የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ኢያሱ 14

14
ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተምዕራብ ያለው ምድር አከፋፈል
1ካህኑ አልዓዛር፥ የነዌ ልጅ ኢያሱና የእስራኤል ነገድ የቤተሰብ አለቆች በከነዓን ምድር ለእስራኤላውያን አከፋፍለዋቸው የተቀበሉት ርስት ይህ ነው። 2እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተምዕራብ ያለው ግዛት በሙሉ ለዘጠኙ ነገድ ተኩል በዕጣ ተከፈለ። #ዘኍ. 26፥52-56፤ 34፥13። 3ሙሴ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ያለውን ምድር ለሁለት ተኩል ነገዶች ርስት አድርጎ ሰጥቶአቸው ነበር፤ ለሌዋውያን ግን በእነርሱ መካከል ርስት አልሰጣቸውም። #ዘኍ. 32፥33፤ 34፥14-15፤ ዘዳ. 3፥12-17። 4የዮሴፍ ልጆች ምናሴና ኤፍሬም ሁለት ነገዶች ነበሩ፤ ለሌዋውያንም በምድሪቱ ለመኖሪያቸው የሚሆኑ ከተሞችና ለከብቶቻቸው ማሰማሪያ የሚሆን መሬት በቀር የርስት ድርሻ አልተሰጣቸውም፤ 5እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት እስራኤላውያን ምድሪቱን ተካፈሉ።
ኬብሮን ለካሌብ መሰጠቱ
6አንድ ቀን ከይሁዳ ነገድ የሆኑ ሰዎች በጌልገላ ወደ ኢያሱ ቀረቡ፤ ከእነርሱ አንዱ የቀኒዛዊው የይፉኔ ልጅ ካሌብ እንዲህ አለው፦ “በቃዴስ በርኔ በነበርንበት ጊዜ እግዚአብሔር በአገልጋዩ በሙሴ አማካይነት ስለ አንተና ስለ እኔ የተናገረውን ታውቃለህ፤ #ዘኍ. 14፥30። 7የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ የዚህችን ምድር ሁኔታ ለማጥናት ከቃዴስ በርኔ በላከኝ ጊዜ የአርባ ዓመት ጐልማሳ ነበርኩ፤ ለእርሱም አስተማማኝ የሆነ ማስረጃ አቅርቤአለሁ፤ #ዘኍ. 13፥1-30። 8ከእኔ ጋር ሄደው የነበሩ ሰዎች ግን የሕዝቡ ልብ በፍርሃት እንዲቀልጥ አደረጉ፤ እኔ ግን ለአምላኬ ለእግዚአብሔር በታማኝነት ታዛዥ ሆኛለሁ፤ 9ሙሴ፦ ‘አምላኬን እግዚአብሔርን በሙሉ ልብህ ስለ ተከተልከው የረገጥከው ምድር ለአንተና ለልጆችህ የዘለዓለም ርስት ይሆናል’ ” ብሎ በዚያን ቀን በመሐላ ቃል ገብቶልኝ ነበር። #ዘኍ. 14፥24። 10እስራኤል በምድረ በዳ በጉዞ ላይ ሆኖ ሳለ እግዚአብሔር ሙሴን ይህን ቃል ከተናገረበት ቀን ጀምሮ አሁን እንደምታየኝ እግዚአብሔር እንዳለው ይህን አርባ አምስት ዓመት ጠብቆ አኑሮኛል፤ እነሆ አሁን እኔ ሰማኒያ አምስት ዓመት ሆነኝ። 11ሙሴ በላከኝ ጊዜ እንደ ነበርኩት አሁንም እንደዚያው ብርቱ ነኝ፤ በዚያን ጊዜ ለመዋጋት ለመውጣትና ለመግባት የነበረኝ ጒልበት አሁንም እንደዚያው ነው። 12አሁን እንግዲህ እግዚአብሔር በዚያን ቀን በሰጠኝ ተስፋ መሠረት ይህን ኮረብታማ አገር ስጠኝ፤ ዐናቃውያን ከታላላቅ የተመሸጉ ከተሞች ጋር እንደ ነበሩ በዚያን ቀን ሰምተሃል፤ እግዚአብሔር እንዳለ እርሱ ከእኔ ጋር ሆኖ አሳድዳቸዋለሁ።
13ኢያሱም የይፉኔን ልጅ ካሌብን ባረከው፤ ኬብሮንንም ርስት አድርጎ ሰጠው፤ 14ስለዚህም እርሱ የእስራኤላውያን አምላክ እግዚአብሔርን በሙሉ ልቡ ስለ ተከተለ ኬብሮን እስከ አሁን ድረስ የቀኒዛዊው የይፉኔ ልጅ የካሌብ ዘሮች ይዞታ ናት፤ 15የኬብሮንም ስም አስቀድሞ ቂርያት አርባዕ ነበር፤ ይህም አርባዕ ከዐናቃውያን መካከል ታላቅ ሰው ነበር።
ምድሪቱም ከጦርነት ዐረፈች።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ