የሉቃስ ወንጌል 23:26-56

የሉቃስ ወንጌል 23:26-56 አማ05

ስለዚህ ኢየሱስን ወሰዱት፤ ይዘውት ሲሄዱ ሳሉም የቀሬና ሰው የሆነውን ስምዖንን ከገጠር ወደ ከተማ ሲገባ አገኙት፤ እርሱን ይዘው የኢየሱስን መስቀል አሸከሙትና ኢየሱስን እንዲከተል አደረጉት። ብዙ ሰዎችም ኢየሱስን ይከተሉ ነበር፤ ከእነርሱም መካከል ደረታቸውን እየደቁ የሚያለቅሱለት ሴቶች ነበሩ። ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ መለስ ብሎ፥ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ የኢየሩሳሌም ሴቶች፥ ስለ ራሳችሁና ስለ ልጆቻችሁ አልቅሱ እንጂ ስለ እኔ አታልቅሱ! ‘መኻኖች የሆኑ ሴቶች፥ ያልወለዱ ማሕፀኖችና ያላጠቡ ጡቶች እንዴት የታደሉ ናቸው!’ የሚባሉበት ቀኖች ይመጣሉ። በዚያን ጊዜ ሰዎች ተራራዎችን፥ ‘በላያችን ውደቁ!’ ኮረብቶችንም፥ ‘ሸሽጉን!’ ማለት ይጀምራሉ። እንግዲህ ይህ ሁሉ ነገር በእርጥብ እንጨት ላይ የሚደረግ ከሆነ በደረቅ እንጨት ላይማ ምን ይደረግ ይሆን?” እንዲሁም ሁለት ወንጀለኞችን ከኢየሱስ ጋር ሊገድሉአቸው ይዘው ሄዱ። ቀራንዮ ወይም የራስ ቅል ወደ ተባለ ስፍራም በደረሱ ጊዜ በዚያ ኢየሱስን ሰቀሉት፤ እንዲሁም ሁለቱን ወንጀለኞች በኢየሱስ ግራና ቀኝ ሰቀሉአቸው። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ፦ “አባት ሆይ! የሚያደርጉትን ስለማያውቁ ይቅር በላቸው!” አለ። ወታደሮቹም ዕጣ ተጣጥለው የኢየሱስን ልብስ ተከፋፈሉ። ሕዝቡ ቆሞ ይመለከት ነበር፤ የአይሁድ አለቆችም “ሌሎችንስ አዳነ እንግዲህ እርሱ የተመረጠው የእግዚአብሔር መሲሕ ከሆነ እስቲ ራሱን ያድን!” እያሉ ያፌዙበት ነበር። ወታደሮቹም እንዲሁ አፌዙበት፤ ወደ እርሱም ቀርበው ሆምጣጤ ሰጡት። እንዲሁም “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ከሆንክ እስቲ ራስህን አድን!” ይሉት ነበር። “ይህ የአይሁድ ንጉሥ ነው” የሚል ጽሑፍም በኢየሱስ ራስጌ በመስቀሉ ላይ አኖሩ። ከኢየሱስ ጋር ከተሰቀሉት ወንጀለኞች አንዱ፥ ኢየሱስን፦ “አንተ መሲሕ አይደለህምን? እስቲ በል ራስህንና እኛን አድን!” እያለ ይሰድበው ነበር። ሌላው ወንጀለኛ ግን እንዲህ ብሎ ገሠጸው፦ “አንተ በተመሳሳይ ፍርድ ላይ እያለህ እግዚአብሔርን አትፈራምን? እኛ ባደረግነው በደል ምክንያት የሚገባንን ቅጣት አግኝተናል፤ ይህ ሰው ግን ምንም ጥፋት አላደረገም።” ቀጥሎም ኢየሱስን፦ “ጌታ ሆይ! በመንግሥትህ ስትመጣ አስታውሰኝ!” አለው። ኢየሱስም “በእውነት እልሃለሁ፤ ዛሬውኑ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ!” አለው። እነሆ፥ ይህ የሆነው ከቀኑ ስድስት ሰዓት ገደማ ነበር፤ ከዚያን ጊዜም ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። ፀሐይ ጨለመ፤ የቤተ መቅደስ መጋረጃም ከመካከሉ ተቀዶ ከሁለት ተከፈለ። ኢየሱስም ድምፁን ከፍ አድርጎ፥ “አባት ሆይ! እነሆ! ነፍሴን በእጅህ ዐደራ እሰጣለሁ!” አለ፤ ይህንንም ካለ በኋላ ነፍሱ ከሥጋው ተለየች። በዚያ የነበረው መቶ አለቃ፥ የሆነውን ነገር ባየ ጊዜ፥ “በእርግጥ ይህ ሰው ጻድቅ ኖሮአል!” ብሎ እግዚአብሔርን አከበረ። ነገሩን ለመመልከት እዚያ ተሰብስበው የነበሩ ሰዎች ሁሉ የሆነውን ነገር ባዩ ጊዜ በማዘን ደረታቸውን እየመቱ ወደየቤታቸው ተመለሱ። ኢየሱስን በቅርብ ያውቁት የነበሩ ሰዎች ሁሉና ከገሊላ ጀምሮ ይከተሉት የነበሩ ሴቶችም በሩቅ ቆመው ይህን ነገር ይመለከቱ ነበር። የአይሁድ ከተማ በሆነችው በአርማትያስ የሚኖር ዮሴፍ የሚባል ሰው ነበረ፤ እርሱ ጻድቅና ደግ ሰው ነበረ፤ የአይሁድ ሸንጎ አባልም ነበረ። ይሁን እንጂ በአይሁድ ምክርና ሤራ አልተባበረም፤ እርሱ የእግዚአብሔርን መንግሥት በተስፋ የሚጠባበቅ ሰው ነበረ። ይህ ሰው ወደ ጲላጦስ ፊት ቀርቦ የኢየሱስ አስከሬን እንዲሰጠው ጠየቀ። አስከሬኑንም አውርዶ በቀጭን ሐር ልብስ ከፈነው፤ ማንም ሰው ባልተቀበረበት ከአለት ተወቅሮ በተዘጋጀ መቃብር ውስጥ ቀበረው፤ ይህንንም ያደረገው ዓርብ ማታ ለሰንበት ዝግጅት በሚደረግበት ጊዜ ነበር። ኢየሱስን ተከትለው ከገሊላ የመጡ ሴቶች ከዮሴፍ ጋር ሄደው መቃብሩን አዩ፤ አስከሬኑም እንዴት እንደ ተቀበረ ተመለከቱ። ወደ ቤታቸውም ተመልሰው ለአስከሬን የሚሆኑ ጥሩ መዓዛ ያለው ቅመምና ሽቶ አዘጋጁ፤ በሕግ መሠረት በሰንበት ቀን ዐርፈው ዋሉ።