መጽሐፈ ኢያሱ 17
17
በዮርዳኖስ ምዕራብ የሰፈረው የምናሴ ነገድ እኩሌታ
1ይህ የዮሴፍ በኲር ልጅ የነበረው የምናሴ ነገድ ድርሻ የሚከተለው ነው። የምናሴ በኲር ልጅ የገለዓድ አባት ማኪር የጦር ጀግና ስለ ነበረ ገለዓድና ባሳን በርስትነት ተሰጠው። 2ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ ያለው ምድር ለቀሩት ለምናሴ ልጆች በየወገናቸው ተሰጠ፤ እነርሱም አቢዔዜር፥ ሔሌቅ፥ አሥሪኤል፥ ሼኬም፥ ሔፌርና ሸሚዳዕ የተባሉት ናቸው፤ የዮሴፍ ልጅ የምናሴ ዘሮች በየወገናቸው የሚከተሉት ናቸው። 3ጸለጰሐድ የሔፌር ልጅ፥ ሔፌር የገለዓድ ልጅ፥ ገለዓድ የማኪር ልጅ፥ ማኪርም የምናሴ ልጅ ነው፤ ታዲያ ይህ ጸለጰሐድ ሴቶች እንጂ ወንዶች ልጆች አልነበሩትም፤ አምስቱ ሴቶች ልጆቹም ማሕላ፥ ኖዓ፥ ሖግላ፥ ሚልካ እና ቲርጻ ተብለው ይጠሩ ነበር። 4እነርሱም ወደ ካህኑ አልዓዛር፥ ወደ ነዌ ልጅ ኢያሱና ወደ መሪዎቹ ቀርበው “እንደ ወንዶች ዘመዶቻችን የርስት ድርሻ እንዲሰጠን እግዚአብሔር ሙሴን አዞታል” አሉአቸው። ስለዚህም እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ለእነርሱ ከወንዶች ዘመዶቻቸው ጋር የርስት ድርሻ ተሰጣቸው፤ #ዘኍ. 27፥1-7። 5ምናሴ በዮርዳኖስ ወንዝ በስተምሥራቅ ከሚገኙት ከገለዓድና ከባሳን ጋር በተጨማሪ ዐሥር ዕጣ እንዲደርሰው ተደርጎአል። 6ሴቶች ዘሮቹ እንደ ወንዶች ዘሮቹ የርስት ድርሻ ስለ ተቀበሉ የገለዓድም ምድር ለቀሩት ለምናሴ ዘሮች ተሰጠ።
7የምናሴ የርስት ይዞታ ከአሴር ተነሥቶ በሴኬም በስተ ምሥራቅ እስከምትገኘው እስከ ሚክመታት ይደርስ ነበር፤ ድንበሩም ወደ ደቡብ በማለፍ የዔንታፑዓሕን ሕዝብ ይጨምራል፤ 8በታፑሐ ዙሪያ የሚገኘውም ምድር ለምናሴ ተሰጠ፤ በድንበር ላይ የምትገኘው ትንሽዋ የታፑሐ ከተማ ግን የኤፍሬም ዘሮች ይዞታ ነበረች። 9ድንበሩም ከዚያ ተነሥቶ እስከ ቃና ወንዝ ይደርሳል፤ ከወንዙ በስተ ደቡብ የሚገኙት ከተሞች ምንም እንኳ በምናሴ ግዛት ክልል ውስጥ ቢሆኑ የኤፍሬም ይዞታዎች ነበሩ፤ የምናሴ ድንበር በሰሜን በኩል ከወንዙ እየተዋሰነ መጨረሻው የሜድትራኒያን ባሕር ነበር፤ 10ከዚህም የተነሣ የሁለቱም ምዕራባዊ ወሰን የሜድትራኒያን ባሕር ሆኖ ኤፍሬም በደቡብ፥ ምናሴ በሰሜን እንዲሰፍሩ ተደረገ፤ አሴር በሰሜን ይሳኮር ደግሞ በምሥራቅ ሰፈሩ። 11በይሳኮርና በአሴር ግዛት ውስጥ ምናሴ ቤትሼንና መንደሮችዋ፥ ይብልዓምና መንደሮችዋ፥ የዶር ኑዋሪዎችና መንደሮችዋ የዕንዶር ኑዋሪዎችና መንደሮችዋ፥ የታዕናክ ኑዋሪዎችና መንደሮችዋ፥ የመጊዶና ኑዋሪዎችና መንደሮችዋ፥ (በሦስተኛው ተራ ዶር የተባለው ናፋት ዶርም ይባላል)። እነዚህም ሁሉ የምናሴ ይዞታዎች ሆኑ። 12ይሁን እንጂ የምናሴ ልጆች ሕዝቡን አባረው እነዚያን ከተሞች ለመያዝ አልቻሉም፤ ስለዚህም ከነዓናውያን በዚያ መኖርን ቀጠሉ፤ 13እስራኤላውያን በኀይል እየበረቱ ቢሄዱም እንኳ ከነዓናውያንን ሁሉ አላባረሩአቸውም፤ ነገር ግን የጒልበት ሥራ እንዲሠሩላቸው ያስገድዱአቸው ነበር። #መሳ. 1፥27-28።
ኤፍሬምና የምናሴ ነገድ እኩሌታ ተጨማሪ መሬት መጠየቃቸው
14የዮሴፍ ነገድ ወደ ኢያሱ ቀርበው “እግዚአብሔር ባርኮን ለበዛነው ለእኛ እንዴት አንድ ዕጣ ብቻ ሰጠኸን?” ብለው ጠየቁት። 15ኢያሱም መልሶ “ብዙዎች ከሆናችሁና ኮረብታማይቱ የኤፍሬም ምድር ትንሽ ከሆነችባችሁ፥ ፈሪዛውያንና ረፋያውያን ወደሚኖሩበት ምድር ሄዳችሁ ጫካውን መንጥሩ” አላቸው። 16እነርሱም “ኮረብታማይቱ አገር ለእኛ በቂ አይደለችም፤ ከዚህም ሁሉ ጋር በኢይዝራኤል ሸለቆ በቤትሻንና በዙሪያዋ ባሉት ታናናሽ ከተሞችና በሜዳማው አገር የሚኖሩ ከነዓናውያን ብዙ የብረት ሠረገሎች አሉአቸው” ሲሉ መለሱ።
17ኢያሱም ለኤፍሬምና በዮርዳኖስ ምዕራብ ለሰፈረው ለምናሴ ነገዶች እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ በእውነት ብዙዎች ናችሁ፤ በኀይልም ብርቱዎች ናችሁ፤ አንድ ዕጣ ብቻ ሊኖራችሁ አይገባም፤ 18ስለዚህ ኮረብታማው አገር የእናንተ ይሆናል፤ ጫካም ቢሆን መንጥራችሁ ዳር እስከ ዳር የራሳችሁ ርስት አድርጉት፤ ስለ ከነዓናውያን ጉዳይ የሆነ እንደሆን ምንም የብረት ሠረገሎች ቢኖራቸውና ምንም ብርቱዎች ቢሆኑ ነቃቅላችሁ ልታባርሩአቸው ትችላላችሁ።”
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢያሱ 17: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997