የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 13:44-53

የማቴዎስ ወንጌል 13:44-53 አማ05

ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “መንግሥተ ሰማይ በእርሻ ውስጥ የተሸሸገውን ሀብት ትመስላለች። አንድ ሰው ይህን ሀብት ባገኘው ጊዜ መልሶ ደበቀው፤ ከደስታውም ብዛት የተነሣ ሄደና ያለውን ሁሉ ሸጦ ያንን እርሻ ገዛ።” እንደገናም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ደግሞ መንግሥተ ሰማይ ጥሩ ዕንቊ ለመግዛት የሚፈልግ ነጋዴን ትመስላለች፤ ነጋዴውም እጅግ ክቡር የሆነ ዕንቊ ባገኘ ጊዜ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ያንን ዕንቊ ገዛ።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “እንዲሁም መንግሥተ ሰማይ ወደ ባሕር የተጣለች መረብን ትመስላለች፤ እርስዋ በየዐይነቱ ዓሣ የምትሰበስብ ናት፤ በሞላች ጊዜ ዓሣ አጥማጆቹ ወደ ባሕሩ ዳር ጐትተው ያወጡአታል፤ ተቀምጠውም መልካም መልካሙን መርጠው በዕቃ ያስቀምጣሉ፤ መጥፎ መጥፎውን ግን ወዲያ ይጥላሉ። በዓለም መጨረሻም እንዲህ ይሆናል፤ መላእክት መጥተው ኃጢአተኞችን ከጻድቃን ይለዩአቸዋል። ክፉዎችን ወደ እቶን እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።” ደግሞም ኢየሱስ፦ “ይህን ሁሉ አስተዋላችሁን?” አላቸው። እነርሱም “አዎን ጌታ ሆይ!” አሉ። እርሱም “እንግዲያውስ የመንግሥተ ሰማይን ምሥጢር ጠንቅቆ የሚያውቅ የሕግ መምህር፦ ከዕቃ ግምጃ ቤቱ አዲስ የሆነውንና አሮጌ የሆነውን ዕቃ የሚያመጣ የንብረት ባለቤትን ይመስላል” ሲል መለሰላቸው። ኢየሱስ እነዚህን ምሳሌዎች ተናግሮ ካበቃ በኋላ፥ ከዚያ ስፍራ ሄደ።