መጽሐፈ ኢያሱ 18
18
የቀሪው ምድር አከፋፈል
1ድል አድርገው ምድሪቱን ከያዙ በኋላ መላው የእስራኤል ሕዝብ በሴሎ ተሰብስበው እግዚአብሔር የሚመለክበትን ድንኳን ተከሉ። 2ከእስራኤልም ሕዝብ መካከል ገና የርስት ድርሻ ያላገኙ ሰባት ነገዶች ነበሩ፤ 3ስለዚህም ኢያሱ ለእስራኤላውያን እንዲህ አለ፦ “ገብታችሁ የቀድሞ አባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር የሰጣችሁን ምድር ሳትወርሱ የምትቈዩት እስከ መቼ ነው? 4ከእያንዳንዱ ነገድ ሦስት ሦስት ሰዎች ምረጡልኝ፤ እኔም እያንዳንዱ ነገድ ማግኘት የሚገባውን የርስት ድርሻ ለማወቅ የምድሪቱን ሁኔታ አጥንተው እንዲመዘግቡ በመላ አገሪቱ እልካቸዋለሁ፤ ከዚያም በኋላ ተመልሰው ወደ እኔ ይመጣሉ። 5እነርሱም የሚያጠኑት ምድር ለሰባቱ ነገድ ይከፋፈላል፤ ይሁዳ በደቡብ በኩል፥ ዮሴፍም በሰሜን በኩል የተመደበላቸውን የርስት ድርሻ ይዘው ይኖራሉ፤ 6የእነዚህን ሰባት ክፍያዎች የሚገልጠውንም ማስረጃ በጽሑፍ አድርጋችሁ አምጡልኝ፤ አምላካችንን እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ዕጣ እጥልላችኋለሁ። 7ይሁን እንጂ የሌዋውያን ድርሻ ካህናት ሆነው እግዚአብሔርን ማገልገል ስለ ሆነ እነርሱ ከሌሎቻችሁ ጋር የርስት ድርሻ አይኖራቸውም፤ የሮቤልና የጋድ እንዲሁም የምናሴ ነገድ እኩሌታ ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምሥራቅ በኩል የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ የሰጣቸውን ርስት አስቀድመው ወርሰዋል።”
8ሰዎቹም የምድሪቱን ሁኔታ ለማጥናት ከመሄዳቸው በፊት ኢያሱ፥ “ወደ ምድሪቱ ሁሉ ሂዱ፤ አቀማመጥዋንም አጥንታችሁ መዝግቡ፤ ወደ እኔም ተመልሳችሁ ኑ፤ እኔም በዚህ በሴሎ ስለ እናንተ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ዕጣ እጥልላችኋለሁ” የሚል መመሪያ ሰጣቸው፤ 9ሰዎቹም በአገሪቱ በመላ ተዘዋወሩ፤ ከተሞቹንም ሁሉ መዝግበው ምድሪቱ ለሰባት ነገድ እንዴት እንደምትከፈል በጽሑፍ ገለጡ፤ ከዚህም በኋላ ኢያሱ ወዳለበት ወደ ሴሎ ተመልሰው መጡ፤ 10ኢያሱም እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ዕጣ አወጣላቸው፤ ለቀሩትም ለእስራኤል ነገዶች ለእያንዳንዳቸው ተመጣጣኝ የሆነ የርስት ድርሻ ተመደበላቸው።
ለብንያም ርስት ሆኖ የተመደበ ምድር
11የብንያም ነገድ የርስት ድርሻ በየወገናቸው ወጣ፤ ለእነርሱም የተመደበላቸው ርስት የሚገኘው በይሁዳና በዮሴፍ ነገዶች መካከል ነበር፤ 12በሰሜን በኩል የሚገኘውም ድንበራቸው ከዮርዳኖስ ወንዝ ተነሥቶ ወደ ኢያሪኮ ሰሜን ሽቅብ ይወጣና በምዕራብ አቅጣጫ በሚገኘው ኮረብታማ አገር በኩል እስከ ቤትአዌን በረሓ ይደርሳል፤ 13ይኸው ድንበር በደቡብ በኩል ቀድሞ ሎዛ ተብላ ትጠራ ወደነበረችው ወደ ቤትኤል ይወጣና በታችኛው ቤትሖሮን ተራራ በኩል ወደ ዐጣሮትአዳር ይወርዳል። 14ይኸው ድንበር በሌላም አቅጣጫ ከዚህ ተራራ በስተ ምዕራብ ወደ ደቡብ በመታጠፍ የይሁዳ ነገድ ይዞታ ወደ ሆነችው ከተማ ወደ ቂርያትባዓል ወይም ቂርያትይዓሪም ያልፋል፤ ይህም በምዕራብ በኩል የሚገኘው ድንበር ነው፤ 15የደቡቡም ድንበር በምዕራብ በኩል ከቂርያትይዓሪም መጨረሻ ተነሥቶ ወደ ኔፍቶሐ ውሃ ምንጮች ያልፋል። 16ከዚያም ድንበሩ የሔኖም ልጅ ሸለቆ ትይዩ ወደ ሆነው ተራራ ግርጌ ይወርዳል፤ እርሱም ከራፋይም ሸለቆ በሰሜን በኩል ነው፤ ከዚያም ወደ ሔኖም ሸለቆ ይወርድና በኢያቡሳውያን ተረተር ጐን አድርጎ ወደ ኤንሮጌል ይደርሳል፤ 17ከዚያ በኋላ ወደ ሰሜን በመታጠፍ ወደ ዔንሺሜሽ አቅጣጫ ይሄዳል፤ ከዚያም ወደ ገሊሎት ይሄዳል፤ እርሱም ከአዱሚም ዐቀበት ትይዩ ነው፤ እንዲሁም የሮቤል ልጅ ወደ ሆነው ወደ ቦሄን ድንጋይ ይወርዳል፤ 18በስተሰሜን በኩል በዮርዳኖስ ሸለቆ ትይዩ በሚገኘው ተረተር በኩል አልፎ ይወርዳል። 19ድንበሩ በቤትሆግላ ጐን ያልፋል፤ ከጨው ባሕር በስተሰሜን እስከ ዮርዳኖስ ወንዝ ደቡብ ድረስ ይሄዳል። ይህም የደቡቡ ድንበር ነው። 20የምሥራቁ ድንበር የዮርዳኖስ ወንዝ ነው፤ ይህ በዙሪያቸውና በዳር ድንበራቸው የብንያም ነገድ ርስት ነው።
21የብንያም ነገድ ከተሞች በየወገናቸው ቤትሖግላ፥ ዔሜቀጺጽ፥ 22የዮርዳኖስ ሸለቆ ጸማራይም፥ ቤትኤል፥ 23ዐዊም፥ ፋራ፥ ዖፍራ፥ 24ከፋርዐሞናይ፥ ዖፍኒና፥ ጌባዕ ተብለው የሚጠሩ በድምሩ ዐሥራ ሁለት ከተሞች ሲሆኑ፥ በዙሪያቸው የሚገኙ ትናንሽ ከተሞችንም መንደሮችንም ይጨምራሉ። 25በተጨማሪም ገባዖን፥ ራማ፥ በኤሮት፥ 26ምጽጳ፥ ከፊራ፥ ሞጻ፥ 27ሬቄም፥ ይርጰኤል፥ ታራላ፥ 28ጼላዕ፥ ኤሌፍ፥ ኢያቡስ (ኢየሩሳሌም) ጊብዓና ቂርያትይዓሪም ተብለው የሚጠሩ በድምሩ ዐሥራ አራት ከተሞች ሲሆኑ፥ በዙሪያቸው የሚገኙትን ትናንሽ ከተሞችንም ይጨምራሉ። እንግዲህ የብንያም ነገድ በየወገኖቻቸው የተቀበሉት ርስት ይህ ነው።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢያሱ 18: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997