ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር ከተራራው ወርዶ በሜዳ ላይ ቆመ፤ ከደቀ መዛሙርቱም ብዙዎቹ በዚያ ነበሩ፤ እንዲሁም ሊሰሙትና ከበሽታቸው ሊፈወሱ ፈልገው የመጡ፥ እጅግ ብዙ ሕዝብ ነበሩ። እነርሱም የመጡት ከይሁዳ ምድር ከኢየሩሳሌም ከተማ፥ በባሕር አጠገብ ከሚገኙት ከጢሮስና ከሲዶና ከተሞች ነበር። በርኩሳን መናፍስት ተይዘው ይታወኩ የነበሩት ሰዎችም መጥተው ይፈወሱ ነበር። የማዳን ኀይል ከእርሱ እየወጣ ሁሉንም ይፈውስ ስለ ነበር የተሰበሰቡት ሰዎች ሁሉ ኢየሱስን ለመንካት ይፈልጉ ነበር። ኢየሱስ ቀና ብሎ ወደ ደቀ መዛሙርቱ እየተመለከተ እንዲህ አላቸው፦ “የእግዚአብሔር መንግሥት የእናንተ ናትና፥ እናንተ ድኾች የተባረካችሁ ናችሁ! እናንተ አሁን የምትራቡ፥ በኋላ ትጠግባላችሁና የተባረካችሁ ናችሁ! እናንተ አሁን የምታለቅሱ፥ በኋላ ትስቃላችሁና የተባረካችሁ ናችሁ፤ “በእኔ በሰው ልጅ ምክንያት ሰዎች ሲጠሉአችሁ፥ ሲለዩአችሁ፥ ሲያንቋሽሹአችሁና ስማችሁን ሲያጠፉ የተባረካችሁ ናችሁ! በሰማይ ዋጋችሁ ትልቅ ነውና ይህ ሁሉ ሲደርስባችሁ የተባረካችሁ ናችሁ! ሐሴትም አድርጉ፤ የቀድሞ አባቶቻቸውም በነቢያት ላይ እንዲህ ያለውን ክፋት አድርገውባቸው ነበር። “እናንተ ሀብታሞች ግን ለምቾታችሁ የሚሆነውን ሁሉ አሁን አግኝታችኋልና ወዮላችሁ! “እናንተ አሁን የጠገባችሁ፥ ኋላ ትራባላችሁና ወዮላችሁ! እናንተ አሁን የምትስቁ፥ ኋላ ስለምታዝኑና ስለምታለቅሱ ወዮላችሁ! “ሰዎች ሁሉ ስለ እናንተ መልካም ሲናገሩ ወዮላችሁ! አባቶቻቸውም ለሐሰተኞች ነቢያት እንዲሁ አድርገው ነበር። “ለእናንተ ለምትሰሙኝ ግን እንዲህ እላችኋለሁ፤ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ ለሚጠሉአችሁም መልካም ነገር አድርጉ፤ የሚረግሙአችሁን መርቁ፤ ለሚበድሉአችሁም ጸልዩላቸው፤ አንዱን ጒንጭህን በጥፊ ለሚመታህ፥ ሌላውንም ጒንጭህን እንዲመታ አዙርለት፤ ነጠላህን ለሚወስድብህ፥ እጀ ጠባብህንም ጨምረህ ስጠው፤ ለሚለምንህ ሁሉ ስጥ፤ ንብረትህን የሚወስድብህን ሰው እንዲመልስ አትጠይቀው። ሰዎች ለእናንተ ሊያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን እናንተም እንዲሁ ለእነርሱ አድርጉላቸው። “የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ብልጫ ታገኛላችሁ! ኃጢአተኞችም የሚወዱአቸውን ይወዳሉ፤ መልካም ነገር ለሚያደርጉላችሁ እናንተም መልካም ነገር ብታደርጉላቸው ምን ብልጫ ታገኛላችሁ! ኃጢአተኞችም እንዲሁ ያደርጋሉ፤ ‘ይመልሱልናል’ ብላችሁ ለምታስቡአቸው ሰዎች ብታበድሩ ምን ብልጫ ታገኛላችሁ? ያንኑ ያበደሩትን መልሰው ለመቀበልማ ኃጢአተኞችም ለኃጢአተኞች ያበድራሉ። እናንተ ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ! መልካም ነገርም አድርጉላቸው፤ ‘ብድራችን ይመለስልናል’ ብላችሁ ተስፋ ሳታደርጉ አበድሩ፤ ይህን ብታደርጉ ዋጋችሁ ትልቅ ይሆናል፤ የልዑል እግዚአብሔር ልጆችም ትሆናላችሁ፤ እርሱ ለውለታ ቢሶችና ለክፉዎች እንኳ ሳይቀር ቸር ነው። የሰማይ አባታችሁ መሓሪ እንደ ሆነ እናንተም እንዲሁ መሓሪዎች ሁኑ። “በማንም ላይ አትፍረዱ፤ በእናንተም ላይ አይፈረድባችሁም፤ ሌሎችን አትንቀፉ፤ እናንተም አትነቀፉም፤ ይቅር በሉ፤ እናንተም ይቅርታ ታገኛላችሁ፤ ስጡ፤ ለእናንተም ይሰጣችኋል፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ እንዲሁ ይሰፈርላችኋል፤ እንዲያውም በጥሩ መስፈሪያ ታምቆና ተጠቅጥቆ እስኪትረፈረፍ ድረስ ተሰፍሮ ይሰጣችኋል።” ቀጥሎም ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፦ “ ዕውር ዕውርን ሊመራ ይችላልን? እንዲህማ ቢያደርግ ሁለቱም ተያይዘው በጒድጓድ ውስጥ ይወድቃሉ። ተማሪ ከአስተማሪው አይበልጥም፤ ይሁን እንጂ ተማሪ ትምህርቱን በደንብ ከተማረ እንደ አስተማሪው ይሆናል። “በአንተ ዐይን ያለውን ግንድ ሳታይ ስለምን በወንድምህ ዐይን ያለውን ጒድፍ ትመለከታለህ? ደግሞስ በአንተ ዐይን ያለውን ግንድ ሳታይ ወንድምህን ‘ወንድሜ ሆይ፥ እስቲ በዐይንህ ያለውን ጒድፍ ላውጣልህ፤’ ማለት እንዴት ትችላለህ? አንተ ግብዝ፥ አስቀድመህ በአንተ ዐይን ያለውን ግንድ አውጣ፤ ከዚህ በኋላ በወንድምህ ዐይን ያለውን ጒድፍ ለማውጣት አጥርተህ ማየት ትችላለህ።
የሉቃስ ወንጌል 6 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 6:17-42
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች