የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መሳፍንት 9

9
አቤሜሌክ
1የጌዴዎን ልጅ አቤሜሌክ የእናቱ ዘመዶች ወደሚኖሩበት ወደ ሴኬም ከተማ ሄዶ ለእናቱ ወገኖች ሁሉ እንዲህ አላቸው፦ 2“ለሴኬም ሰዎች ሁሉ እንዲህ ብላችሁ ንገሩአቸው፦ ‘የጌዴዎን ሰባ ልጆች፥ ወይስ አንድ ሰው ብቻ ቢገዛችሁ ይሻላል? እኔ ደግሞ ለእናንተ የአጥንታችሁ ፍላጭ የሥጋችሁ ቊራጭ መሆኔን አስታውሱ።’ ” 3የእናቱም ዘመዶች እርሱን ወክለው ይህንኑ ለሴኬም ሰዎች ነገሩአቸው፤ የሴኬም ሰዎችም እርሱ ወንድማችን ነው ብለው አቤሜሌክን የመከተል ፍላጎት አደረባቸው። 4ከባዓልበሪት ቤት ሰባ ጥሬ ብር ወስደው ሰጡት፤ አቤሜሌክም በዚያ በሰባ ጥሬ ብር ዋልጌዎችንና ወሮበሎችን ቀጥሮ እንዲከተሉት አደረገ። 5ወደ አባቱ ቤት ወደ ዖፍራም ሄዶ የጌዴዎን ልጆች የሆኑትን ሰባውን ወንድሞቹን በአንድ ድንጋይ ላይ ዐረዳቸው፤ የጌዴዎን መጨረሻ ልጅ ኢዮአታም ግን ተደብቆ ስለ ነበር ከሞት ተረፈ፤ 6ከዚያን በኋላ የሴኬምና የቤትሚሎ ሕዝብ በአንድነት ተሰብስበው፥ በሴኬም ወደሚገኘው ወደተቀደሰው ወርካ ዛፍ ሄዱ፤ በዚያም አቤሜሌክን አነገሡ።
7ኢዮአታም ይህን ነገር በሰማ ጊዜ ወደ ገሪዛን ተራራ ጫፍ ላይ ወጥቶ እንዲህ በማለት ወደ እነርሱ ጮኸ፤ “እናንተ የሴኬም ሰዎች! እኔን ብታዳምጡኝ እግዚአብሔርም እናንተን ያዳምጣችኋል። 8ከዕለታት አንድ ቀን ዛፎች ተሰብስበው በላያቸው ንጉሥ ሊያነግሡ ሄዱ፤ የወይራንም ዛፍ ‘በእኛ ላይ ንገሥ’ አሉት። 9የወይራ ዛፍም ‘ለአማልክትና ለሰዎች ጠቃሚ የሆነውን ዘይቴን መስጠት ትቼ በዛፎች ላይ ልንገሥን?’ አላቸው። 10ከዚህ በኋላ ዛፎቹ የበለስን ዛፍ ‘መጥተህ በእኛ ላይ ንገሥ’ አሉት። 11የበለስ ዛፍ ግን ‘ጣፋጭና መልካም ፍሬዬን መስጠት ትቼ በዛፎች ላይ ለመንገሥ ልሂድን?’ አላቸው። 12ስለዚህ ዛፎቹ የወይን ተክልን ‘መጥተህ በእኛ ላይ ንገሥ’ አሉት። 13የወይን ተክሉ ግን ‘አማልክትንና ሰዎችን የሚያስደስተውን የወይን ጠጄን መስጠቴን አቁሜ በዛፎች ላይ ለመንገሥ ልሂድን?’ ሲል መለሰላቸው። 14ስለዚህ ዛፎች ሁሉ የእሾኽ ቊጥቋጦን ‘መጥተህ በእኛ ላይ ንገሥ’ አሉት። 15የእሾኽ ቊጥቋጦም ‘በእርግጥ ንጉሥ ልታደርጉኝ ከፈለጋችሁ፥ ኑና በጥላዬ ሥር ተጠለሉ፤ ይህን ባታደርጉ ከእሾኻማዎቹ ቅርንጫፎቼ እሳት ወጥቶ የሊባኖስ ዛፍን ያቃጥላል’ ሲል መለሰላቸው።”
16ኢዮአታምም ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አላቸው፤ “አቤሜሌክን ስታነግሡ በቅንነትና ተገቢ በሆነ መንገድ ነውን? ጌዴዎን ያደረገውን በማስታወስ ቤተሰቡን እንደሚገባ ረዳችሁለትን? 17አባቴ ለእናንተ እንደ ተዋጋና እናንተንም ከምድያማውያን እጅ ለማዳን ሲል ሕይወቱን በአደጋ ላይ ጥሎ እንደ ነበረ አስታውሱ፤ 18ዛሬ ግን እናንተ በአባቴ ቤተሰብ ላይ በጠላትነት ተነሣችሁ፤ ልጆቹን ገደላችሁ፤ ሰባውንም በአንድ ድንጋይ ላይ ዐረዳችሁ፤ ይህንንም ያደረጋችኹት ጌዴዎን ከገረዱ የወለደው አቤሜሌክ የእናንተ ዘመድ ስለ ሆነ ነው፤ እርሱንም የሴኬም ንጉሥ አደረጋችሁት። 19እንግዲህ ዛሬ ለጌዴዎንና ለቤተሰቡ ያደረጋችኹት በቅንነትና ተገቢ በሆነ መንገድ ከሆነ ከአቤሜሌክ ጋር ደስ ይበላችሁ፤ እርሱም ከእናንተ ጋር ደስ ይበለው፤ 20ይህ ካልሆነ ግን ከአቤሜሌክ እሳት ወጥቶ የሴኬምንና የቤትሚሎንን ሰዎች ይብላ፤ እንዲሁም ከሴኬምና ከቤትሚሎ እሳት ወጥቶ አቤሜሌክን ይብላ።” 21ኢዮአታም ይህን ከተናገረ በኋላ ወንድሙን አቤሜሌክን ስለ ፈራ ሸሽቶ ወደ በኤር ሄዶ እዚያ ተቀመጠ።
አቤሜሌክና የሴኬም ሰዎች
22አቤሜሌክም በእስራኤል ላይ ሦስት ዓመት ነገሠ፤ 23ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር በአቤሜሌክና በሴኬም ሰዎች መካከል ርኩስ መንፈስን ላከ፤ ስለዚህም የሴኬም ሰዎች በእርሱ ላይ ዐመፁበት። 24ይህም የሆነው ወንድማቸው አቤሜሌክ የገደላቸውን የጌዴዎንን ሰባ ልጆች ደምና እነርሱንም እንዲገድል ያበረታቱትን የሴኬምን ሰዎች ለመበቀል ነው። 25የሴኬም ኗሪዎች በአቤሜሌክ ላይ በጠላትነት ተነሥተው ጥቂት ሰዎችን መርጠው በተራሮች ጫፍ ላይ ሸመቁ፤ በመንገዳቸው የሚያልፈውን ሰው ሁሉ ዘረፉ፤ አቤሜሌክም ይህን ሁሉ ሰማ። 26ከዚህ በኋላ የዔቤድ ልጅ ጋዓል ከወንድሞቹ ጋር ወደ ሴኬም መጣ፤ የሴኬምም ሰዎች እምነታቸውን በእርሱ ላይ ጣሉ። 27ሁሉም ወደ ወይን ተክሎቻቸው ወጥተው የወይን ፍሬ ለቀሙ፤ የወይን ጠጅ ጠምቀው ትልቅ በዓል አደረጉ፤ ወደ አምላካቸውም መቅደስ ገብተው በዚያ እየበሉና እየጠጡ ስለ አቤሜሌክ በማፌዝ ተናገሩ። 28የዓቤድ ልጅ ጋዓልም እንዲህ አለ፦ “አቤሜሌክ ማን ነው? እኛ የሴኬም ሰዎች ለእርሱ የምንገዛው ለምንድነው? የጌዴዎን ልጅና የእርሱ የጦር መሪ ዜቡር የሐሞርን አባት ሴኬምን ያገለገሉ አይደሉምን? ለምን ለእርሱ እንታዘዛለን? ይልቅስ የጐሣችሁ መሥራች ለሆነው ለሴኬም አባት ለሐሞር ታማኞች ሁኑ። 29ይህን ሕዝብ የምመራው እኔ በሆንኩ ኖሮ! አቤሜሌክን ወዲያ አስወግደው ነበር፤ ደግሞም ‘ሠራዊትህን በማጠንከር ወጥተህ ተዋጋ!’ ብዬ እነግረው ነበር።”
30የከተማይቱ ገዢ ዘቡል የዔቤድ ልጅ ጋዓል የተናገረውን በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጣ፤ 31በአሩማ ወዳለውም ወደ አቤሜሌክ መልእክተኞችን ልኮ እንዲህ ብለው እንዲነግሩት አሳሰባቸው፥ “የዔቤድ ልጅ ጋዓል ከወንድሞቹ ጋር ወደ ሴኬም መጥቶአል፤ በአንተም ላይ የከተማውን ሕዝብ አነሣሥቶአል። 32እንግዲህ አንተና ተከታዮችህ በሌሊት ከዚያ ተነሥታችሁ በመስክ ውስጥ ደፈጣ አድርጉ፤ 33ነገ ጧትም ፀሐይ ስትወጣ ተነሥታችሁ በከተማይቱ ላይ በድንገት አደጋ ጣሉ፤ ጋዓልና ተከታዮቹ እናንተን ለመውጋት ሲወጡም በተቻላችሁ መጠን በብርቱ ምቱአቸው።”
34ስለዚህ አቤሜሌክና ተከታዮቹ ሁሉ በሌሊት ተነሥተው ከሴኬም ውጪ በአራት ወገን ተከፍለው ደፈጣ አደረጉ፤ 35አቤሜሌክና ተከታዮቹ የዔቤድ ልጅ ጋዓል ወጥቶ በከተማይቱ ቅጽር በር መቆሙን ባዩ ጊዜ ከሸመቁባቸው ስፍራዎች ወጡ፤ 36ጋዓልም እነርሱን አይቶ ዘቡልን “ተመልከት! ሰዎች ከተራራው ጫፍ ላይ እየወረዱ ነው!” አለው።
ዘቡልም “እነርሱ በተራሮች ላይ የሚታዩ ጥላዎች እንጂ ሰዎች አይደሉም” ሲል መለሰለት።
37ቀጥሎም ጋዓል “ተመልከት! ከከፍተኛ ቦታ መካከል ሰዎች ቊልቊል በመውረድ ላይ ናቸው፤ አንዱ ቡድን የአስማተኞች የወርካ ዛፍ በሚባለው መንገድ እየመጣ ነው!” አለ።
38ከዚህ በኋላ ዘቡል እንዲህ አለው፤ “ያ ሁሉ ፉከራህ አሁን የት ደረሰ? ‘አቤሜሌክ የተባለውን ሰው የምናገለግለው ለምንድን ነው?’ ብለህ የጠየቅህ አንተ አልነበርክምን? በማፌዝ ስታላግጥባቸው የነበርከው ሰዎች እነሆ፥ እነዚህ ናቸው፤ በል ወጥተህ ጦርነት ግጠማቸው፤” 39ጋዓል የሴኬምን ሰዎች እየመራ ወጥቶ አቤሜሌክን ጦርነት ገጠመው፤ 40ጋዓል ሸሸ፤ አቤሜሌክም አሳደደው፤ በከተማይቱ ቅጽር በር ላይ ሳይቀር ብዙዎች ቈሰሉ፤ 41አቤሜሌክም መኖሪያውን በአሩማ አደረገ፤ ዘቡል ግን ጋዓልንና ወንድሞቹን ከሴኬም እያባረረ አስወጣቸው፤ ከዚያም በኋላ እዚያ ለመኖር አልቻሉም።
42በማግስቱ የሴኬም ሕዝብ ወደየእርሻቸው መሄዳቸውን አቤሜሌክ ሰማ፤ 43የእርሱ ተከታዮች የሆኑትን ሰዎች ወስዶ በሦስት ወገን በመክፈል በየመስኩ ሸምቀው እንዲጠባበቁ አደረገ፤ ሴኬማውያንንም ከከተማ ሲወጡ ባየ ጊዜ እነርሱን ከሸመቀበት ቦታ ወጥቶ ገደላቸው፤ 44አቤሜሌክና ከእርሱ ጋር የተመደበው ቡድን የከተማይቱን ቅጽር በር ለመጠበቅ ተጣድፈው ወጥተው በከተማው መግቢያ በር ላይ ቆሙ፤ የቀሩት ሁለቱ ቡድኖች በመስኩ በተገኙት ላይ አደጋ ጥለው ፈጁአቸው። 45ውጊያውም ቀኑን ሙሉ ቀጥሎ ዋለ፤ አቤሜሌክ ከተማይቱን ይዞ ሕዝብዋን ሁሉ ገደለ፤ ከተማይቱን አፈራረሰ፤ በምድሪቱም ላይ ጨው ዘራባት።
46በሴኬም ግንብ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ይህን በሰሙ ጊዜ ባዓልበሪት በሚመለክበት ቤት በሚገኘው ምሽግ ውስጥ ገቡ። 47አቤሜሌክም በሴኬም መሰብሰባቸውን ሰማ። 48ስለዚህም ከተከታዮቹ ጋር ወደ ጻልሞን ተራራ ወጣ፤ ከዚያም መጥረቢያ ወስዶ ከዛፍ ላይ እንጨት በመቊረጥ በትከሻው ተሸከመ፤ ተከታዮቹም በፍጥነት እርሱ እንዳደረገው ያደርጉ ዘንድ ነገራቸው። 49እያንዳንዱም ሰው ከዛፍ እንጨት ቈረጠ፤ አቤሜሌክንም ተከትለው ያን እንጨት ምሽጉን በማስደገፍ ከመሩት፤ ሰዎቹ በውስጡ እንዳሉም በእሳት አቃጠሉት፤ ስለዚህም በምሽጉ ውስጥ የነበሩት ሰዎች ሁሉ ሞቱ፤ የወንዶቹና የሴቶቹ ቊጥር አንድ ሺህ ያኽል ነበር።
50ከዚህ በኋላ አቤሜሌክ ወደ ቶቤጽ ሄደ፤ ከተማይቱንም ከቦ ያዛት፤ 51በከተማይቱ ውስጥ አንድ ትልቅ የከተማ መጠበቂያ ግንብ ስለ ነበረ፥ መሪዎቹ ሳይቀሩ እያንዳንዱ ወንድም ሆነ ሴት ሮጦ ወደ እርሱ ገባ፤ በሩንም ዘግተው ወደ ጣራው ወጡ፤ 52አቤሜሌክ እየተዋጋ ወደ ግንቡ በደረሰ ጊዜ በእሳት ለማያያዝ ወደ በሩ ቀረበ። 53ነገር ግን አንዲት ሴት በራሱ ላይ የወፍጮ ድንጋይ ናዳ በመጣል አናቱን ፈጠፈጠችው። #2ሳሙ. 11፥21። 54እርሱም የጦር መሣሪያ አንጋቹን ወጣት በፍጥነት በመጥራት፥ “ሰይፍህን መዘህ ግደለኝ፤ ሴት ገደለችው እንድባል አልፈልግም” ሲል አዘዘው። ስለዚህ ወጣቱ በሰይፍ መትቶ ገደለው። 55እስራኤላውያን አቤሜሌክ መሞቱን ባዩ ጊዜ ሁሉም ወደየቤታቸው ሄዱ።
56በዚህ ዐይነት አቤሜሌክ ሰባ ወንድሞቹን በመግደል በአባቱ ላይ በፈጸመው በደል እግዚአብሔር ፍዳውን ከፈለው፤ 57እንዲሁም እግዚአብሔር የሴኬም ሰዎች ስለ ክፋታቸው ዋጋ የሆነውን መከራ እንዲቀበሉ አደረገ፤ በዚህ አኳኋን የጌዴዎን ልጅ ኢዮአታም በረገማቸው ጊዜ በእነርሱ ላይ እንደሚደርስባቸው የተናገረው ሁሉ ተፈጸመ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ