የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ኢያሱ 8

8
የዐይ ከተማ መያዝና መደምሰስ
1ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ኢያሱን እንዲህ አለው፤ “የጦር ወታደሮችህን ይዘህ ወደ ዐይ ከተማ ለመዝመት ውጣ፤ ከቶ አትፍራ፤ ደፋር ሁን፤ እኔ በዐይ ንጉሥ ላይ ድልን እንድትቀዳጅ አድርጌሃለሁ፤ ሕዝቡ፥ ከተማይቱና ምድሪቱ የአንተ ይሆናሉ፤ 2ከዚህ በፊት በኢያሪኮና በንጉሥዋ ላይ የደረሰውን ጥፋት በዐይና በንጉሥዋም ላይ ደግሞ ትፈጽምባቸዋለህ፤ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ከእርስዋ የሚገኘውን የንብረትና የከብት ምርኮ ለራሳችሁ ታደርጋላችሁ፤ ከኋላ በኩል በከተማይቱ ላይ በድንገት አደጋ ለመጣል ተዘጋጅ።”
3ስለዚህም፥ ኢያሱ ከወታደሮቹ ጋር በዐይ ላይ ዘመተ፤ ከሠራዊቱም የተሻለ ችሎታ ያላቸውን ሠላሳ ሺህ ወታደሮች መርጦ በሌሊት ሲልካቸው 4እንዲህ የሚል ትእዛዝ ሰጣቸው፦ “ከከተማይቱ በስተኋላ አድፍጣችሁ ቈዩ፤ ይሁን እንጂ ከከተማይቱ ብዙ ሳትርቁ አደጋ ለመጣል በሚያስችላችሁ ሁኔታ ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ፤ 5እኔና ከእኔ ጋር የተመደቡት የጦር ሰልፈኞች ወደ ከተማይቱ እንቀርባለን፤ የዐይ ወታደሮች በእኛ ላይ አደጋ ለመጣል በሚመጡብን ጊዜ ልክ ከዚህ በፊት ባደረግነው ዐይነት ወደ ኋላ እንሸሻለን፤ 6ከእነርሱ እየሸሸን ሳለን እንደ ቀድሞው ከእኛ እየሸሹ ነው ይላሉ፤ ከከተማው እስክናርቃቸው ድረስ እኛን ይከተላሉ፤ 7በዚህን ጊዜ እናንተ ከተደበቃችሁበት ስፍራ ወጥታችሁ ከተማይቱን ያዙ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔርም ከተማይቱን ለእናንተ አሳልፎ ይሰጣችኋል። 8ከተማይቱን ከያዛችሁ በኋላ፥ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት በእሳት አቃጥሉአት። እነሆ፥ አዝዤአችኋለሁ።” 9ከዚህ በኋላ ኢያሱ ወታደሮቹን ላከ፤ ከዐይ በስተምዕራብ በኩል በዐይና በቤትኤል መካከል ድብቅ ጦር ሆነው ቈዩ፤ ኢያሱም በሠራዊቱ መካከል ዐደረ።
10በማግስቱም ጠዋት ኢያሱ ቀደም ብሎ በመነሣት ሕዝቡን ጠራ፤ እርሱና የእስራኤል መሪዎች ሁሉ ዘማቹን ጦር ወደ ዐይ መምራት ጀመሩ፤ 11ከእርሱም ጋር የነበረው ሠራዊት ወደ ፊት ቀድሞ በመጓዝ ወደ ከተማይቱ ቀረበ፤ በስተሰሜንም በኩል በእርሱና በዐይ መካከል ካለው ሸለቆ ማዶ ሰፈረ። 12ኢያሱ አምስት ሺህ ሰዎችን ያኽል መርጦ ከከተማይቱ በስተምዕራብ በኩል በዐይና በቤትኤል መካከል እንዲሸምቁ አድርጎ ነበር። 13እነርሱም ዋናውን ሠራዊት ከከተማ በስተሰሜን በኩል፥ የኋላውን ደጀን በስተምዕራብ በኩል አሰለፉ፤ ኢያሱ ግን ሌሊቱን በሸለቆው አሳለፈ። 14የዐይ ንጉሥ ይህን በአየ ጊዜ እርሱና የከተማው ሕዝብ እስራኤልን በጦርነት ለመግጠም ወደ ዓራባ ፊት ለፊት ወጡ። ከከተማው በስተጀርባ በኩል የደጀን ጦር መኖሩን አላወቁም ነበር። 15ኢያሱና ሠራዊቱ ሁሉ የተሸነፉ በማስመሰል ወደ ኋላ በማፈግፈግ ወደ ምድረ በዳ ሸሹ። 16የከተማይቱም ሰዎች እርስ በርስ በመጠራራት በሙሉ ወጥተው እነርሱን ማሳደድ ቀጠሉ፤ ኢያሱንም በሚያሳድዱበት ጊዜ ከከተማይቱ እየራቁ ሄዱ። 17በዐይ ወይም በቤትኤል የሚገኝ ሰው ሁሉ ወጥቶ እስራኤላውያንን ሲያሳድድ ከተማይቱ ባዶዋን ክፍት ሆና ቀረች።
18ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር ኢያሱን፦ “ጦርህን በዐይ ከተማ ላይ አንሣ፤ እኔ እርስዋን ለአንተ አሳልፌ እሰጥሃለሁ” አለው። ኢያሱም በእጁ ያለውን ጦር ወደ ከተማይቱ ዘረጋ። 19እጁንም በዘረጋ ጊዜ ሸምቀው የነበሩት ወታደሮች ከቦታቸው ተነሥተው ወደፊት ሄዱ፤ ወደ ከተማዋም በፍጥነት ገብተው በቊጥጥራቸው ሥር አደረጓትና ወዲያውኑ አቃጠሉአት። 20የዐይ ከተማ ሰዎችም ወደ ኋላ መለስ ብለው ባዩ ጊዜ የከተማይቱ ጢስ ወደ ሰማይ ሲወጣ አዩ፤ ወደ ምድረ በዳ የሸሹት እስራኤላውያን በአሳዳጆቻቸው ላይ ስለ ተመለሱባቸው፥ በየትም በኩል ለማምለጥ አልቻሉም። 21ኢያሱና ከእርሱ ጋር ተሰልፎ የነበረው ሠራዊት ቀደም ብለው ያዘጋጁት ሽምቅ ጦር ከተማይቱን በቊጥጥር ሥር ማድረጉንና በእሳት ማቃጠሉን በተመለከቱ ጊዜ ወደ ኋላ መለስ ብለው የዐይን ሰዎች መቱ። 22ወደ ከተማይቱም ገብተው የነበሩት እስራኤላውያን ወደ እነርሱ ወርደው የጦርነቱ ተካፋዮች ሆኑ፤ ስለዚህም የዐይን ሰዎች የተወሰኑ እስራኤላውያን በአንድ በኩል፥ ሌሎች ደግሞ በሌላ በኩል ከበዋቸው ስለ ነበረ ወደየትም ለማምለጥ አልቻሉም። ከእነርሱም አንድ እንኳ እንዳያመልጥ ወይም በሕይወት እንዳይኖር ሁሉንም ፈጁአቸው። 23የዐይ ንጉሥ ግን ተማርኮ ወደ ኢያሱ ቀረበ።
24እስራኤላውያን በሜዳና በምድረ በዳ ቀደም ሲል የዐይ ወታደሮች እነርሱን አሳደዋቸው በነበረው ስፍራ ሁሉንም ገድለው ከጨረሱ በኋላ ወደ ዐይ ከተማ ገብተው በዚያ የተረፉትንም በሰይፍ ፈጁአቸው። 25በዚያን ቀን የሞቱት የዐይ ወንዶችና ሴቶች ዐሥራ ሁለት ሺህ ነበሩ። 26ኢያሱም በዐይ የሚኖሩትን ሁሉ ፈጽሞ እስኪያጠፋ ድረስ ጦር የዘረጋባትን እጁን አላጠፈም። 27እግዚአብሔርም ለኢያሱ በነገረው መሠረት እስራኤላውያን በዚያች ያገኙትን የከብትና የሌላ ንብረት ምርኮ ሁሉ ለራሳቸው አደረጉ። 28ኢያሱ የዐይን ከተማ በማቃጠል ለዘለዓለም ፍርስራሽ አድርጎ ተዋት፤ እስከ አሁንም ድረስ በዚህ ዐይነት ትገኛለች። 29የዐይንም ከተማ ንጉሥ በእንጨት ላይ ሰቅሎ ሬሳው እስከ ማታ ተንጠልጥሎ እንዲቈይ አደረገ። ፀሐይም በምትጠልቅበት ጊዜ ሬሳው ከተሰቀለበት እንጨት ላይ ወርዶ በከተማይቱ ቅጽር በር መግቢያ እንዲጣል አደረገ፤ በእርሱም ላይ ብዙ የድንጋይ ቊልል ከመሩበት፤ የድንጋዩም ቊልል እስከ አሁን በዚያው ይገኛል።
ሙሴ የጻፈው ሕግ በዔባል ተራራ ላይ መነበቡ
30ከዚህም በኋላ ኢያሱ በዔባል ተራራ ላይ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ፤ 31የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ እስራኤላውያንን ባዘዘው መሠረት በሙሴ አማካይነት በተሰጠው የሕግ መጽሐፍ ውስጥ እንደ ተጻፈው ባልተጠረበና ብረት ባልነካው ድንጋይ መሠዊያ ሠርተው የሚቃጠል መሥዋዕትና የአንድነት ቊርባን አቀረቡ። #ዘፀ. 20፥25። 32ሙሴ ጽፎት የነበረውን የኦሪትን ሕግ ኢያሱ በእስራኤላውያን ፊት በድንጋይ ላይ ጻፈው። #ዘዳ. 27፥2-8። 33የእስራኤልን ሕዝብ እንዲባርኩ ቀደም ብሎ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ ባዘዘው መሠረት እስራኤላውያን ሁሉና መጻተኞች ሽማግሌዎቻቸው፥ ሹሞቻቸውና ዳኞቻቸው የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት ከተሸከሙት ከሌዋውያን ካህናት ፊት ለፊት ግራና ቀኝ እኩሌቶቹ ከጌሪዚም ተራራ ፊት ለፊት፥ እኩሌቶቹ ደግሞ ከኤባል ተራራ ፊት ለፊት ቆሙ። 34ከዚህም በኋላ ኢያሱ በሕጉ መጽሐፍ በተጻፈው መሠረት የሕጉን ቃላት በሙሉ በረከቱን፥ መርገሙንም ጭምር አነበበ። 35ኢያሱም በእስራኤል ጉባኤ ሁሉ በሴቶች፥ በሕፃናትና በመጻተኞች ፊት ሙሴ ካዘዘው ሕግ አንዲት ቃል እንኳ ሳያስቀር አነበበ። #ዘዳ. 11፥29፤ 27፥11-14።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ