መጽሐፈ መሳፍንት 20
20
የእስራኤል ሕዝብ ለጦርነት መዘጋጀት
1ከሰሜን እስከ ደቡብ፥ ማለትም ከዳን እስከ ቤርሳቤህ እንዲሁም በስተምሥራቅ በገለዓድ ምድር ያሉት የእስራኤል ሕዝብ በሙሉ ለጦርነት ተዘጋጁ፤ በአንድነትም ሆነው በምጽጳ በእግዚአብሔር ፊት ተሰበሰቡ፤ 2የእስራኤል ሕዝብና ነገድ አለቆች ሁሉ፥ እንዲሁም አራት መቶ ሺህ መሣሪያ የታጠቁ የእግረኛ ጦር ወታደሮች በስብሰባው ተገኝተው ነበር። 3በዚያን ጊዜ የብንያም ነገድ እስራኤላውያን በሙሉ በምጽጳ መሰብሰባቸውን ሰሙ።
እስራኤላውያንም “ይህ ክፉ ሥራ የተፈጸመው እንዴት እንደ ሆነ ንገሩን!” አሉ፤ 4ቊባቱ የተገደለችበት ያ ሌዋዊ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እኔና ቊባቴ ሌሊቱን ለማሳለፍ በብንያም ግዛት ወደምትገኘው ወደ ጊብዓ ሄድን፤ 5የጊብዓ ሰዎች በእኔ ላይ አደጋ ለመጣል መጥተው በሌሊት ቤቱን ከበቡት፤ በመጀመሪያ እኔን ለመግደል አስበው ነበር፤ በኋላ ግን በቊባቴ ላይ ተረባርበው ስላመነዘሩባት ሞተች፤ 6ከዚህ በኋላ የቁባቴን አስከሬን ወስጄ ቈራረጥሁት፤ እነርሱ ይህን የመሰለ ክፉ በደል ስለ ሠሩ የቈራረጥኋቸውን ቊርጥራጮች ወደ እስራኤል አገር ሁሉ ላክሁ። 7እዚህ ያላችሁት እስራኤላውያን ሁሉ ምክራችሁንና ፍርዳችሁን ስጡ።”
8ሕዝቡም ሁሉ በአንድነት ቆመው እንዲህ አሉ፤ “ከእኛ መካከል በድንኳንም ሆነ በቤት ውስጥ የሚኖር ማንኛውም ሰው ወደ ቤቱ አይመለስም፤ 9የምናደርገውም ይህ ነው፤ ዕጣ በመጣል በጊብዓ ላይ አደጋ የሚጥሉ ሰዎችን እንመርጣለን፤ 10በእስራኤል ላይ በፈጸሙት አሳፋሪ ተግባር በብንያም ግዛት የምትገኘውን የጊብዓን ሕዝብ ለመበቀል ለሚዘምተው ሠራዊት ስንቅ ያቀብሉ ዘንድ ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ መካከል ከመቶ ዐሥር፥ ከሺህ መቶ፥ ከዐሥር ሺህ አንድ ሺህ ሰው እንመድባለን።” 11ስለዚህም የእስራኤል ሰዎች ሁሉ በከተማይቱ ላይ አደጋ ለመጣል በአንድነት ተሰበሰቡ።
12የእስራኤል ነገዶች በመላው በብንያም ግዛት ተዘዋውረው እንዲህ የሚል ቃል የሚናገሩትን መልእክተኞች ላኩ፥ “ይህ የፈጸማችሁት ክፉ ነገር ምንድን ነው? 13እነርሱን ገድለን ይህን ክፉ ነገር ከእስራኤል እናስወግድ ዘንድ እነዚያን በጊብዓ ያሉትን ነውረኞች አሳልፋችሁ ስጡን።” የብንያም ሕዝብ ግን የቀሩት እስራኤላውያን የነገሩአቸውን ነገር አልተቀበሉም፤ 14እንዲያውም እነርሱን ለመውጋት ከብንያም ከተሞች ሁሉ ተሰባስበው ወደ ጊብዓ መጡ፤ 15በዚያን ቀን ብንያማውያን፥ ከየከተሞቻቸው ኻያ ስድስት ሺህ መሣሪያ የታጠቁ ሰዎችን አሰባሰቡ፤ ይህም ከጊብዓ ኗሪዎች ከተመረጡት ከሰባት መቶ ሰዎች ሌላ ነው። 16ከእነዚያም መካከል የተመረጡ ሰባት መቶ ግራኝ ሰዎች ነበሩ፤ እነዚህም ድንጋይ የሚወነጭፉና ሌላው ቀርቶ አንዲት ጠጒርን እንኳ የማይስቱ ነበሩ። 17እስራኤላውያን የብንያምን ነገድ ሳይጨምሩ ብዛቱ አራት መቶ ሺህ መሣሪያ የታጠቀ ሠራዊት አሰለፉ።
በብንያማውያን ላይ የተደረገ ጦርነት
18እስራኤላውያን ወደ ቤትኤል ወጥተው “በብንያማውያን ላይ መጀመሪያ አደጋ መጣል የሚገባው የትኛው ነገድ ነው?” ሲሉ እግዚአብሔርን ጠየቁ።
እግዚአብሔርም “የይሁዳ ነገድ አስቀድሞ ይዝመት” አላቸው።
19ስለዚህ በማግስቱ ጧት ጒዞ ጀመሩ፤ በጊብዓ አጠገብም ሰፈሩ፤ 20በብንያም ሠራዊት ላይ አደጋ ለመጣል ሄዱ፤ ወታደሮቻቸውንም በጊብዓ ትይዩ አሰለፉ፤ 21የብንያም ሠራዊት ከከተማይቱ ወጥቶ ቀኑ ከመምሸቱ በፊት ኻያ ሁለት ሺህ የእስራኤላውያንን ወታደሮች ገደለ፤ 22የእስራኤልም ሠራዊት ተበራቱ፤ በመጀመሪያው ቀን በተሰለፉበትም ስፍራ ደግመው ተሰለፉ፤ 23እስራኤላውያንም ወጥተው በእግዚአብሔር ፊት እስከ ማታ ድረስ አለቀሱ፤ እግዚአብሔርንም “ወንድሞቻችንን ብንያማውያንን ለመውጋት እንደገና እንዝመትን?” ብለው ጠየቁት፤ እግዚአብሔርም፦ “አዎ፥ በእነርሱ ላይ ዝመቱ” አላቸው። 24በሁለተኛውም ቀን በብንያም ሠራዊት ላይ ዘመቱ፤ 25እንዲሁም ብንያማውያን በሁለተኛው ቀን ከጊብዓ ወጡ፤ በዚህም ጊዜ ዐሥራ ስምንት ሺህ የሠለጠኑ የእስራኤላውያንን ወታደሮች ገደሉ፤ 26ከዚህም በኋላ የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ወደ ቤትኤል ሄደው አለቀሱ፤ በዚያም ምንም ሳይበሉ እስከ ምሽት በእግዚአብሔር ፊት ተቀምጠው ቈዩ፤ የሚቃጠልና የደኅንነት መሥዋዕት አቀረቡ፤ 27በዚያን ጊዜ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት በቤቴል ስለ ነበረ እስራኤላውያን እግዚአብሔርን ጠየቁ። 28በዚያን ዘመን የአሮን ልጅ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ በእግዚአብሔር ፊት ያገለግል ስለ ነበረ እግዚአብሔርን ጠየቀ፦ “ወንድሞቻችንን ብንያማውያንን ለመውጋት እንደገና እንውጣን ወይስ እንቅር” ብሎ ጠየቀ። እግዚአብሔርም፥ “ነገ በእነርሱ ላይ ድልን እንድትቀዳጁ አደርጋለሁና ሂዱና ውጉአቸው!” አለ።
29ስለዚህ እስራኤላውያን ጥቂት ወታደሮችን በጊብዓ ዙሪያ እንዲሸምቁ አደረጉ፤ 30ከዚህ በፊት እንዳደረጉት ሁሉ በሦስተኛው ቀን በብንያም ሠራዊት ላይ ዘመቱ፤ ወታደሮቻቸውንም በጊብዓ ትይዩ አሰለፉአቸው። 31ብንያማውያን ሠራዊቱን እየተከተሉ በወጡ ጊዜ ከከተማው ርቀው ሄዱ፤ በዋናው መንገድ ላይ እንደበፊቱ በሠራዊቱ ላይ አደጋ መጣል ጀመሩ፤ ወደ ቤትኤልና ወደ ጊብዓ በሚወስዱት መንገዶችና በሜዳው ላይ ሠላሳ እስራኤላውያንን ገደሉ። 32ብንያማውያንም “ልክ ከዚህ በፊት እንዳደረግነው ፈጀናቸው” አሉ።
እስራኤላውያን ግን “ወደ ኋላ አፈግፍገን ከከተማው ወደ አውራ ጐዳናው እናስወጣቸው” አሉ። 33ዋናው የእስራኤል ሠራዊት ወደ በዓልታማር አፈገፈጉ፤ በጊብዓ ሜዳ ሸምቀው የነበሩት እስራኤላውያንም ድንገት ብቅ አሉ። 34ከእስራኤል በልዩ ሁኔታ የተመረጡት ዐሥር ሺህ ሰዎች በጊብዓ ላይ አደጋ ጣሉ፤ ውጊያውም ከባድ ሆነ፤ ይህ ሁሉ ሲሆን ብንያማውያን በቅርብ ጊዜ ችግር እንደሚደርስባቸው አልተገነዘቡም ነበር። 35እግዚአብሔርም እስራኤልን በብንያማውያን ላይ ድልን እንዲቀዳጁ አደረገ። በዚያን ቀን እስራኤላውያን ከብንያም ወገን ኻያ አምስት ሺህ አንድ መቶ የጦር መሣሪያ የታጠቁ ሠራዊትን ገደሉ። 36በዚህም ጊዜ ብንያማውያን መሸነፋቸውን ተገነዘቡ። ይህም የሆነበት ምክንያት እስራኤላውያን በጊብዓ አካባቢ አስፍረዋቸው በነበሩ የሽምቅ ወታደሮች በመተማመን ወደ ኋላ አፈግፍገው ስለ ነበረ ነው። 37ሸምቆም የነበረው ጦር መጥቶ በከተማው ውስጥ ያለውን ሰው ሁሉ በሰይፍ ገደሉ። 38ሸምቀው የነበሩት ሰዎች በከተማው ብዙ የጢስ ደመና እንዲያስነሡ በዋናው የእስራኤል ሠራዊትና ሸምቀው በነበሩት ሰዎች መካከል የምልክት ስምምነት ተደርጎ ነበር። 39በምልክቱም መሠረት በጦር ሜዳ የነበሩት እስራኤላውያን የመልሶ ማጥቃት እርምጃ ይወስዳሉ፤ እስከ አሁን ብንያማውያን ሠላሳ እስራኤላውያንን በመግደላቸው “ከዚህ በፊት እንዳደረግነው አሁንም ፈጀናቸው!” እያሉ ይደነፉ ነበር። 40ከዚህም በኋላ ምልክቱ ታየ፤ ይኸውም ጢሱ እንደ ደመና ሆኖ እየተትጐለጐለ ወደ ላይ ይወጣ ነበር፤ ብንያማውያንም ወደኋላቸው ሲመለከቱ ከተማይቱ በሙሉ በእሳት ተያይዛ ነበልባሉ ወደ ላይ ሲወጣ አዩ፤ 41እስራኤላውያንም የመልሶ ማጥቃት እርምጃቸውን በወሰዱ ጊዜ፥ ጨርሰው መደምሰሳቸውን ስለ ተገነዘቡ ብንያማውያን በፍርሃት ተሸበሩ፤ 42ከእስራኤላውያንም ፊት አፈግፍገው ወደ በረሓው ሸሹ፤ ነገር ግን ማምለጥ አልቻሉም፤ በዋናው ሠራዊትና አሁን ከከተማው ውስጥ በመውጣት ላይ ባሉት ወታደሮች መካከል ተይዘው ተደመሰሱ። 43እስራኤላውያን ብንያማውያንን ከበው በጊብዓ በስተ ምሥራቅ እስከሚገኘው ስፍራ ድረስ አሳደው ፈጁአቸው። 44ከብንያማውያን ምርጥ ወታደሮች ዐሥራ ስምንት ሺህ ተገደሉ፤ 45የቀሩት ወደ ኋላቸው ተመልሰው ወደ በረሓው፥ ወደ ሪሞን አለት በሸሹ ጊዜ በአውራው ጐዳና ላይ አምስት ሺህ ተገደሉ፤ እስከ ጊድዖም ድረስ ተሳደው ሁለት ሺህ ተገደሉ። 46በዚያን ቀን በአጠቃላይ የተገደሉት ብንያማውያን ኻያ አምስት ሺህ ሲሆኑ ሁሉም ምርጥ ጦረኞች ነበሩ።
47ነገር ግን ወደ በረሓው፥ የሪሞን አለት ተብሎ ወደሚጠራው ስፍራ በመሸሽ ለማምለጥ የቻሉት ስድስት መቶ ሰዎች ብቻ ነበሩ። እነርሱም በዚያ አራት ወር ቈዩ። 48እስራኤላውያን ወደ ኋላ ተመልሰው በቀሩት ብንያማውያን ላይ አደጋ በመጣል ወንዶችንም ሴቶችንም ልጆችንና እንዲሁም እንስሶችን ጭምር ያገኙትን በሙሉ ገደሉ፤ በዚያ አካባቢ ያሉትን ከተሞች ሁሉ በእሳት አቃጠሉ።
Currently Selected:
መጽሐፈ መሳፍንት 20: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997