የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መሳፍንት 17

17
ሚካ ያሠራቸው ጣዖቶች
1ሚካ ተብሎ የሚጠራ አንድ ሰው በኮረብታማው በኤፍሬም አገር ይኖር ነበር፤ 2እርሱም አንድ ቀን እናቱን እንዲህ አላት፤ “አንድ ሰው አንድ ሺህ አንድ መቶ ጥሬ ብር በሰረቀሽ ጊዜ ያን የሰረቀሽን ሰው ስትረግሚው ሰምቼሽ ነበር፤ እነሆ ያ ብር በእኔ እጅ ነው፤ እርሱንም የወሰድኩ እኔ ነበርኩ።”
እናቱም “ልጄ! እግዚአብሔር ይባርክህ!” አለችው። 3ልጁም ገንዘቡን መልሶ ለእናቱ ሰጣት፤ እርስዋም “እኔ ራሴ ብሩን ለእግዚአብሔር ስለ ልጄ የተለየ አደርገዋለሁ፤ ከእንጨት ተሠርቶ በብር የተለበጠ ጣዖት ማሠሪያም ይሆናል፤ ስለዚህ ብሩን ለአንተ መልሼ እሰጥሃለሁ” አለችው። 4ልጁም ብሩን ለእናቱ ሰጣት፤ እርስዋም ከላዩ ሁለት መቶ ብር አንሥታ እንጨት ጠርቦ በብሩ በመለበጥ ጣዖት ለሚሠራላት የብር አንጥረኛ ሰጠችው፤ ጣዖቱም በሚካ ቤት ተቀመጠ።
5ይህ ሚካ የተባለ ሰው የራሱ የሆነ የአምልኮ ስፍራ ነበረው፤ በርከት ያሉ ጣዖቶች አንድ ኤፉድ ሠርቶ ከልጆቹ አንዱን ካህን ሆኖ እንዲያገለግለው ሾመው፤ 6በዚያን ጊዜ በእስራኤል ንጉሥ አልነበረም፤ እያንዳንዱም ሰው ለራሱ ደስ ያለውን ነገር ሁሉ እንደ ፈለገ ያደርግ ነበር። #መሳ. 21፥25።
7በዚያን ወቅት በይሁዳ ግዛት በቤተልሔም ከተማ የሚኖር አንድ ወጣት ሌዋዊ ነበር፤ 8ይህም ሰው የሚኖርበትን ስፍራ ለማግኘት ከቤተልሔም ተነሥቶ ሄደ፤ በጒዞም ላይ ሳለ በኮረብታማው በኤፍሬም አገር ወደሚገኘው ወደ ሚካ ቤት መጣ፤ 9ሚካም “ከወዴት መጣህ?” አለው።
እርሱም “እኔ በይሁዳ ግዛት ከምትገኘው ከቤተልሔም የመጣሁ ሌዋዊ ነኝ፤ የምኖርበትን ስፍራ እየፈለግሁ ነው” ሲል መለሰለት።
10ሚካም “እንግዲያውስ ከእኔ ጋር ኑር፤ የእኔ አማካሪና ካህን ሁንልኝ፤ በዓመት ዐሥር ብር እንዲሁም ልብስና ምግብ እሰጥሃለሁ” አለው። 11ወጣቱ ሌዋዊም ከሚካ ጋር ለመኖር ተስማማ፤ ያም ወጣት ካህን ለሚካ እንደ ልጅ ሆነለት፤ 12ሚካም እርሱን ካህን አድርጎ ሾመው፤ በቤቱም ተቀመጠ። 13ሚካም “እንግዲህ ሌዋዊ ካህን ካገኘሁ እግዚአብሔር ሁሉን ነገር እንደሚያሳካልኝ ዐውቃለሁ” አለ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ