ሉቃስ 6:17-42
ሉቃስ 6:17-42 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢየሱስም አብሯቸው ከተራራው ወርዶ ደልዳላ ቦታ ላይ ቆመ፤ ከደቀ መዛሙርቱም እጅግ ብዙ ሰዎች በዚያ ነበሩ፤ ከይሁዳ ሁሉና ከኢየሩሳሌም እንዲሁም ከጢሮስና ከሲዶና ባሕር ጠረፍ የመጣ ብዙ ሕዝብም በዚያ ነበረ፤ እነዚህም የመጡት ሊሰሙትና ካለባቸው ደዌ ሊፈወሱ ነበር። በርኩሳን መናፍስት ይሠቃዩ የነበሩትም ተፈወሱ፤ ኀይል ከእርሱ እየወጣ ሁሉንም ይፈውስ ስለ ነበር፣ ሰዎቹ ሁሉ እርሱን ለመንካት ይፈልጉ ነበር። ወደ ደቀ መዛሙርቱም በመመልከት እንዲህ አለ፤ “እናንት ድኾች ብፁዓን ናችሁ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት የእናንተ ናትና፤ እናንት አሁን የምትራቡ ብፁዓን ናችሁ፤ ኋላ ትጠግባላችሁና፤ እናንት አሁን የምታለቅሱ ብፁዓን ናችሁ፤ ኋላ ትሥቃላችሁና፤ ሰዎች ስለ ሰው ልጅ ሲጠሏችሁ፣ ከመካከላቸው ሲለዩአችሁና ሲነቅፏችሁ፣ ክፉ ስምም ሲሰጧችሁ ብፁዓን ናችሁ። “እነሆ፤ ወሮታችሁ በሰማይ ታላቅ ነውና፣ በዚያን ቀን ደስ ይበላችሁ፤ ፈንድቁም፤ የቀድሞ አባቶቻቸውም በነቢያት ላይ ያደረጉት ይህንኑ ነበርና። “ነገር ግን እናንት ሀብታሞች ወዮላችሁ፤ መጽናናታችሁን አሁኑኑ ተቀብላችኋልና። እናንት አሁን የጠገባችሁ ወዮላችሁ፤ ኋላ ትራባላችሁና። እናንት አሁን የምትሥቁ ወዮላችሁ፤ ኋላ ታዝናላችሁ፤ ታለቅሳላችሁም። ሰዎች ሁሉ ስለ እናንተ መልካም ሲናገሩላችሁ ወዮላችሁ፤ የቀድሞ አባቶቻቸው ለሐሰተኞች ነቢያት ያደረጉላቸው ይህንኑ ነበርና። “ነገር ግን ለእናንተ ለምትሰሙ እላችኋለሁ፤ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ ለሚጠሏችሁም መልካም አድርጉ፤ የሚረግሟችሁን መርቁ፤ ለሚበድሏችሁም ጸልዩ። አንዱን ጕንጭህን ለሚመታህ ሌላውን ጕንጭህን ደግሞ ስጠው፤ መጐናጸፊያህን ለሚወስድብህ እጀ ጠባብህን አትከልክለው። ለሚለምንህ ሁሉ ስጥ፤ ንብረትህን የሚወስድ እንዲመልስልህ አትጠይቀው። ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን እናንተም እንዲሁ አድርጉላቸው። “የሚወድዷችሁን ብትወድዱ ምን የተለየ ዋጋ ታገኛላችሁ? ኀጢአተኞችም እንኳ የሚወድዷቸውን ይወድዳሉና። መልካም ላደረጉላችሁ መልካም ብታደርጉ ምን የተለየ ዋጋ ታገኛላችሁ? ኀጢአተኞችም እንኳ እንደዚያ ያደርጋሉና። ብድር ይመልሳል ለምትሉት ብታበድሩ ምን የተለየ ዋጋ ታገኛላችሁ? ኀጢአተኞችም እንኳ ያበደሩትን ያህል መልሰው ለመቀበል ለኀጢአተኞች ያበድራሉ። ነገር ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ መልካም አድርጉ፤ መልሳችሁ ለመቀበል ተስፋ ሳታደርጉም አበድሩ፤ በዚህም ወሮታችሁ ታላቅ ይሆናል፤ የልዑልም ልጆች ትሆናላችሁ፤ እርሱ ለማያመሰግኑና ለክፉዎች ቸር ነውና። አባታችሁ ርኅሩኅ እንደ ሆነ እናንተም ርኅሩኆች ሁኑ። “አትፍረዱ፤ አይፈረድባችሁም፤ አትኰንኑ፤ አትኰነኑም። ይቅር በሉ፤ ይቅር ትባላላችሁ። ስጡ፤ ይሰጣችኋል፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ተመልሶ ስለሚሰፈርላችሁ፣ ጫን በተደረገ፣ በተነቀነቀና በተትረፈረፈ መልካም መስፈሪያ ተሰፍሮ በዕቅፋችሁ ይሰጣችኋል።” ደግሞም ይህን ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “ዕውር ዕውርን ሊመራ ይችላልን? ሁለቱ ተያይዘው ጕድጓድ አይገቡምን? ደቀ መዝሙር ከመምህሩ አይበልጥም፤ ነገር ግን በሚገባ የተማረ ሰው ሁሉ እንደ መምህሩ ይሆናል። “በወንድምህ ዐይን ውስጥ ያለውን ጕድፍ ለምን ታያለህ? በራስህ ዐይን ውስጥ የተጋደመውን ግንድ አትመለከትምን? በራስህ ዐይን ውስጥ ያለውን ግንድ ሳታይ ወንድምህን፣ ‘ወንድሜ ሆይ፤ በዐይንህ ውስጥ ያለውን ጕድፍ ላውጣልህ’ እንዴት ልትለው ትችላለህ? አንተ ግብዝ፤ በመጀመሪያ በዐይንህ ውስጥ የተጋደመውን ግንድ አውጣ፤ ከዚያ በኋላ በወንድምህ ዐይን ውስጥ ያለውን ጕድፍ ለማውጣት አጥርተህ ታያለህ።
ሉቃስ 6:17-42 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከእነርሱም ጋር ወርዶ በሰፊ ቦታ ቆመ፤ ከደቀ መዛሙርቱም ወገን ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ከመላው ይሁዳና ከኢየሩሳሌም፥ ከጢሮስና ከሲዶና ባሕር ዳርቻ ትምህርቱን ሊሰሙ፥ ከደዌአቸውም ሊፈወሱ የመጡት ከሕዝቡ ወገን እጅግ ብዙዎች ነበሩ። ክፉዎች አጋንንት ያደሩባቸውም ይፈወሱ ነበር። ሕዝቡ ሁሉ ሊዳስሱት ይሹ ነበር፤ ኀይል ከእርሱ ይወጣ ነበርና፥ ሁሉንም ይፈውሳቸው ነበር። እርሱም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዐይኖቹን አንሥቶ እንዲህ አላቸው፥ “እናንተ ድሆች፥ ብፁዓን ናችሁ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት የእናንተ ናትና። ዛሬ የምትራቡ፥ ብፁዓን ናችሁ፤ ትጠግባላችሁና፤ ዛሬ የምታለቅሱ፥ ብፁዓን ናችሁ፤ ትስቃላችሁና። ሰዎች ስለ ሰው ልጅ ቢጠሉአችሁ፥ ከሰው ለይተው ቢአሳድዱአችሁ፥ ቢሰድቡአችሁ፥ ክፉ ስምም ቢአወጡላችሁ ብፁዓን ናችሁ። ያንጊዜ ደስ ይበላችሁ፤ በደስታም ዝለሉ፤ ዋጋችሁ በሰማይ ብዙ ነውና፤ አባቶቻቸውም ነቢያትን እንዲሁ አድርገዋቸው ነበርና። ነገር ግን እናንተ ባለጠጎች፥ ወዮላችሁ፥ ደስታችሁን ጨርሳችኋልና። ዛሬ ለምትጠግቡ፥ ወዮላችሁ፥ ትራባላችሁና፤ ዛሬ ለምትስቁም ወዮላችሁ፥ ታዝናላችሁና፤ ታለቅሳላችሁምና። ሰዎች ሁሉ ስለ እናንተ መልካሙን ነገር ቢናገሩላችሁ ወዮላችሁ፥ አባቶቻቸው ለሐሰተኞች ነቢያት እንዲህ ያደርጉ ነበርና። “ለምትሰሙኝ ለእናንተ ግን እንዲህ እላችኋለሁ፦ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ። የሚረግሙአችሁን መርቁአቸው፤ ለሚበድሉአችሁም ጸልዩላቸው። ጕንጭህን ለሚመታህም ሁለተኛይቱን ስጠው፤ መጐናጸፊያህን ለሚወስድም ቀሚስህን ደግሞ አትከልክለው። ለሚለምንህም ሁሉ ስጥ፤ ገንዘብህን የሚወስደውንም እንዲመልስ አትጠይቀው። ሰዎች ሊያደርጉላችሁ እንደምትወዱትም እንዲሁ እናንተ አድርጉላቸው። የሚወድዱአችሁን ብቻ ብትወዱማ እንግዲህ ዋጋችሁ ምንድን ነው? ይህንስ ኃጥኣንም ያደርጋሉ፤ የሚወድዳቸውንም ይወድዳሉ። በጎ ለሚያደርጉላችሁ በጎ ብታደርጉ እንግዲህ ዋጋችሁ ምንድን ነው? እንዲህስ ኃጥኣንም ያደርጋሉ። እንዲከፍላችሁ ተስፋ ለምታደርጉት ብታበድሩ እንግዲህ ዋጋችሁ ምንድን ነው? ኃጥኣንም በአበደሩት ልክ ይከፍሉአቸው ዘንድ ለኃጥኣን ያበድራሉና። አሁንም ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ መልካምም አድርጉላቸው፤ እንዲመልሱላችሁ ተስፋ ሳታደርጉ አበድሩ፤ ዋጋችሁም ብዙ ይሆናል፤ የልዑልም ልጆች ትሆናላችሁ፤ እርሱ ለበጎዎችና ለክፉዎች ቸር ነውና። ሰማያዊ አባታችሁ የሚራራ እንደ ሆነ እናንተም የምትራሩ ሁኑ። አትፍረዱ፥ አይፈረድባችሁምም፤ አትበድሉ፥ አይበድሉአችሁምም፤ ይቅር በሉ፥ ይቅርም ይሉአችኋል። ስጡ፥ ይሰጣችኋልም፤ የሞላና የበዛ፥ የተትረፈረፈም መልካም መስፈሪያ በዕቅፋችሁ ይሰጡአችኋል፤ በሰፈራችሁበትም መስፈሪያ ይሰፍሩላችኋል።” ምሳሌም መሰለላቸውና እንዲህ አላቸው፥ “ዕውር ዕውርን ሊመራ ይችላልን? ሁለቱስ በጕድጓድ ውስጥ ይወድቁ የለምን? ከመምህሩ የሚበልጥ ደቀ መዝሙር የለም፤ ለሁሉም መጠኑ እንደ መምህሩ ይሆናል። በወንድምህ ዐይን ውስጥ ያለውን ጕድፍ ለምን ታያለህ? በዐይንህ ውስጥ ያለውን ምሰሶ አታይምን? ወንድምህንም፦ ወንድሜ ሆይ፥ ታገሥ፤ በዐይንህ ያለውን ጕድፍ ላውጣልህ ልትለው እንደምን ትችላለህ? አንተ ግን በዐይንህ ውስጥ ያለውን ምሰሶ አታይም፤ አንተ ግብዝ፥ አስቀድሞ ከዐይንህ ምሰሶውን አውጣ፤ ከዚህ በኋላ በባልንጀራህ ዐይን ውስጥ ያለውን ጕድፍ ታወጣ ዘንድ አጥርተህ ታያለህ።
ሉቃስ 6:17-42 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከእነርሱም ጋር ወርዶ በተካከለ ስፍራ ቆመ፥ ከደቀ መዛሙርቱም ወገን ብዙ ሕዝብ ነበረ፥ ደግሞም ሊሰሙትና ከደዌአቸው ሊፈወሱ ከይሁዳ ሁሉ ከኢየሩሳሌምም ከጢሮስና ከሲዶና ባሕር ዳርም የመጡ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ከርኵሳንም መናፍስት ይሠቃዩ የነበሩት ተፈወሱ፤ ከእርሱም ኃይል ወጥቶ ሁሉን ይፈውስ ነበርና ሕዝቡ ሁሉ ሊዳስሱት ይሹ ነበር። እርሱም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዓይኑን አነሣ እንዲህም አላቸው፦ እናንተ ድሆች ብፁዓን ናችሁ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት የእናንተ ነውና። እናንተ አሁን የምትራቡ ብፁዓን ናችሁ፥ ትጠግባላችሁና። እናንተ አሁን የምታለቅሱ ብፁዓን ናችሁ፥ ትስቃላችሁና። ሰዎች ስለ ሰው ልጅ ሲጠሉአችሁ ሲለዩአችሁም ሲነቅፉአችሁም ስማችሁንም እንደ ክፉ ሲያወጡ፥ ብፁዓን ናችሁ። እነሆ፥ ዋጋችሁ በሰማይ ታላቅ ነውና በዚያን ቀን ደስ ይበላችሁ ዝለሉም፤ አባቶቻቸው ነቢያትን እንዲህ ያደርጉባቸው ነበርና። ነገር ግን እናንተ ባለ ጠጎች ወዮላችሁ፥ መጽናናታችሁን ተቀብላችኋልና። እናንተ አሁን የጠገባችሁ ወዮላችሁ፥ ትራባላችሁና። እናንተ አሁን የምትስቁ ወዮላችሁ፥ ታዝናላችሁና ታለቅሱማላችሁ። ሰዎች ሁሉ መልካም ሲናገሩላችሁ፥ ወዮላችሁ፤ አባቶቻቸው ለሐሰተኞች ነቢያት እንዲሁ ያደርጉላቸው ነበርና። ነገር ግን ለእናንተ ለምትሰሙ እላችኋለሁ፥ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ ለሚጠሉአችሁ መልካም አድርጉ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ስለሚበድሉአችሁም ጸልዩ። ጕንጭህን ለሚመታህ ደግሞ ሁለተኛውን ስጠው፥ መጐናጸፊያህንም ለሚወስድ እጀ ጠባብህን ደግሞ አትከልክለው። ለሚለምንህ ሁሉ ስጥ፥ ገንዘብህንም የሚወስድ እንዲመልስ አትጠይቀው። ሰዎችም ሊያደርጉላችሁ እንደምትወዱ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው። የሚወዱአችሁንማ ብትወዱ፥ ምን ምስጋና አላችሁ? ኃጢአተኞች ደግሞ የሚወዱአቸውን ይወዳሉና። መልካምም ለሚያደርጉላችሁ መልካም ብታደርጉ፥ ምን ምስጋና አላችሁ? ኃጢአተኞች ደግሞ ያን ያደርጋሉና። እንድትወስዱባቸው ተስፋ ለምታደርጉአቸው ብታበድሩ፥ ምን ምስጋና አላችሁ? ኃጢአተኞች ደግሞ በትክክል እንዲቀበሉ ለኃጢአተኞች ያበድራሉ። ነገር ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ መልካም አድርጉ፤ ምንም ተስፋ ሳታደርጉም አበድሩ፥ ዋጋችሁም ታላቅ ይሆናል፥ የልዑልም ልጆች ትሆናላችሁ፥ እርሱ ለማያመሰግኑ ለክፉዎችም ቸር ነውና። አባታችሁ ርኅሩኅ እንደ ሆነ ርኅሩኆች ሁኑ። አትፍረዱ አይፈረድባችሁምም፤ አትኰንኑ አትኰነኑምም። ይቅር በሉ ይቅርም ትባላላችሁ። ስጡ ይሰጣችሁማል፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ተመልሶ ይሰፈርላችኋልና፥ የተጨቈነና የተነቀነቀ የተትረፈረፈም መልካም መስፈሪያ በእቅፋችሁ ይሰጣችኋል። ምሳሌም አላቸው፦ ዕውር ዕውርን ሊመራ ይችላልን? ሁለቱ በጕድጓድ አይወድቁምን? ደቀ መዝሙር ከመምህሩ አይበልጥም፤ ፈጽሞ የተማረ ሁሉ ግን እንደ መምህሩ ይሆናል። በወንድምህም ዓይን ያለውን ጉድፍ ስለ ምን ታያለህ፥ በራስህ ዓይን ግን ያለውን ምሰሶ ስለ ምን አትመለከትም? በዓይንህ ያለውን ምሰሶ ራስህ ሳታይ፥ እንዴት ወንድምህን፦ ወንድሜ ሆይ፥ በዓይንህ ያለውን ጉድፍ ላውጣ ፍቀድልኝ ልትል ትችላለህ? አንተ ግብዝ፥ አስቀድመህ ከዓይንህ ምሰሶውን አውጣ ከዚያም በኋላ በወንድምህ ዓይን ያለውን ጉድፍ ታወጣ ዘንድ አጥርተህ ታያለህ።
ሉቃስ 6:17-42 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር ከተራራው ወርዶ በሜዳ ላይ ቆመ፤ ከደቀ መዛሙርቱም ብዙዎቹ በዚያ ነበሩ፤ እንዲሁም ሊሰሙትና ከበሽታቸው ሊፈወሱ ፈልገው የመጡ፥ እጅግ ብዙ ሕዝብ ነበሩ። እነርሱም የመጡት ከይሁዳ ምድር ከኢየሩሳሌም ከተማ፥ በባሕር አጠገብ ከሚገኙት ከጢሮስና ከሲዶና ከተሞች ነበር። በርኩሳን መናፍስት ተይዘው ይታወኩ የነበሩት ሰዎችም መጥተው ይፈወሱ ነበር። የማዳን ኀይል ከእርሱ እየወጣ ሁሉንም ይፈውስ ስለ ነበር የተሰበሰቡት ሰዎች ሁሉ ኢየሱስን ለመንካት ይፈልጉ ነበር። ኢየሱስ ቀና ብሎ ወደ ደቀ መዛሙርቱ እየተመለከተ እንዲህ አላቸው፦ “የእግዚአብሔር መንግሥት የእናንተ ናትና፥ እናንተ ድኾች የተባረካችሁ ናችሁ! እናንተ አሁን የምትራቡ፥ በኋላ ትጠግባላችሁና የተባረካችሁ ናችሁ! እናንተ አሁን የምታለቅሱ፥ በኋላ ትስቃላችሁና የተባረካችሁ ናችሁ፤ “በእኔ በሰው ልጅ ምክንያት ሰዎች ሲጠሉአችሁ፥ ሲለዩአችሁ፥ ሲያንቋሽሹአችሁና ስማችሁን ሲያጠፉ የተባረካችሁ ናችሁ! በሰማይ ዋጋችሁ ትልቅ ነውና ይህ ሁሉ ሲደርስባችሁ የተባረካችሁ ናችሁ! ሐሴትም አድርጉ፤ የቀድሞ አባቶቻቸውም በነቢያት ላይ እንዲህ ያለውን ክፋት አድርገውባቸው ነበር። “እናንተ ሀብታሞች ግን ለምቾታችሁ የሚሆነውን ሁሉ አሁን አግኝታችኋልና ወዮላችሁ! “እናንተ አሁን የጠገባችሁ፥ ኋላ ትራባላችሁና ወዮላችሁ! እናንተ አሁን የምትስቁ፥ ኋላ ስለምታዝኑና ስለምታለቅሱ ወዮላችሁ! “ሰዎች ሁሉ ስለ እናንተ መልካም ሲናገሩ ወዮላችሁ! አባቶቻቸውም ለሐሰተኞች ነቢያት እንዲሁ አድርገው ነበር። “ለእናንተ ለምትሰሙኝ ግን እንዲህ እላችኋለሁ፤ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ ለሚጠሉአችሁም መልካም ነገር አድርጉ፤ የሚረግሙአችሁን መርቁ፤ ለሚበድሉአችሁም ጸልዩላቸው፤ አንዱን ጒንጭህን በጥፊ ለሚመታህ፥ ሌላውንም ጒንጭህን እንዲመታ አዙርለት፤ ነጠላህን ለሚወስድብህ፥ እጀ ጠባብህንም ጨምረህ ስጠው፤ ለሚለምንህ ሁሉ ስጥ፤ ንብረትህን የሚወስድብህን ሰው እንዲመልስ አትጠይቀው። ሰዎች ለእናንተ ሊያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን እናንተም እንዲሁ ለእነርሱ አድርጉላቸው። “የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ብልጫ ታገኛላችሁ! ኃጢአተኞችም የሚወዱአቸውን ይወዳሉ፤ መልካም ነገር ለሚያደርጉላችሁ እናንተም መልካም ነገር ብታደርጉላቸው ምን ብልጫ ታገኛላችሁ! ኃጢአተኞችም እንዲሁ ያደርጋሉ፤ ‘ይመልሱልናል’ ብላችሁ ለምታስቡአቸው ሰዎች ብታበድሩ ምን ብልጫ ታገኛላችሁ? ያንኑ ያበደሩትን መልሰው ለመቀበልማ ኃጢአተኞችም ለኃጢአተኞች ያበድራሉ። እናንተ ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ! መልካም ነገርም አድርጉላቸው፤ ‘ብድራችን ይመለስልናል’ ብላችሁ ተስፋ ሳታደርጉ አበድሩ፤ ይህን ብታደርጉ ዋጋችሁ ትልቅ ይሆናል፤ የልዑል እግዚአብሔር ልጆችም ትሆናላችሁ፤ እርሱ ለውለታ ቢሶችና ለክፉዎች እንኳ ሳይቀር ቸር ነው። የሰማይ አባታችሁ መሓሪ እንደ ሆነ እናንተም እንዲሁ መሓሪዎች ሁኑ። “በማንም ላይ አትፍረዱ፤ በእናንተም ላይ አይፈረድባችሁም፤ ሌሎችን አትንቀፉ፤ እናንተም አትነቀፉም፤ ይቅር በሉ፤ እናንተም ይቅርታ ታገኛላችሁ፤ ስጡ፤ ለእናንተም ይሰጣችኋል፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ እንዲሁ ይሰፈርላችኋል፤ እንዲያውም በጥሩ መስፈሪያ ታምቆና ተጠቅጥቆ እስኪትረፈረፍ ድረስ ተሰፍሮ ይሰጣችኋል።” ቀጥሎም ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፦ “ ዕውር ዕውርን ሊመራ ይችላልን? እንዲህማ ቢያደርግ ሁለቱም ተያይዘው በጒድጓድ ውስጥ ይወድቃሉ። ተማሪ ከአስተማሪው አይበልጥም፤ ይሁን እንጂ ተማሪ ትምህርቱን በደንብ ከተማረ እንደ አስተማሪው ይሆናል። “በአንተ ዐይን ያለውን ግንድ ሳታይ ስለምን በወንድምህ ዐይን ያለውን ጒድፍ ትመለከታለህ? ደግሞስ በአንተ ዐይን ያለውን ግንድ ሳታይ ወንድምህን ‘ወንድሜ ሆይ፥ እስቲ በዐይንህ ያለውን ጒድፍ ላውጣልህ፤’ ማለት እንዴት ትችላለህ? አንተ ግብዝ፥ አስቀድመህ በአንተ ዐይን ያለውን ግንድ አውጣ፤ ከዚህ በኋላ በወንድምህ ዐይን ያለውን ጒድፍ ለማውጣት አጥርተህ ማየት ትችላለህ።
ሉቃስ 6:17-42 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከእነርሱም ጋር ወርዶ በሜዳማ ስፍራ ቆመ፤ ከደቀ መዛሙርቱም ወገን ብዙ ሕዝብ ነበረ፤ እንዲሁም ከይሁዳ ሁሉ ከኢየሩሳሌምም፥ ከጢሮስና ከሲዶና ባሕር ዳርም እጅግ ብዙ ሰዎች እርሱን ሊሰሙትና ከደዌአቸው ሊፈወሱ የመጡ ነበሩ፤ በርኩሳንም መናፍስት ይሠቃዩ የነበሩት ሰዎች ተፈወሱ፤ ከእርሱም ኃይል ወጥቶ ሁሉን ይፈውስ ነበርና ሕዝቡ ሁሉ ሊዳስሱት ይሹ ነበር። እርሱም ወደ ደቀመዛሙርቱ ዐይኑን አነሣ፤ እንዲህም አለ፦ “እናንተ ድሆች ብፁዓን ናችሁ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት የእናንተ ነውና።” እናንተ አሁን የምትራቡ ብፁዓን ናችሁ፤ ትጠግባላችሁና። እናንተ አሁን የምታለቅሱ ብፁዓን ናችሁ፤ ትስቃላችሁና። ሰዎች ስለ ሰው ልጅ ሲጠሉአችሁ፥ ሲለዩአችሁና ሲነቅፉአችሁ፥ በክፉም ስማችሁን ሲያጠፉ ብፁዓን ናችሁ! እነሆ፥ ዋጋችሁ በሰማይ ታላቅ ነውና፤ በዚያን ቀን ተደሰቱ፤ በደስታም ዝለሉ፤ አባቶቻቸው ነቢያትን እንዲህ ያደርጉባቸው ነበርና። ነገር ግን እናንተ ባለ ጠጎች ወዮላችሁ! መጽናናታችሁን ተቀብላችኋልና። እናንተ አሁን የጠገባችሁ ወዮላችሁ! ትራባላችሁና። እናንተ አሁን የምትስቁ ወዮላችሁ! ታዝናላችሁ እንባንም ታፈሳላችሁና። ሰዎች ሁሉ ስለ እናንተ መልካም ሲናገሩ ወዮላችሁ! አባቶቻቸው ለሐሰተኞች ነቢያት እንዲሁ ያደርጉ ነበርና። “ነገር ግን ለእናንተ ለምትሰሙ እላችኋለሁ፤ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ ለሚጠሉአችሁ መልካም አድርጉ፤ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፤ ስለሚበድሉአችሁም ጸልዩ። ጉንጭህን ለሚመታህ ሌላውን ጉንጭህን ደግሞ ስጠው፤ መጐናጸፊያህንም ለሚወስድ እጀ ጠባብህን እንኳ አትከልክለው። ለሚለምንህ ሁሉ ስጥ፤ ንብረትህንም የሚወስድብህን ሰው እንዲመልስ አትጠይቀው። እንዲሁም ሰዎች ለእናንተ እንዲያደርጉላችሁ የምትወድዱትን ነገር እናንተ ለእነርሱ እንዲሁ አድርጉላቸው። “የሚወዱአችሁንማ ብትወዱ ምስጋናችሁ ምንድነው? ኀጢአተኞች እንኳ የሚወዱአቸውን ይወዳሉና። መልካምም ለሚያደርጉላችሁ መልካም ብታደርጉ ምስጋናችሁ ምንድነው? ኀጢአተኞች እንኳ ያን ያደርጋሉና። ልትቀበሉአቸው ተስፋ የምታደርጉአቸውን ሰዎች ብታበድሩ ምስጋናችሁ ምንድነው? ኀጢአተኞች እንኳ ባበደሩት ዋጋ ልክ እንዲመለስላቸው ለኀጢአተኞች ያበድራሉ። ነገር ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ መልካምም አድርጉ፤ ይመለስልናልም ብላችሁ ምንም ተስፋ ሳታደርጉ አበድሩ፤ ዋጋችሁም ታላቅ ይሆናል፤ የልዑልም ልጆች ትሆናላችሁ፤ እርሱ ለማያመሰግኑና ለክፉዎች ቸር ነውና። አባታችሁ ርኅሩኅ እንደሆነ ርኅሩኆች ሁኑ። “አትፍረዱ እንዳይፈረድባችሁም፤ አትኰንኑ እንዳትኰነኑም። ይቅር በሉ ይቅርም ትባላላችሁ፤ ስጡ ይሰጣችኋልም፤ በመልካምም መስፈሪያ የተጠቀጠቀና የተነቀነቀ የተትረፈረፈም በእቅፋችሁ ይሰጣችኋል፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ተመልሶ ይሰፈርላችኋልና።” እርሱም ይህን ምሳሌ ነገራቸው፦ “ዐይነ ስውር ዐይነ ስውርን መምራት ይችላልን? ሁለቱም በጉድጓድ አይወድቁምን? ደቀመዝሙር ከመምህሩ አይበልጥም፤ ፈጽሞ የተማረ ሁሉ ግን እንደ መምህሩ ይሆናል። በወንድምህም ዐይን ያለውን ጉድፍ ስለምን ታያለህ? በራስህ ዐይን ግን ያለውን ምሰሶ ስለምን አትመለከትም? አንተ ራስህ በዐይንህ ያለውን ምሰሶ ሳታይ እንዴት ወንድምህን፦ ‘ወንድሜ ሆይ! በዐይንህ ያለውን ጉድፍ እዳወጣ ፍቀድልኝ፤’ ልትል ትችላለህ? አንተ ግብዝ፤ አስቀድመህ ከዐይንህ ምሰሶውን አውጣ፤ ከዚያም በኋላ በወንድምህ ዐይን ያለውን ጉድፍ ለማውጣት አጥርተህ ታያለህ።”