መጽሐፈ መሳፍንት 6
6
ጌዴዎን
1የእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔርን እንደገና በደሉ፤ እግዚአብሔርም ለምድያማውያን አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱም ሰባት ዓመት ሙሉ ገዙአቸው፤ 2የምድያማውያን ኀይል በእስራኤል ላይ በረታ፤ በእነርሱም ምክንያት የእስራኤል ሕዝብ መሸሸጊያ ቦታ፥ ዋሻና ምሽግ አዘጋጁ። 3እስራኤላውያን ዘር በሚዘሩበት ጊዜ ምድያማውያን፥ ከዐማሌቃውያንና የምሥራቅ ሰዎች እየመጡ አደጋ ይጥሉባቸው ነበር። 4በአገሪቱ ላይ በመስፈር በጋዛ ዙሪያ እስካለው ስፍራ ድረስ የምድሪቱን ሰብል ያጠፉ ነበር፤ የበግ፥ የከብትና የአህያ መንጋቸውንም እየነዱ ስለሚወስዱባቸው ለእስራኤላውያን ምንም ነገር አያስቀሩላቸውም ነበር። 5ከከብቶቻቸውና ከድንኳኖቻቸው ጋር ሲመጡ ያንበጣ መንጋ ይመስሉ ነበር፤ እነርሱንና ግመሎቻቸውን ለመቊጠር እስከማይቻል ድረስ እጅግ ብዙዎች ነበሩ፤ መጥተውም ምድሪቱን ያጠፉ ነበር። 6ስለዚህ የእስራኤል ሕዝብ በምድያማውያን ምክንያት ችግር ደረሰባቸው፤ እንዲረዳቸውም ወደ እግዚአብሔር ጮኹ።
7እስራኤላውያን ከምድያማውያን እጅ ያድናቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር በጮኹ ጊዜ፥ 8እግዚአብሔር ወደ እስራኤል ሕዝብ አንድ ነቢይ ላከ፤ ያም ነቢይ ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያመጣው መልእክት ይህ ነው፦ “እኔ በባርነት ከኖራችሁባት ከግብጽ ምድር አወጣኋችሁ፤ 9ከግብጻውያንና በዚህች ምድር ከሚጨቊኑአችሁ ሕዝቦች ሁሉ አዳንኳችሁ፤ ከፊታችሁም አስወጣኋቸው፤ ምድራቸውንም ሰጠኋችሁ። 10እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደ ሆንኩና አሁን ምድራቸውን የወረሳችኋቸውን የአሞራውያንን ባዕዳን አማልክት እንዳታመልኩ ነግሬአችሁ ነበር፤ እናንተ ግን አልሰማችሁኝም።”
11ከዚያ በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ “ዖፍራ” ተብላ ወደምትጠራው መንደር መጥቶ ከአቢዔዜር ጐሣ የተወለደው የኢዮአስ ንብረት በሆነው የወርካ ዛፍ ሥር ተቀመጠ፤ የኢዮአስ ልጅ ጌዴዎን ምድያማውያን እንዳያዩት ተሸሽጎ በወይን መጭመቂያው ስፍራ የስንዴ ነዶ ይወቃ ነበር። 12በዚያም የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለትና “አንተ ኀያልና ብርቱ ሰው! እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው” አለው።
13ጌዴዎንም እንዲህ አለው፦ “ጌታዬ ሆይ! ታዲያ፥ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ሁሉ ችግር እንዴት ሊደርስብን ቻለ? አባቶቻችን እንደ ነገሩን እግዚአብሔር ያደርገው የነበረ ድንቅ ሥራ ሁሉ ዛሬ የት አለ? ከግብጽ እንዴት እንዳወጣቸውም ነግረውን ነበር፤ ዛሬ ግን እግዚአብሔር እኛን በመተው እንደ ፈለጉ ያደርጉን ዘንድ ለምድያማውያን አሳልፎ ሰጥቶናል።”
14ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር “ሂድ፤ በዚህ ባለህ ብርቱ ኀይል ሁሉ በመጠቀም እስራኤላውያንን ከምድያማውያን እጅ ነጻ አውጣ፤ እነሆ እኔ ራሴ ልኬሃለሁ” ሲል አዘዘው።
15ጌዴዎንም “ታዲያ እኔ እንዴት አድርጌ እስራኤልን ላድን እችላለሁ? ወገኔም ከምናሴ ነገድ መካከል እጅግ ደካማ ነው፤ እኔም ከቤተሰቤ መካከል በጣም አነስተኛ ነኝ” ሲል መለሰ።
16እግዚአብሔርም “እኔ ስለምረዳህ ይህን ማድረግ ትችላለህ፤ ምድያማውያንንም እንደ አንድ ሰው ያኽል አድርገህ ታደቃቸዋለህ” አለው።
17ጌዴዎንም “በአንተ ዘንድ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ፥ አንተ በእርግጥ እግዚአብሔር መሆንህን የሚያስረዳ ምልክት ስጠኝ፤ 18ምግብ የሚሆን ቊርባን እስካመጣልህም ድረስ እባክህ ከዚህ ስፍራ አትሂድ” አለው።
እግዚአብሔርም “አንተ እስክትመለስ ድረስ እቈያለሁ” አለው።
19ጌዴዎንም ወደ ቤት ገባና የፍየል ጠቦት ዐርዶ አዘጋጀ፤ ዐሥር ኪሎ የሚያኽልም ዱቄት ወስዶ እርሾ ያልገባበት እንጀራ ጋገረ፤ ሥጋውን በመሶብ፥ መረቁን በምንቸት አድርጎ በወርካው ሥር ለተቀመጠው ለእግዚአብሔር መልአክ ወስዶ አቀረበለት። 20መልአኩም “ሥጋውንና እንጀራውን በዚህ አለት ላይ አስቀምጠህ መረቁን በላዩ አፍስስበት” ሲል አዘዘው፤ ጌዴዎንም እንደታዘዘው አደረገ። 21የእግዚአብሔር መልአክ ቀረብ ብሎ በያዘው በትር ጫፍ ሥጋውንና እንጀራውን ነካ፤ እሳትም ከአለቱ ላይ ተነሥቶ ሥጋውንና እንጀራውን በላ፤ ከዚያም በኋላ መልአኩ ተሰወረ።
22ጌዴዎን ያየው የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን በተገነዘበ ጊዜ “ልዑል እግዚአብሔር ሆይ! የአንተን መልአክ ፊት ለፊት አይቼአለሁ ወዮልኝ!” አለ።
23እግዚአብሔር ግን “ሰላም ለአንተ ይሁን፤ አይዞህ አትፍራ፤ አትሞትም” አለው። 24ጌዴዎንም በዚያ መሠዊያ ሠርቶ “እግዚአብሔር የሰላም አምላክ ነው” ብሎ ሰየመው፤ (ይህም መሠዊያ እስከ ዛሬ የአቢዔዜር ጐሣ ይዞታ በሆነችው በዖፍራ ቆሞ ይገኛል።)
25በዚያን ሌሊት እግዚአብሔር ጌዴዎንን እንዲህ አለው፤ “የአባትህን ኰርማና ሰባት ዓመት የሞላው አንድ ሌላ ኰርማ ውሰድ፤ አባትህ ለባዓል የሠራውን መሠዊያ አፍርስ፤ በአጠገቡ ያለውን ‘አሼራ’ ተብላ የምትጠራውን የሴት አምላክ ምስል ሰባብረህ ጣል፤ 26በዚያም የፍርስራሽ ጒብታ አናት ላይ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር በደንብ የተስተካከለ መሠዊያ ሥራ፤ ከዚያን በኋላ ሁለተኛውን ኰርማ ውሰድ፤ ሰባብረህ የጣልከውንም የአሼራን ምስል ስብርባሪ በማንደድ ኰርማውን በሙሉ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ አቅርብ።” 27ጌዴዎንም ከአገልጋዮቹ ዐሥሩን ወስዶ እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ቤተሰቡንና የከተማይቱን ኗሪዎች ከመፍራቱም የተነሣ ይህን ያደረገው ቀን ሳይሆን በሌሊት ጨለማ ለብሶ ነበር።
28በማግስቱ የከተማይቱ ኗሪዎች ማልደው በተነሡ ጊዜ ለባዓል የተሠራው መሠዊያ መፍረሱንና የአሼራም ምስል ተሰባብሮ መውደቁን አዩ፤ ከዚያም በተሠራው መሠዊያ ላይ ሁለተኛው ኰርማ ታርዶ የሚቃጠል መሥዋዕት ሆኖ መቅረቡን ተመለከቱ። 29እርስ በርሳቸውም “ይህን ያደረገ ማን ነው?” በማለት ተጠያየቁ፤ ብዙ ከተመራመሩም በኋላ ይህን ያደረገው የኢዮአስ ልጅ ጌዴዎን መሆኑን ደረሱበት፤ 30ከዚህም በኋላ ኢዮአስን “የባዓልን መሠዊያ ስላፈረሰና በአጠገቡ ያለውንም የአሼራን ምስል ሰባብሮ ስለ ጣለ፥ እንዲሞት ልጅህን ወዲህ አውጣልን!” አሉት።
31ኢዮአስ ግን በቊጣ ተነሣሥተው በእርሱ ላይ የመጡትን ሁሉ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ ለበዓል ትሟገታላችሁን? እርሱንስ ታድኑታላችሁን? ለእርሱ የሚሟገትለት ሁሉ እስከ ነገ ጧት ይገደላል፤ እርሱ አምላክ ከሆነ መሠዊያውን ካፈረሰው ሰው ጋር ለራሱ እስቲ ይሟገት!” 32ከዚህ በኋላ ኢዮአስ “ፈራርሶ የወደቀው የእርሱ መሠዊያ ስለ ሆነ እስቲ ይችል እንደ ሆነ ባዓል ራሱን ይከላከል፤” ለማለት ፈልጎ፥ ለጌዴዎን ይሩባዓል የሚል ስም አወጣለት።
33ከዚያም በኋላ ምድያማውያን፥ ዐማሌቃውያንና የምሥራቅ ሰዎች በአንድነት ተሰብስበው የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻገሩ፤ በኢይዝራኤል ሸለቆም ሰፈሩ። 34የእግዚአብሔር መንፈስ በጌዴዎን ላይ ወረደ፤ የአቢዔዜር ጐሣ ሰዎች ሁሉ እንዲከተሉት እነርሱን ለመጥራት እምቢልታ ነፋ፤ 35የምናሴን ነገድ ሁሉ መልእክት ልኮ ይከተሉት ዘንድ አስጠራቸው፤ እንዲሁም ወደ አሴር፥ ወደ ዛብሎንና ወደ ንፍታሌም ነገዶች መልእክተኞች ላከ፤ እነርሱም ከሌሎቹ ጋር ለመሰለፍ ወጡ።
36ከዚህ በኋላ ጌዴዎን እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፦ “እንደ ተናገርከው እስራኤልን በእኔ እጅ ታድን ዘንድ መርጠኸኛል። 37እነሆ! ስንዴ በምንወቃበት አውድማ ላይ የተባዘተ የበግ ጠጒር አስቀምጣለሁ፤ ነገ ጧት ሌላው ምድር ሁሉ ደረቅ ሆኖ በዚህ ጠጒር ባዘቶ ላይ ብቻ ጤዛ ከሆነ፥ እንደ ተናገርከው እስራኤልን ለማዳን የመረጥከኝ መሆኑን አረጋግጣለሁ።” 38ልክ እርሱ እንዳለውም ሆነለት፤ ጌዴዎን ጧት በማለዳ በተነሣ ጊዜ የበግ ጠጒሩን ባዘቶ ሲጨምቀው በአንድ መቅጃ የሚሞላ ውሃ ከውስጡ ወጣ። 39ቀጥሎም ጌዴዎን እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፤ “እባክህ አትቈጣኝ፤ እንደገና አንድ ጊዜ እንድናገር ፍቀድልኝ፤ ይኸውም በበግ ጠጒሩ ባዘቶ ላይ ሌላ ምልክት እንዲታይ ልጠይቅ፤ በዚህን ጊዜ የጠጒሩ ባዘቶ ደረቅ ሆኖ በዙሪያው ያለው ምድር እርጥብ እንዲሆን አድርግልኝ።” 40በዚያን ሌሊት እግዚአብሔር ያንኑ ምልክት አደረገ፤ በማግስቱ ጧት የጠጒሩ ባዘቶ ደረቅ ሆኖ በዙሪያው ያለው መሬት ግን በጤዛ ርሶ ተገኘ።
Currently Selected:
መጽሐፈ መሳፍንት 6: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997