣ ከማንኛውም ሕዝብ ጋር ግንኙነት ሳይኖራቸው ከሲዶናውያን በመራቅ ተገልለው ይኖሩ ነበር። 8አምስቱም ሰዎች ወደ ጾርዓና ወደ ኤሽታኦል በተመለሱ ጊዜ ወገኖቻቸው፦ “ምን ወሬ አላችሁ?” ብለው ጠየቁአቸው። 9እነርሱም እንዲህ አሉአቸው፦ “እንግዲህ ኑ! በላዪሽ ላይ አደጋ እንጣል! ምድሪቱ በጣም ጥሩ መሆንዋን አይተናል፤ እዚህ ያለ ሥራ ቦዝናችሁ አትቀመጡ፤ ይልቅስ በፍጥነት ሄዳችሁ ያዙአት! 10ወደዚያም በምትሄዱበት ጊዜ ምንም የማይጠራጠሩ ሰላም ወዳዶች ሆነው ታገኙአቸዋላችሁ፤ አገሪቱ ታላቅ ናት፤ ለሰው የሚያስፈልገው ማናቸውም ነገር በውስጥዋ ይገኛል፤ እግዚአብሔር ይህችን አገር ለእናንተ ሰጥቶአችኋል።”
11ስለዚህ ከዳን ነገድ የጦር መሣሪያ የታጠቁ ስድስት መቶ ሰዎች ከጾርዓና ከኤሽታኦል ተነሡ፤ 12እነርሱም ወጥተው በይሁዳ በምትገኘው ከቂርያትይዓሪም በስተ ምዕራብ ሰፈሩ፤ ያ ስፍራ እስከ አሁን የዳን ሰፈር ተብሎ የሚጠራውም ስለዚህ ነው። 13ከዚያም ጒዞአቸውን በመቀጠል በኮረብታማው በኤፍሬም አገር ወደሚገኘው ወደ ሚካ ቤት መጡ።
14በላዪሽ ዙሪያ ያለውን አገር ሊያጠኑ ተልከው የነበሩት አምስት ሰዎች ለጓደኞቻቸው “በዚህ ስፍራ ከነዚህ ቤቶች በአንዱ ውስጥ በብር የተለበጠ የእንጨት ጣዖት እንዳለ ታውቃላችሁን? ሌሎች ጣዖቶች አንድ ኤፉድም በተጨማሪ አለ፤ ታዲያ ምን ማድረግ የሚገባን ይመስላችኋል?” አሉአቸው። 15ወጣቱ ሌዋዊ ወደሚኖርበትም ወደ ሚካ ቤት ገቡ፤ ሌዋዊውንም እንዴት እንደሚኖር ጠየቁት፤ 16የጦር መሣሪያ የታጠቁት ከዳን የመጡት ስድስት መቶ ሰዎች በዚያን ጊዜ በቅጽሩ በር አጠገብ ቆመው ነበር። 17አምስቱም ሰላዮች በቀጥታ ወደ ሚካ ቤት ገብተው ያንን በብር የተለበጠ የእንጨት ጣዖትና ሌሎቹንም ጣዖቶች ኤፉዱንም ጭምር ወሰዱ፤ ይህም በሚሆንበት ጊዜ ካህኑ የጦር መሣሪያ ከታጠቁት ስድስት መቶ ሰዎች ጋር በቅጽር በሩ አጠገብ ቆሞ ነበር።
18እርሱም ሰዎቹ ወደ ሚካ ቤት ሄደው ምስሎቹንና ኤፉዱን በሚወስዱበት ጊዜ “ምን ማድረጋችሁ ነው?” ሲል ጠየቃቸው።
19እነርሱም “ዝም በል! አፍህን ዝጋ፤ ይልቅስ መጥተህ ካህናችንና አማካሪያችን ሁን፤ የአንድ ሰው ቤተሰብ ካህን ከምትሆን የአንድ እስራኤላዊ ነገድ ካህን መሆን አይሻልህምን?” አሉት። 20ይህም አባባል ካህኑን እጅግ ስላስደሰተው ጣዖቶቹንና ኤፉዱን ይዞ ከእነርሱ ጋር ሄደ።
21እነርሱም ልጆቻቸውን ከብቶቻቸውንና ዕቃቸውን ሁሉ ከፊት አስቀድመው ወደ ኋላ በመመለስ ጒዞአቸውን ቀጠሉ። 22ከቤቱ ራቅ ብለው ከሄዱ በኋላ ሚካ ጐረቤቶቹን ሰብስቦ በመከተል ከዳን የመጡትን ሰዎች ደረሰባቸውና፤ 23ደነፋባቸው፤ ከዳን የመጡትም ሰዎች ወደ ኋላ መለስ ብለው ሚካን “ምን ሆነሃል? ይህን ሁሉ ሰውስ የሰበሰብከው ለምንድነው?” ሲሉ ጠየቁት።
24ሚካም “እንዴት ‘ምን ሆነሃል’ ትሉኛላችሁ? የሚያገለግለኝን ካህንና እኔ የሠራኋቸውን ጣዖቶች ዘርፋችሁ ሄዳችሁ፤ ታዲያ እኔ ምን ተረፈኝ?” አላቸው።
25ከዳን የመጡትም ሰዎች “የተቈጡ ሰዎች አደጋ እንዳይጥሉብህና የአንተንና የቤተሰብህን ሕይወት እንዳታጣ በመካከላችን ምንም ድምፅ ባታሰማ ይሻልሃል” አሉት። 26ከዚህም በኋላ ጒዞአቸውን ቀጠሉ፤ ሚካም ሊቋቋማቸው እንደማይችል ባየ ጊዜ ተመልሶ ወደ ቤቱ ሄደ።
27ከዳን የመጡትም ሰዎች ሚካ የሠራውን ጣዖትና ያገለግለው የነበረውን ካህን ይዘው ጸጥ ብሎ ተዝናንቶ ወደ ተቀመጠው ሕዝብ ወደ ላዪሽ መጡ፤ ሕዝቡንም በሰይፍ ፈጁ፤ ከተማይቱንም በእሳት አቃጠሉ። 28የላይሽ ሕዝብ ከማንም ጋር ግንኙነት ስላልነበራቸውና ከሲዶንም ርቀው ይኖሩ ስለ ነበረ የሚያድናቸው አልተገኘም። ከተማዋ በቤትረሖብ አጠገብ በሚገኝ ሸለቆ ውስጥ ነበረች፤ የዳን ሰዎችም ከተማዋን እንደገና ሠርተው ኖሩባት። 29የቀድሞ ስምዋንም ላይሽን ለውጠው የቀድሞው አባታቸው በነበረው በያዕቆብ ልጅ ስም ዳን ብለው ጠሩአት፤ 30የዳን ሰዎችም ያመልኩት ዘንድ ያን ጣዖት በዚያ አኖሩ፤ ከሙሴ ልጅ ከጌርሾም የተወለደው ዮናታንም ለዳን ነገድ ካህን ሆኖ ማገልገል ጀመረ። የእርሱም ዘሮች ሕዝቡ ተማርከው እስከ ተሰደዱበት ጊዜ ድረስ ማገልገላቸውን ቀጠሉ። 31በዚህም ዐይነት የሚካ ጣዖት እግዚአብሔር የሚመለክበት ድንኳን በሴሎ እስከ ነበረበት ዘመን በዚያው ቈየ።
Currently Selected:
መጽሐፈ መሳፍንት 18: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997