ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፥ “እኔ ሕዝቡን እስካሰናብት ድረስ በጀልባ ተሳፈሩና ቀድማችሁኝ ወደ ማዶ ተሻገሩ፤” ሲል አዘዛቸው። ሕዝቡንም ካሰናበተ በኋላ ለመጸለይ ብቻውን ወደ አንድ ተራራ ላይ ወጣ፤ በመሸም ጊዜ ኢየሱስ እዚያ ብቻውን ነበር። በዚያን ጊዜ ጀልባዋ በባሕሩ መካከል ሆና ከምትሄድበት አቅጣጫ በተቃራኒ በሚነፍሰው ነፋስ እየተመታች ማዕበሉ ወዲያና ወዲህ ያንገላታት ነበር። ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት በኋላ ኢየሱስ በባሕር ላይ እየተራመደ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጣ። ደቀ መዛሙርቱም በባሕሩ ላይ እየተራመደ ሲሄድ ባዩት ጊዜ በጣም ፈርተው ደነገጡ፤ “ይህ ምትሐት ነው!” ብለውም በፍርሃት ጮኹ። ኢየሱስም ወዲያውኑ “አይዞአችሁ! እኔ ነኝ፤ አትፍሩ!” አላቸው። በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ፥ “ጌታ ሆይ! አንተስ ከሆንክ በባሕሩ ላይ እየተራመድኩ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ!” አለው። ኢየሱስም “ና!” አለው። ስለዚህ ጴጥሮስ ከጀልባው ወርዶ ወደ ኢየሱስ ለመሄድ በባሕሩ ላይ ተራመደ። ነገር ግን የነፋሱን ኀይል አይቶ ፈራ፤ ወደ ባሕሩ ውስጥ መስጠም በጀመረ ጊዜ “ጌታ ሆይ! አድነኝ!” ሲል ጮኸ። ኢየሱስ ወዲያውኑ እጁን ዘርግቶ ያዘውና፦ “አንተ እምነት የጐደለህ! ስለምን ተጠራጠርክ?” አለው። ኢየሱስና ጴጥሮስ ወደ ጀልባው በገቡ ጊዜ ነፋሱ ጸጥ አለ። በጀልባውም ውስጥ የነበሩት ሁሉ “በእርግጥ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ!” ብለው ለኢየሱስ ሰገዱለት።
የማቴዎስ ወንጌል 14 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማቴዎስ ወንጌል 14:22-33
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች