መጽሐፈ ኢያሱ 13
13
መወረስ የነበረበት ገና ያልተያዘ ምድር
1እነሆ፥ ኢያሱ በዕድሜ እየገፋ ስለ ሄደ አረጀ፤ ስለዚህም እግዚአብሔር እንዲህ አለው፤ “እነሆ፥ አንተ ሸምግለሃል፤ ዕድሜህም ገፍቶአል፤ ገና ብዙ ያልተያዙ ቦታዎች አሉ። 2ገና ያልተያዙትም እነዚህ ናቸው፦ የፍልስጥኤምና የገሹር ግዛት በሙሉ፥ 3እነዚህም ከግብጽ በስተ ምሥራቅ ካለው ከሺሆን ወንዝ ጀምሮ ወደ ሰሜን እስከ ኤክሮን ድንበር ድረስ ያለው ነው። ይህም በአጠቃላይ ከነዓን ተብሎ ይጠራል። እርሱም የአምስቱ የፍልስጥኤም ማለት የጋዛ፥ የአሽዶድ፥ የአስቀሎና፥ የጋትና የኤክሮን ነገሥታት ግዛት ነው። ሌሎች ያልተያዙ ደግሞ በደቡብ በኩል ያለው የአቢብ ግዛት ነው። 4በሌላም በኩል የሲዶናውያን ይዞታ የሆነው የከነዓን አገር መዓራ ተብሎ የሚጠራውን ሁሉ ጨምሮ በአሞራውያን ጠረፍ እስከ አፌቅ ድረስ የሚገኘው፥ 5የጌባላውያን ምድርና ከምሥራቅ በአርሞንኤም ተራራ ደቡብ ከሚገኘው ከባዓልጋድ ተነሥቶ እስከ ሐማት መተላለፊያ ያለው መላው ሊባኖስ ገና አልተያዘም። 6ከሊባኖስ እስከ ሚስረፎትማይም ድረስ በተራራማው አገር የሚኖሩ ነዋሪዎች፥ ማለት ሲዶናውያንን ሁሉ፥ እኔ ራሴ ከእስራኤላውያን ፊት አባርራቸዋለሁ፤ አንተ ግን እኔ እንዳዘዝኩህ ምድሪቱን ለእስራኤላውያን ርስት አድርገህ አከፋፍል። #ዘኍ. 33፥54። 7ይህንንም ምድር ርስት አድርገህ የምታካፍለው ለዘጠኙ ነገዶችና ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ነው።”
ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተምሥራቅ ያለው ግዛት አከፋፈል
8የሮቤልና የጋድ ነገዶች እንዲሁም የምናሴ ነገድ እኩሌታ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ በርስትነት የሰጣቸውን ምድር ቀደም ብለው ተረክበዋል። ይህም ምድር የሚገኘው በስተምሥራቅ ከዮርዳኖስ ወንዝ ማዶ ነው። #ዘኍ. 32፥33፤ ዘዳ. 3፥12። 9ግዛታቸውም ከአርኖን ሸለቆ ዳርቻ ከሆነው ከዓሮዔር ተነሥቶ እንዲሁም በሸለቆው መካከል ካለው ከተማ ከሜዴባ ሜዳ እስከ ዲቦን ድረስ ይደርሳል። 10በሌላም በኩል በሓሴቦን እስከ አሞናውያን ድንበር ድረስ የነገሠውን የአሞራውያን ንጉሥ የሲሖንን ከተሞች ሁሉ ያጠቃልላል። 11እርሱም ገለዓድን፥ የገሹርንና የማዕካን አውራጃዎችና የአርሞንኤምን ተራራ በሙሉ እንዲሁም እስከ ሳለካ ድረስ ያለውን ባሳንን ይጨምራል። 12ከራፋይማውያን ተራፊ የነበረውን በአስታሮትና በኤድራይ የነገሠውን የባሳንን ንጉሥ የዖግን መንግሥት ሁሉ ይጨምራል። ሙሴም እነዚህን ድል አድርጎ አስወጣቸው። 13ይሁን እንጂ እስራኤላውያን የገሹርንና የማዕካን ሕዝብ አላስወጡም፤ ነገር ግን እነርሱ እስከ አሁን በእስራኤላውያን መካከል ይኖራሉ።
14ሙሴ ለሌዊ ነገድ የርስት ድርሻ አልሰጠም፤ እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር በመሠዊያ ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት ሆኖ ከሚቀርበው መባ የሚያገኙት ድርሻ እንደ ርስት ሆኖ ተመድቦላቸዋል። #ዘዳ. 18፥1።
ለሮቤል ርስት ሆኖ የተመደበ ምድር
15ሙሴ ለሮቤል ነገድ በየወገናቸው ርስት ሰጣቸው፤ 16ግዛታቸውም በአርኖን ሸለቆ ዳርቻ እስከሚገኘው እስከ ዓሮዔርና በዚያም ሸለቆ መካከል እስካለችው ከተማ አልፎ በሜደባ ዙሪያ ያለውን ሜዳማ አገር ሁሉ ያጠቃልላል፤ 17እንዲሁም ሐሴቦንን፥ በደጋማ አገር ያሉትን ከተሞች፥ ዲቦን፥ ባሞትበዓል፥ ቤትበዓልመዖን፥ 18ያሀጽ፥ ቀዴሞት፥ ሜፋዓት፥ 19ቂርያታይም፥ ሲበማ፥ በኮረብታማው ሸለቆ የሚገኘው ጼሬትሻሐር፥ 20ቤትፐዖር፥ ከፒስጋ ተራራ በታች ያለው ረባዳ ምድርና ቤትየሺሞት ተብለው የሚጠሩትን ሁሉ ይጨምራል። 21በደጋማው አገር የሚገኙትን ከተሞችና መኖሪያውን በሐሴቦን አድርጎ ይገዛ የነበረውን የአሞራውያን ንጉሥ የሲሖንን ግዛት ሁሉ ይጨምራል። ሙሴም ንጉሥ ሲሖንንና የምድያም መሪዎች የነበሩትን፥ ኤዊን፥ ሬቄምን፥ ጹርን፥ ሑርንና ሬባዕን ድል ነሣ፤ እነዚህ ሁሉ ምድሪቱን የሚያስተዳድሩት የንጉሥ ሲሖን ገባሮች በመሆን ነበር። 22የእስራኤል ሕዝብ ከገደሉአቸውም መካከል አንዱ ጠንቋይ እየተባለ ይጠራ የነበረው የቢዖር ልጅ በለዓም ነበር። 23በምዕራብ በኩል የዮርዳኖስም ወንዝ ለሮቤል ነገድ የርስቱ ወሰን ነበር፤ እንግዲህ ለሮቤል ነገድ ቤተሰቦች ርስት ሆነው የተሰጡአቸው ከተሞችና መንደሮች እነዚህ ነበሩ።
ለጋድ ርስት ሆኖ የተመደበ ምድር
24ሙሴ ለጋድ ነገድ በየቤተሰባቸው ርስት ሰጠ፤ 25የእነርሱም ግዛት ያዕዜርንና በገለዓድ የሚገኙትን ከተሞች ሁሉ የዐሞንን ምድር እኩሌታ ጨምሮ ከራባ በስተምሥራቅ እስከምትገኘው እስከ ዓሮዔር ይደርሳል። 26የምድራቸውም ስፋት ከሐሴቦን ተነሥቶ እስከ ራማት ምጽጳና እስከ ቤጦኒም እንዲሁም ከማሕናይም ተነሥቶ እስከ ሎዴባር ድንበር ይደርሳል፤ 27ከዮርዳኖስ ሸለቆ በተለይ የሐሴቦን ንጉሥ የሲሖን መንግሥት ቅሬታ የሆኑትን ቤትሐራም፥ ቤትኒምራ፥ ሱኮትና ጻፎን ተብለው የሚጠሩትን ጭምር ያጠቃልላል፤ በምዕራብ በኩል የሚዋሰናቸውም የዮርዳኖስ ወንዝ ሲሆን፥ በሰሜን እስከ ገሊላ ባሕር ይደርሳል። 28እንግዲህ ለጋድ ነገድ ቤተሰቦች ርስት ሆነው የተሰጡአቸው ከተሞችና መንደሮች እነዚህ ነበሩ።
በምሥራቅ በኩል ለሚኖረው ለምናሴ ነገድ እኩሌታ የተመደበ ምድር
29ሙሴ ለግማሹ የምናሴ ነገድ ርስት ሰጠ፤ የሰጣቸውም እንደየቤተሰባቸው በማከፋፈል ነበር። 30ግዛታቸውም ማሕናይምንና ባሳንን ሁሉ ያጠቃልላል፤ ይህም ባሳን መላውን የባሳን ንጉሥ የዖግን ግዛት እንዲሁም በባሳን በተለይ ያኢር ተብላ በምትጠራው ስፍራ የሚገኙትን ሥልሳ ከተሞች ሁሉ ይጨምራል፤ 31እንዲሁም የገለዓድ እኩሌታ፥ አስታሮት እና ኤድራይ እነርሱም በባሳን የንጉሥ ዖግ ከተሞች የነበሩት ይህም ከምናሴ ነገድ ለእኩሌቶቹ የማኪር ልጆች እንደየወገናቸው ተከፋፈሉት።
32በሞአብ ሜዳ በነበረበት ጊዜ ሙሴ በኢያሪኮና በዮርዳኖስ ምሥራቅ ወንዝ ያለውን ምድር ያከፋፈለው በዚህ ዐይነት ነበር። 33ይህ ሁሉ ሲሆን፥ ሙሴ ለሌዊ ነገድ የሚሰጥ የርስት ድርሻ አልመደበም፤ የእነርሱ ርስት የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ስለ ሆነ፥ ድርሻቸውን የሚያገኙት ለእግዚአብሔር ከሚቀርበው መሥዋዕት መሆኑን ነግሮአቸዋል። #ዘኍ. 18፥20፤ ዘዳ. 18፥2።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢያሱ 13: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997