የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ኢያሱ 24

24
የኢያሱ የመጨረሻ ንግግር
1ኢያሱ የእስራኤልን ነገዶች በሙሉ በሴኬም በአንድነት ሰበሰበ፤ ሽማግሌዎችን፥ አለቆቻቸውን፥ ዳኞችንና የእስራኤልን የጦር አዛዦች ሁሉ ጠራ፤ እነርሱም በእግዚአብሔር ፊት ተሰበሰቡ፤ 2ኢያሱም ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፦ ‘ከብዙ ዘመናት በፊት የቀድሞ አባቶቻችሁ ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ ባዕዳን አማልክትን በማምለክ ይኖሩ ነበር፤ ከነዚያም አባቶች አንዱ የአብርሃምና የናኮር አባት ታራ ነበር፤ #ዘፍ. 11፥27። 3ከዚህም በኋላ የቀድሞ አባታችሁን አብርሃምን ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ ከሚገኘው ምድር ጠርቼ፥ በከነዓን ምድር ሁሉ መራሁት፤ ዘሩንም አበዛሁለት፤ ይስሐቅንም ሰጠሁት፤ #ዘፍ. 12፥1-9፤ 21፥1-3። 4ለይስሐቅም ያዕቆብንና ዔሳውን ሰጠሁ፤ ለዔሳውም የኤዶምን ኮረብታማ አገር ርስት አድርጌ ሰጠሁት፤ ነገር ግን ያዕቆብና ልጆቹ ወደ ግብጽ ወረዱ፤ #ዘፍ. 25፥24-26፤ 36፥8፤ 46፥1-7፤ ዘዳ. 2፥5። 5ከዚያም በኋላ ሙሴንና አሮንን ላክሁ፤ ግብጽንም በመቅሠፍት መታሁ፤ በመጨረሻም እናንተን አወጣኋችሁ፤ #ዘፀ. 3፥1—12፥42። 6የቀድሞ አባቶቻችሁን ከግብጽ ባወጣኋቸው ጊዜ ወደ ባሕር ደረሱ፤ ግብጻውያንም በሠረገሎችና በፈረሰኞች እስከ ቀይ ባሕር ድረስ ባሳደዱአቸው ጊዜ፥ #ዘፀ. 14፥1-31። 7እረዳቸው ዘንድ ወደ እኔ ጮኹ፤ እኔም በእነርሱና በግብጻውያን መካከል ጨለማ እንዲሆን አደረግሁ። ባሕሩም እንዲከነበልባቸው አድርጌ ግብጻውያንን አሰጠምሁ፤ በግብጻውያን ላይ ምን እንዳደረግሁ በዐይኖቻችሁ አይታችኋል፤ ከዚያም በኋላ እናንተ ለብዙ ጊዜ በበረሓ ኖራችሁ። 8ከዚህም በኋላ ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ ወደሚኖሩት ወደ አሞራውያን ምድር አመጣኋችሁ፤ እነርሱ ተዋጉአችሁ፤ እኔ ግን በእነርሱ ላይ ድልን አቀዳጀኋቸው፤ ከፊታችሁም አጠፋኋቸው፤ ምድራቸውንም ወረሳችሁ። #ዘኍ. 21፥21-35። 9ከዚህም በኋላ የሞአብ ንጉሥ የነበረው የጲፖር ልጅ ባላቅ ሊወጋችሁ በእናንተ ላይ ተነሣሣ፤ እናንተንም ይረግምለት ዘንድ በለዓም ተብሎ ወደሚጠራው ወደ ቢዖር ልጅ መልእክት ላከ፤ 10እኔ ግን በለዓምን አልሰማሁትም፤ ስለዚህም በመርገም ፈንታ ባረካችሁ፤ በዚህም ዐይነት ከባላቅ እጅ አዳንኳችሁ፤ #ዘኍ. 22፥1-24፤25። 11እናንተም የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግራችሁ ወደ ኢያሪኮ መጣችሁ፤ የኢያሪኮም ሰዎች፥ እንዲሁም አሞራውያን፥ ፈሪዛውያን፥ ከነዓናውያን፥ ሒታውያን፥ ጌርጌሳውያን፥ ሒዋውያንና ኢያቡሳውያን እናንተን ለመውጋት ተነሡ፤ እኔ ግን በእነርሱ ላይ ድልን አቀዳጀኋችሁ። #ኢያሱ 3፥14-17፤ 6፥1-21። 12በሁለቱ አሞራውያን ነገሥታት ላይ እንዳደረግሁት አስቀድሜ ከፊታችሁ ያባረራቸውን ተርብ ሰደድኩባቸው፤ ይህ በእናንተ ሰይፍ ወይም በእናንተ ቀስት የሆነ አይደለም። #ዘፀ. 23፥28፤ ዘዳ. 7፥20። 13እናንተ በማረስ ያልደከማችሁበትን የለማ ምድርና ያልሠራችኋቸውንም ከተሞች መኖሪያ አድርጌ ሰጠኋችሁ፤ እነሆ፥ አሁን ያልተከላችሁትን የወይን ተክልና ያልደከማችሁበትን የወይራ ዛፍ ፍሬ እየተመገባችሁ ትኖራላችሁ።’ ” #ዘዳ. 6፥10-11።
14ኢያሱ ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ እግዚአብሔርን አክብሩት፤ በፍጹም ቅንነትና በታማኝነት አገልግሉት፤ የቀድሞ አባቶቻችሁ ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶና በግብጽ ይሰግዱላቸው የነበሩትን ባዕዳን አማልክት አስወግዳችሁ እግዚአብሔርን ብቻ አምልኩ፤ 15እርሱን ማምለክ መልካም መስሎ ካልታያችሁ ግን የቀድሞ አባቶቻችሁ ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ በነበሩበት ጊዜ ያመልኩአቸው የነበሩትን ወይም አሁን በምድራቸው የምትኖሩባቸውን የአሞራውያንን አማልክት ታመልኩ እንደሆን የምታመልኩትን ዛሬውኑ ምረጡ፤ እኔና ቤተሰቤ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን።”
16ሕዝቡም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤ “እግዚአብሔርን ትተን ሌሎች ባዕዳን አማልክትን ማምለክ ከእኛ ይራቅ! 17አምላካችን እግዚአብሔር አባቶቻችንንና እኛን ከግብጽ ባርነት አውጥቶናል፤ ያደረገውን ተአምራት ሁሉ አይተናል፤ ሕዝቦችን ሁሉ አልፈን በመጣንበት ጊዜ በሰላም ጠብቆናል፤ 18እግዚአብሔር ሕዝቦችን እንዲሁም በምድሪቱ የሚኖሩትን አሞራውያንን ሁሉ ከፊታችን አባሮልናል፤ ስለዚህም እርሱ አምላካችን ስለ ሆነ እግዚአብሔርን እናመልካለን።”
19ኢያሱም ለሕዝቡ እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር ቅዱስና ቀናተኛ አምላክ ስለ ሆነ፥ እናንተ እርሱን ማገልገል አትችሉም፤ የምትሠሩትን ዐመፅና ኃጢአት ሁሉ ይቅር አይልም፤ 20እርሱን ትታችሁ ባዕዳን አማልክትን ብታመልኩ፥ ደግ ያደረገላችሁ ቢሆንም እንኳ ተመልሶ እርሱ ክፉ ነገር ያደርግባችኋል፤ ያጠፋችሁማል።”
21ሕዝቡም ለኢያሱ “ይህ ከቶ አይደረግም! እኛ እግዚአብሔርን እናመልካለን” አሉት።
22ኢያሱም “እንግዲህ እግዚአብሔርን ለማምለክ ስለ መምረጣችሁ ራሳችሁ በራሳችሁ ላይ ምስክሮች ናችሁ” ሲል ነገራቸው።
እነርሱም “አዎ፤ ምስክሮች ነን፤” አሉ።
23እርሱም “እንግዲያውስ በመካከላችሁ የሚገኙትን ባዕዳን አማልክት አስወግዱ፤ ልባችሁንም ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር አድርጉ” አላቸው።
24ከዚህም በኋላ ሕዝቡ ኢያሱን “እኛ አምላካችንን እግዚአብሔርን እናመልካለን፥ ትእዛዞችንም እንፈጽማለን” አሉት።
25በዚያም ቀን ኢያሱ ከሕዝቡ ጋር ቃል ኪዳን ገባ፤ በዚያም በሴኬም የሚመሩበትን ሕግና ሥርዓት ሰጣቸው፤ 26ኢያሱም እነዚህን ትእዛዞች በእግዚአብሔር የሕግ መጽሐፍ ጻፈ፤ ከዚያም በኋላ አንድ ትልቅ ድንጋይ ወስዶ በእግዚአብሔር መቅደስ አጠገብ በሚገኘው የወርካ ዛፍ ሥር አቆመው፤ 27ኢያሱም ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር የነገረንን ቃል ሁሉ ስለ ሰማ ይህ ድንጋይ በእኛ ላይ ምስክር ነው፤ ስለዚህም አምላካችሁን ብትክዱ በእናንተ ላይ ምስክር ይሆንባችኋል።” 28ከዚህ በኋላ ኢያሱ ሕዝቡን ሁሉ አሰናበተ፤ እያንዳንዱም ወደየርስት ይዞታው ተመልሶ ሄደ።
የኢያሱና የአልዓዛር መሞት
29ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔር አገልጋይ የነዌ ልጅ ኢያሱ በአንድ መቶ ዐሥር ዓመት ዕድሜው ሞተ። 30እስራኤላውያንም ከጋዓሽ ተራራ በስተሰሜን በኩል በምትገኘው በኮረብታማይቱ በኤፍሬም አገር የራሱ የኢያሱ ርስት በሆነችው በቲምናትሴራሕ ቀበሩት። #ኢያሱ 19፥49-50።
31ኢያሱ በሕይወት በነበረበት ጊዜ ሁሉ የእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔርን አመለኩ፤ ከእርሱም ሞት በኋላ እግዚአብሔር ለእስራኤል ያደረገውን ድንቅ ነገር ሁሉ በዐይናቸው ያዩት ሽማግሌዎች እስከ ኖሩበት ዘመን ድረስ እርሱኑ በማምለክ ኖሩ።
32የእስራኤል ሕዝብ ከግብጽ ምድር ያወጡት የዮሴፍ ዐፅም በሴኬም ተቀበረ፤ ይህም ምድር ያዕቆብ የሼኬም አባት ከሆነው ከሐሞር ልጆች በአንድ መቶ ጥሬ ብር የገዛው ነበር፤ ምድሩም የሚገኘው በዮሴፍ ዘሮች የርስት ድርሻ ክልል ውስጥ ነው። #ዘፍ. 33፥19፤ 50፥24-25፤ ዘፀ. 13፥19፤ ዮሐ. 4፥5፤ ሐ.ሥ. 7፥16።
33የአሮን ልጅ አልዓዛርም ሞተ፤ በጊብዓም ተቀበረ፤ እርስዋም በኮረብታማው በኤፍሬም አገር የምትገኝና ለልጁ ለፊንሐስ መኖሪያ የተሰጠች ትንሽ ከተማ ናት።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ