የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 27

27
ኢየሱስ ወደ ጲላጦስ መወሰዱ
(ማር. 15፥1ሉቃ. 23፥1-2ዮሐ. 18፥28-32)
1ጠዋት በማለዳ የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሌዎች ሁሉ በኢየሱስ ላይ የሞት ፍርድ ለማስፈረድ ተማከሩ። 2ከዚህ በኋላ ኢየሱስን አስረው ወሰዱና ለገዥው ለጲላጦስ አሳልፈው ሰጡት።
3ኢየሱስ እንደተፈረደበት ባየ ጊዜ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ ተጸጸተ፤ ሠላሳውንም ጥሬ ብር ለካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች እንዲህ በማለት መልሶ ሰጣቸው፤ 4“ንጹሑን ሰው ለሞት አሳልፌ በመስጠቴ በድዬአለሁ።” እነርሱ ግን “ታዲያ፥ እኛ ምን ቸገረን! የራስህ ጉዳይ ነው!” አሉት። 5እርሱም ሠላሳውን ጥሬ ብር በቤተ መቅደስ ውስጥ በትኖ፥ ትቶአቸው ወጣ፤ ሄዶም ታንቆ ሞተ።
6የካህናት አለቆች ሠላሳውን ጥሬ ብር አንሥተው “ይህ ገንዘብ የደም ዋጋ ስለ ሆነ ከቤተ መቅደስ መባ ጋር ልንቀላቅለው አይፈቀድም” አሉ። 7ስለዚህ ከተመካከሩ በኋላ ለእንግዶች የመቃብር ቦታ እንዲሆን የሸክላ ሠሪውን መሬት ገዙበት። 8በዚህ ምክንያት ያ መሬት እስከ ዛሬ ድረስ “የደም መሬት” እየተባለ ይጠራል። #ሐ.ሥ. 1፥18-19።
9በዚህ ሁኔታ “የእስራኤል ልጆች የገመቱትን ለእርሱ ዋጋ የሚሆን ሠላሳ ጥሬ ብር ወሰዱ፤ 10ጌታም እንዳዘዘኝ ስለ ሸክላ ሠሪው መሬት ከፈሉት” ተብሎ በነቢዩ ዘካርያስ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ። #ዘካ. 11፥12-13።
ኢየሱስ ወደ ጲላጦስ መቅረቡ
(ማር. 15፥2-5ሉቃ. 23፥3-5ዮሐ. 18፥33-38)
11በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ወደ ገዢው ወደ ጲላጦስ ፊት ቀረበ፤ ገዢውም “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ሲል ጠየቀው፤ ኢየሱስም “አንተ እንዳልከው ነው” ሲል መለሰ። 12ነገር ግን የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች ሲወነጅሉት ምንም መልስ አልሰጠም። 13ከዚህ በኋላ ጲላጦስ “በስንት ነገር ሲወነጅሉህ አትሰማምን?” አለው። 14ኢየሱስ ግን ገዢው እስኪደነቅ ድረስ ለአንዲት ክስ እንኳ ቃል አልመለሰለትም።
ኢየሱስ የሞት ፍርድ እንደተፈረደበት
(ማር. 15፥6-15ሉቃ. 23፥13-25ዮሐ. 18፥39-4019፥1-16)
15ገዢው በየዓመቱ በአይሁድ ፋሲካ በዓል ጊዜ እንዲፈታላቸው ሕዝቡ የጠየቁትን አንድ እስረኛ ፈቶ መልቀቅ አስለምዶ ነበር። 16በዚያን ጊዜ “በርባን” የተባለ በዓመፀኛነቱ የታወቀ እስረኛ ነበረ። 17ስለዚህ ሰዎቹ በተሰበሰቡ ጊዜ ጲላጦስ፥ “ማንን እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ? በርባንን ነውን ወይስ መሲሕ የተባለውን ኢየሱስን?” ሲል ጠየቃቸው። 18ይህን ያለበት ምክንያት ኢየሱስን በቅናት አሳልፈው እንደ ሰጡት ያውቅ ስለ ነበር ነው። 19ከዚህም በላይ ጲላጦስ በፍርድ ወንበር ተቀምጦ ሳለ ሚስቱ፦ “በእርሱ ምክንያት ዛሬ ሌሊት በሕልም ብዙ ተሠቃይቻለሁና በዚያ በንጹሕ ሰው ላይ ምንም እንዳታደርግ” ስትል ላከችበት። 20በዚያን ጊዜ የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች “በርባን ይለቀቅ! ኢየሱስ ይገደል!” ብለው እንዲጠይቁ ሕዝቡን አግባቡ። 21ገዢውም “ከሁለቱ የትኛውን እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ?” ሲል ሕዝቡን እንደገና ጠየቀ። እነርሱም “በርባንን እንድትፈታልን እንፈልጋለን” ሲሉ መለሱ። 22ጲላጦስም “ታዲያ፥ መሲሕ የተባለውን ኢየሱስን ምን ላድርገው?” አላቸው። ሁሉም “ይሰቀል!” ሲሉ መለሱ። 23ገዢውም ለምን? “እርሱ ያደረገው በደል ምንድን ነው?” አላቸው። እነርሱ ግን “ይሰቀል!” እያሉ አብዝተው ጮኹ። 24ስለዚህ ጲላጦስ ይህ ነገር ሁከት እንደሚያስነሣ እንጂ ሌላ ምንም እንደማይጠቅም ባየ ጊዜ ውሃ አስመጥቶ “እኔ ለዚህ ሰው ሞት ኀላፊ አይደለሁም፤ ኀላፊነቱ የእናንተ ነው!” ብሎ በሕዝቡ ፊት እጁን ታጠበ። #ዘዳ. 21፥6-9።
25ሕዝቡም ሁሉ “በእርሱ ሞት ምክንያት የሚመጣው ቅጣት በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን” አሉ።
26በዚያን ጊዜ ጲላጦስ በርባንን ፈቶ ለቀቀላቸው፤ ኢየሱስን ግን ካስገረፈው በኋላ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጣቸው።
የወታደሮቹ በኢየሱስ ላይ ማፌዝ
(ማር. 15፥16-20ዮሐ. 19፥2-3)
27በዚያን ጊዜ የገዢው ወታደሮች ኢየሱስን ወደ ገዢው ግቢ ወሰዱት፤ ወታደሮቹንም ሁሉ በኢየሱስ ዙሪያ ሰበሰቡ። 28ልብሱንም ገፈው ቀይ ልብስ አለበሱት። 29የእሾኽ አክሊልም ጐንጒነው በራሱ ላይ ደፉበት፤ በቀኝ እጁም የመቃ ዘንግ አስያዙት፤ በፊቱም እየተንበረከኩ “የአይሁድ ንጉሥ ሆይ! ሰላም ለአንተ ይሁን!” እያሉ ያፌዙበት ነበር፤ 30ምራቃቸውንም ይተፉበት ነበር፤ ዘንጉንም ከእጁ ወስደው ራስ ራሱን ይመቱት ነበር። 31ካፌዙበት በኋላ ቀዩን ልብስ አውልቀው የራሱን ልብስ አለበሱት፤ ሊሰቅሉትም ይዘውት ሄዱ።
የኢየሱስ መሰቀል
(ማር. 15፥21-32ሉቃ. 23፥26-43ዮሐ. 19፥17-27)
32ከገዢው ግቢ ሲወጡ ሳሉ ስምዖን የተባለውን የቀሬና አገር ሰው አገኙና የኢየሱስን መስቀል እንዲሸከም አስገደዱት። 33ከዚህ በኋላ ትርጒሙ “የራስ ቅል” ወደ ሆነው ወደ ጎልጎታ ደረሱ። 34በዚያም ከሐሞት ጋር የተቀላቀለ የወይን ጠጅ እንዲጠጣ ለኢየሱስ አቀረቡለት፤ እርሱ ግን ቀመስ አድርጎ ሊጠጣው አልፈለገም። #መዝ. 69፥21። 35ኢየሱስን ከሰቀሉት በኋላ ልብሱን ዕጣ ተጣጥለው ተካፈሉ። #መዝ. 22፥18። 36በዚያም ተቀምጠው ይጠብቁት ነበር። 37የተከሰሰበትንም ወንጀል የሚያመለክት፥ “ይህ የአይሁድ ንጉሥ ኢየሱስ ነው?” የሚል ጽሑፍ በመስቀሉ ራስጌ ላይ አኖሩ። 38በዚያን ጊዜ ከኢየሱስ ጋር ሁለት ወንበዴዎችን አንዱን በቀኝ አንዱን በግራ ሰቀሉ።
39በአጠገቡ ያልፉ የነበሩትም ሰዎች በንቀት ራሳቸውን እየነቀነቁ፥ #መዝ. 22፥7፤ 109፥25። 40“አንተ ቤተ መቅደስን የምታፈርስና በሦስት ቀን የምትሠራው! እስቲ ራስህን አድን! የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ እስቲ ከመስቀል ውረድ!” በማለት ያላግጡበት ነበር። #ማቴ. 26፥61፤ ዮሐ. 2፥19።
41በዚሁም ዓይነት የካህናት አለቆች ከሕግ መምህራንና ከሽማግሌዎች ጋር እንዲህ እያሉ ያፌዙበት ነበር፤ 42“ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ግን ማዳን አይችልም! እርሱ የእስራኤል ንጉሥ ከሆነ እስቲ አሁን ከመስቀል ይውረድ፤ እኛም እንመንበት! 43እርሱ በእግዚአብሔር ታምኖአል፤ ‘የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ’ ብሎአል፤ ስለዚህ እግዚአብሔር የሚወደው ከሆነ እስቲ አሁን ያድነው!” #መዝ. 22፥8። 44እንዲሁም ከእርሱ ጋር የተሰቀሉት ወንበዴዎች ይሰድቡት ነበር።
የኢየሱስ ሞት
(ማር. 15፥33-41ሉቃ. 23፥44-49ዮሐ. 19፥28-30)
45ከስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ጨለማ ሆነ። 46ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን ኢየሱስ፦ “ኤሎሄ! ኤሎሄ! ላማ ሰበቅታኒ?” ሲል በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ትርጓሜውም “አምላኬ! አምላኬ! ለምን ተውከኝ?” ማለት ነው። #መዝ. 22፥1። 47በዚያም ቆመው ከነበሩት ሰዎች አንዳንዶቹ ይህን ሰምተው “ይህስ ኤልያስን ይጠራል!” አሉ። 48በዚያን ጊዜ ከእነርሱ አንዱ ሰፍነግ አምጥቶ ሆምጣጤ ሞላበት፤ በመቃ ላይ አድርጎም ኢየሱስ እንዲጠጣ አቀረበለት። #መዝ. 69፥21። 49ሌሎች ግን “ቈይ እስቲ ኤልያስ መጥቶ ያድነው እንደ ሆነ እንይ!” አሉ። 50ኢየሱስ እንደገና በታላቅ ድምፅ ጮኸና ነፍሱን ሰጠ። #27፥50 ሰፍነግ፦ እንደ ኳስ ክብ ሆኖ በባሕር ውስጥ የሚበቅል ብቋያ፥ ሁለንተናው ዐይን ውሃ መጣጭ የባሕር እንጒዳይ ዐይነ በጎ መሳይ ውሃ መጦ ሊይዝ የሚችል ለስላሳ ነገር ነው።
51በዚያን ጊዜ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ተቀዶ ከሁለት ተከፈለ፤ ምድርም ተናወጠች፤ አለቶችም ተሰነጠቁ፤ #ዘፀ. 26፥31-33። 52መቃብሮችም ተከፍተው ሞተው ከነበሩት ቅዱሳን ሰዎች ብዙዎች ከሞት ተነሡ። 53ከመቃብርም ወጡና ኢየሱስ ከሞት ከተነሣ በኋላ ወደ ቅድስት ከተማ ወደ ኢየሩሳሌም ገቡ፤ በዚያም ለብዙ ሰዎች ታዩ። 54የመቶ አለቃውና ከእርሱም ጋር ኢየሱስን ይጠብቁ የነበሩት የምድርን መናወጥና የሆነውንም ነገር ባዩ ጊዜ እጅግ ፈርተው “በእውነት ይህ የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ!” አሉ። 55በሩቅ ሆነው የሚመለከቱት ብዙ ሴቶችም በዚያ ነበሩ፤ እነርሱ ከገሊላ ጀምረው ኢየሱስን እያገለገሉ ይከተሉት የነበሩ ናቸው። 56ከእነርሱም መካከል መግደላዊት ማርያም፥ የያዕቆብና የዮሴፍ እናት ማርያም የዘብዴዎስ ልጆች እናት ይገኙባቸው ነበር። #ሉቃ. 8፥2-3።
የኢየሱስ መቀበር
(ማር. 15፥42-47ሉቃ. 23፥50-56ዮሐ. 19፥38-42)
57በመሸ ጊዜ ዮሴፍ የሚባል አንድ የአርማትያስ ከተማ ሀብታም ሰው ወደዚያ መጣ፤ እርሱም የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነበረ፤ 58ይህ ሰው፥ ወደ ጲላጦስ ሄደና የኢየሱስን አስከሬን ለመነ፤ ጲላጦስም አስከሬኑ እንዲሰጠው አዘዘ። 59ስለዚህ ዮሴፍ አስከሬኑን አውርዶ በንጹሕ በፍታ ከፈነው። 60ከአለት ተወቅሮ በተዘጋጀው በራሱ አዲስ መቃብር ውስጥ ቀበረው፤ ከዚህ በኋላ ትልቅ ድንጋይ አንከባሎ የመቃብሩን በር ዘጋና ሄደ። 61መግደላዊት ማርያምና ሌላይቱ ማርያም፥ እዚያ በመቃብሩ ፊት ለፊት ተቀምጠው ነበር።
62በማግስቱ ቅዳሜ፥ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን በአንድነት ወደ ጲላጦስ ሄዱና እንዲህ አሉት፦ 63“ጌታ ሆይ! ያ አሳሳች ገና በሕይወቱ ሳለ ‘ከሦስት ቀን በኋላ ከሞት እነሣለሁ’ ያለው ትዝ አለን። #ማቴ. 16፥21፤ 17፥23፤ 20፥19፤ ማር. 8፥31፤ 9፥31፤ 10፥33-34፤ ሉቃ. 9፥22፤ 18፥31-33። 64ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ ሄደው እንዳይሰርቁትና ለሕዝቡም ‘እነሆ፥ ከሞት ተነሥቶአል’ እንዳይሉ መቃብሩ እስከ ሦስት ቀን ድረስ እንዲጠበቅ እዘዝ፤ አለበለዚያ የኋለኛው ማሳሳት ከመጀመሪያው ይልቅ የባሰ ይሆናል።” 65ጲላጦስም “እነሆ፥ የሚጠብቁ ወታደሮች አሉአችሁ፤ ሂዱና በምታውቁት ዐይነት አስጠብቁ” አላቸው። 66ስለዚህ ሄደው ድንጋዩን በማኅተም አሸጉና መቃብሩን በወታደሮች አስጠበቁ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ