የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ኢያሱ 23

23
ኢያሱ የተናገረው የመሰናበቻ ቃል
1ከብዙ ጊዜ በኋላ እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በዙሪያቸው ከሚገኙ ጠላቶቻቸው በማሳረፍ የሰላምን ኑሮ ሰጣቸው። በዚያን ጊዜ ኢያሱ በዕድሜው ሸምግሎ ነበር፤ 2ስለዚህም እርሱ መላውን እስራኤልን፥ ሽማግሌዎችን፥ መሪዎችን፥ ዳኞችንና የጦር አዛዦችን በአንድነት ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “እነሆ እኔ በዕድሜ ሸምግያለሁ፤ 3አምላካችን እግዚአብሔር እናንተን ለመርዳት በእነዚህ ሕዝቦች ላይ ያደረገውን ሁሉ አይታችኋል፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር ስለ እናንተ ተዋግቶላችኋል፤ 4እኔም ገና ድል ያልተመቱትና ድል የመታኋቸው ሕዝቦች ይዞታ የነበረውና በምሥራቅ በኩል ከዮርዳኖስ ወንዝ በመዋሰን በስተምዕራብ እስከ ሜዲቴራኒያን ባሕር የሚደርሰውን ሁሉ ለነገዶቻችሁ ርስት አድርጌ ሰጥቼአለሁ፤ 5አምላካችሁ እግዚአብሔር እነርሱን በፊታችሁ እንዲሸሹ ያደርጋል፤ እነርሱን ነቃቅሎ ያጠፋል፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር በሰጣችሁም ተስፋ መሠረት ምድራቸውን ትወርሳላችሁ። 6ስለዚህም በኦሪት ሕግ መጽሐፍ የተጻፉትን ትእዛዞች ሁሉ ለመጠበቅ ብርቱ ጥንቃቄ አድርጉ፤ ከእነርሱም ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ፈቀቅ አትበሉ። 7በመካከላችሁ ከቀሩት ሕዝቦች ጋር ከቶ አትተባበሩ፤ የአማልክታቸውንም ስም አትጥሩ፤ በእነርሱም አትማሉ፤ ለእነርሱም አገልጋዮች አትሁኑ፤ አትስገዱላቸውም። 8ይልቅስ እስከ አሁን እንዳደረጋችሁት ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር ታማኞች ሁኑ፤ 9እናንተ ታላላቅና ብርቱዎች የሆኑትን ሕዝቦች እግዚአብሔር ነቃቅሎ አባሮላችኋል፤ እናንተን እስከ ዛሬ ድረስ ሊቋቋማችሁ የቻለ ማንም የለም፤ 10አምላካችሁ እግዚአብሔር በሰጣችሁ ተስፋ መሠረት ስለ እናንተ ስለሚዋጋ ከእናንተ አንዱ ብቻውን ሆኖ ከእነርሱ ወገን አንዱን ሺህ ማባረር ይችላል፤ #ዘዳ. 3፥22፤ 32፥30። 11እንግዲህ አምላካችሁን እግዚአብሔርን የምትወዱ መሆን እንደሚገባችሁ በጥንቃቄ አስቡ። 12እናንተ ግን ከእግዚአብሔር ርቃችሁ በእናንተ መካከል ከቀሩት ከእነዚህ ሕዝቦች ጋር ብትተባበሩ፥ እናንተ የእነርሱን ሴቶች እነርሱ ደግሞ የእናንተን ሴቶች በመጋባት ብትተሳሰሩ፥ 13አምላካችሁ እግዚአብሔር እነዚህን ሕዝቦች ከፊታችሁ ማባረሩን እንደማይቀጥል በእርግጥ ዕወቁ፤ እንዲያውም አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ ከዚህች መልካም ምድር እስክትጠፉ ድረስ እነዚህን ሕዝቦች ለጀርባችሁ መግረፊያ፥ ለዐይኖቻችሁ እንደሚወጋ እሾኽ፥ እንዲሁም አደገኛ ወጥመድና መውደቂያ ጒድጓድ ይሆኑባችኋል።
14“እነሆ እኔ የምሞትበት ጊዜ ደርሶአል፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር በሰጣችሁ ተስፋ መሠረት ያደረገላችሁን መልካም ነገር ሁሉ ከእናንተ እያንዳንዱ በፍጹም ልቡና በፍጹም ነፍሱ ያውቃል፤ እርሱ ከሰጣችሁ ተስፋ አንድም ሳይቀር ሁሉም ተፈጽሞአል። 15አምላካችሁ እግዚአብሔር የተናገረውን መልካም ነገር ሁሉ እንደ ፈጸመላችሁ፥ እንዲሁም እርሱ ከሰጣችሁ ከዚህች መልካም ምድር እስኪያጠፋችሁ ድረስ ክፉን ነገር ሁሉ ሊያመጣባችሁ ይችላል። 16ስለዚህ አምላካችሁ እግዚአብሔር የሰጣችሁን ቃል ኪዳን በማፍረስ ወደ ሌሎች አማልክት ሄዳችሁ ብታመልኩአቸውና ብትሰግዱላቸው እግዚአብሔርን ታስቈጣላችሁ፤ ከሰጣችሁም መልካም ምድር በፍጥነት ትጠፋላችሁ።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ