የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማርቆስ ወንጌል 6

6
ኢየሱስ በናዝሬት ተቃውሞ እንደ ደረሰበት
(ማቴ. 13፥53-58ሉቃ. 4፥16-30)
1ኢየሱስ ከዚያ ወጥቶ ወደ አገሩ መጣ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። 2በሰንበት ቀን በምኲራብ ማስተማር ጀመረ፤ ብዙ ሰዎች በዚያ ተገኝተው ይሰሙት ነበር፤ እነርሱም “ይህ ሰው ይህን ሁሉ ነገር ከየት አገኘው? ምን ዐይነት ጥበብ ተሰጥቶታል? እነዚህንስ ተአምራት የሚያደርገው እንዴት ነው?” እያሉ ይደነቁ ነበር። 3ቀጥለውም “ለመሆኑ ይህ እንጨት ጠራቢው የማርያም ልጅ አይደለምን? የያዕቆብ፥ የዮሳ የይሁዳና የስምዖን ወንድም አይደለምን? እኅቶቹስ እዚህ ከእኛ ጋር አይደሉምን?” እያሉ በመናቅ ሳይቀበሉት ቀሩ።
4ኢየሱስ ግን፥ “ነቢይ በሌሎች ዘንድ ይከበራል፤ በገዛ አገሩ፥ በዘመዶቹና በቤተ ሰቡ መካከል ግን ይናቃል፤” ሲል መለሰላቸው። #ዮሐ. 4፥44።
5በዚያም በጥቂት ሕመምተኞች ላይ እጁን ጭኖ ከመፈወስ በቀር ሌላ ተአምር ማድረግ አልቻለም። 6ሕዝቡ ሳያምኑ በመቅረታቸው እጅግ ተገረመ፤ ከዚህም በኋላ ኢየሱስ በየመንደሩ እየተዘዋወረ ያስተምር ነበር።
ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ለማስተማር እንደ ተላኩ
(ማቴ. 10፥5-15ሉቃ. 9፥1-6)
7ዐሥራ ሁለቱን ወደ እርሱ ጠርቶ ሁለት ሁለት አድርጎ ላካቸው፤ በርኩሳን መናፍስትም ላይ ሥልጣን ሰጣቸው፤ 8ለመንገዳቸው ከበትር በቀር እንጀራም ሆነ ከረጢት፥ ገንዘብም በመቀነታቸው እንዳይዙ አዘዛቸው። #ሉቃ. 10፥4-11። 9እንዲህም አላቸው፤ “በእግራችሁ ጫማ አድርጉ እንጂ ሁለት እጀጠባብ እንኳ አትልበሱ፤ 10በማናቸውም ስፍራ ወደ አንድ ሰው ቤት ስትገቡ፥ ያንን ስፍራ እስክትለቁ ድረስ በዚያው ቈዩ፤ 11ሰዎች በማይቀበሉአችሁና በማይሰሙአችሁ ቦታ ሁሉ የእግራችሁን አቧራ አራግፉና ከዚያ ወጥታችሁ ሂዱ፤ ይህም ለእነርሱ የማስጠንቀቂያ ምስክር ይሆንባቸዋል።” #ሐ.ሥ. 13፥51። #6፥11 የግዕዝ ሐዲስ ኪዳንና በ 1947 ዓ.ም. የታተመው የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ የሚቀጥለውን ይጨምራሉ፦ “እውነት እላችኋለሁ፤ ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ በፍርድ ቀን ይቀልላቸዋል።” ይህ ዐረፍተ ነገር ግን በማናቸውም የግሪኩ ምንባብ ውስጥ አይገኝም።
12የተላኩትም ከዚያ ወጥተው፥ ሰዎች ሁሉ ንስሓ እንዲገቡ አስተማሩ። 13ብዙ አጋንንትንም አስወጡ፤ ብዙ ሰዎችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱ። #ያዕ. 5፥14።
የመጥምቁ ዮሐንስ መገደል
(ማቴ. 14፥1-12ሉቃ. 9፥7-9)
14የኢየሱስ ዝና በሁሉም ዘንድ ስለ ታወቀ፥ ንጉሡ ሄሮድስ ስለ እርሱ ሰማ። አንዳንድ ሰዎች፥ “መጥምቁ ዮሐንስ ከሞት ተነሥቶአል፤ ስለዚህ ይህ ሁሉ ተአምራት በእርሱ ይደረጋል” ይሉ ነበር።
15ሌሎችም “ኤልያስ ነው፤” ይሉ ነበር፤ የቀሩትም ደግሞ “ከቀድሞዎቹ ነቢያት እንደ አንዱ ነው፤” ይሉ ነበር። #ማቴ. 16፥14፤ ማር. 8፥28፤ ሉቃ. 9፥19።
16ሄሮድስ ግን ይህን ሁሉ ሰምቶ፦ “ይህ እኔ አንገቱን ያስቈረጥኩት ዮሐንስ ነው፤ እነሆ! እርሱ ከሞት ተነሥቶአል፤” አለ። 17ሄሮድስ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮዲያዳን ስለአገባ ዮሐንስን በእርስዋ ምክንያት አስይዞ በወህኒ ቤት አስሮት ነበር። 18ዮሐንስም የታሰረው፥ ሄሮድስን “የወንድምህን ሚስት ማግባትህ ተገቢ አይደለም!” ብሎት ስለ ነበር ነው። #ሉቃ. 3፥9-20።
19ሄሮዲያዳ በዚህ ተቀይማ ዮሐንስን ልታስገድለው ትፈልግ ነበር፤ ነገር ግን አልቻለችም። 20ሄሮድስ በመጀመሪያ ዮሐንስ ጻድቅና ቅዱስ መሆኑን ስለሚያውቅ ይፈራውና ይጠብቀውም ነበር። ሄሮድስ የዮሐንስን ንግግር በሰማ ቊጥር ይታወክ ነበር፤ ይሁን እንጂ በደስታ ይሰማው ነበር።
21ሄሮድስ የተወለደበትን ቀን ለማክበር ለመንግሥት ባለሥልጣኖች፥ ለጦር ሹማምንትና ለአንዳንድ የታወቁ የገሊላ ነዋሪዎች ታላቅ ግብዣ አደረገ፤ ይህም ለሄሮዲያዳ ጥሩ አጋጣሚ ሆነላት፤ 22ስለዚህም የሄሮዲያዳ ልጅ ወደ ግብዣው አዳራሽ ገብታ እየጨፈረች ሄሮድስንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ተጋባዦች አስደሰተች፤ ንጉሡም ልጅትዋን፦ “የምትፈልጊውን ማንኛውንም ነገር ጠይቂኝ፤ እሰጥሻለሁ” አላት፤ 23“የመንግሥቴንም እኩሌታ እንኳ ቢሆን፥ የምትጠይቂኝን ሁሉ እሰጥሻለሁ!” ሲል ማለላት።
24እርስዋም ወደ እናትዋ ሄዳ፥ “ምን ልጠይቅ?” አለቻት፤ እናትዋም “ ‘የመጥምቁ ዮሐንስ ራስ ይሰጠኝ፤’ ብለሽ ጠይቂ፤” አለቻት።
25ልጅትዋም ወዲያውኑ በፍጥነት ወደ ንጉሡ ተመልሳ፥ “የመጥምቁ ዮሐንስ ራስ በሳሕን ሆኖ አሁን እንዲሰጠኝ እፈልጋለሁ፤” ስትል ጠየቀች።
26ንጉሡ በዚህ ነገር በጣም አዘነ፤ ይሁን እንጂ በተጋባዦች ፊት ስላደረገው መሐላ የጠየቀችውን ሊከለክላት አልፈለገም። 27ስለዚህ ንጉሡ ወዲያውኑ አንዱን የዘብ ጠባቂ ወታደር የዮሐንስን ራስ ቈርጦ እንዲያመጣ ላከው፤ ወታደሩም ወደ ወህኒው ቤት ሄዶ የዮሐንስን ራስ ቈረጠ፤ 28የተቈረጠውንም ራስ በሳሕን አድርጎ አመጣና ለልጅትዋ ሰጣት፤ ልጅትዋም ለእናትዋ ሰጠች። 29የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ይህን በሰሙ ጊዜ መጡና በድኑን ወስደው ቀበሩት።
ኢየሱስ አምስት ሺህ ሰዎችን መመገቡ
(ማቴ. 14፥13-21ሉቃ. 9፥10-17ዮሐ. 6፥1-14)
30ሐዋርያት ከተላኩበት ተመልሰው መጥተው በኢየሱስ ፊት ተሰበሰቡ፤ ያደረጉትንና ያስተማሩትን ሁሉ ነገሩት። 31እርሱም “እናንተ ብቻችሁን ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራ ሂዱና ጥቂት ዕረፉ፤” አላቸው፤ ይህንንም ያለበት ምክንያት ወደ እነርሱ የሚመጡና የሚሄዱ ብዙዎች ስለ ነበሩ ለመመገብ እንኳ ጊዜ ሊኖራቸው ስላልቻለ ነው። 32ስለዚህ ብቻቸውን ለመሆን በጀልባ ተሳፍረው ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራ፥ ሄዱ።
33ይሁን እንጂ እነርሱ ሲሄዱ ብዙ ሰዎች አይተው ዐወቁአቸው፤ ከየከተማውም ወጥተው በእግር እየሮጡ ቀደሙአቸውና ወደ እነርሱ ተሰበሰቡ። 34ኢየሱስ ከጀልባው ሲወርድ ብዙ ሰዎችን አየ፤ እረኛ እንደሌላቸው በጎች በመሆናቸውም አዘነላቸው፤ ብዙ ነገርም ያስተምራቸው ጀመር። #ዘኍ. 27፥17፤ 1ነገ. 22፥17፤ 2ዜ.መ. 18፥16፤ ሕዝ. 34፥5፤ ማቴ. 9፥36። 35ጊዜው እየመሸ በመሄዱ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው እንዲህ አሉት፦ “ቦታው በረሓ ነው፤ ጊዜውም መሽቶአል፤ 36የሚበሉት የላቸውምና በአካባቢው ወዳሉት ገጠሮችና መንደሮች ሄደው ምግብ እንዲገዙ እነዚህን ሰዎች አሰናብታቸው።”
37ኢየሱስ ግን፦ “የሚበሉትን እናንተ ስጡአቸው” ሲል መለሰ። እነርሱም “ታዲያ፥ ሄደን የሚበሉትን እንጀራ በሁለት መቶ ዲናር ገዝተን እንስጣቸውን?” አሉ። #6፥37 ዲናር፦ የአንድ የቀን ሠራተኛ የአንድ ቀን ደመወዝ ነበር።
38እርሱም “ስንት እንጀራ አላችሁ? እስቲ ሂዱና እዩ፤” አላቸው፤ አይተውም “አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣ አለ፤” አሉት።
39ኢየሱስም ሕዝቡን በቡድን ከፋፍለው፥ በለመለመው መስክ ላይ እንዲያስቀምጡአቸው ደቀ መዛሙርቱን አዘዘ። 40ስለዚህ ሕዝቡ በመቶና በኀምሳ ተከፋፍለው በቡድን ተቀመጡ። 41ኢየሱስም አምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ አንሥቶ፥ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረከ፤ እንጀራውንም ቈርሶ ለሰዎቹ እንዲያድሉ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ እንዲሁም ሁለቱን ዓሣ ለሁሉም አከፋፈለ። 42ሁሉም በልተው ጠገቡ። 43ደቀ መዛሙርቱም የተረፈውን ቊርስራሽ ዐሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ ሰበሰቡ። 44እንጀራውን የበሉ ወንዶች ቊጥር አምስት ሺህ ያኽል ነበር።
ኢየሱስ በባሕር ላይ እየተራመደ እንደ ሄደ
(ማቴ. 14፥22-33ዮሐ. 6፥15-21)
45ኢየሱስ ወዲያውኑ ሕዝቡን ሲያሰናብት ሳለ ደቀ መዛሙርቱ በጀልባ ሆነው ወደ ማዶ ወደ ቤተ ሳይዳ ተሻግረው እንዲቀድሙት አዘዛቸው። 46ከዚህ በኋላ ከእነርሱ ተለይቶ ለመጸለይ ወደ ተራራ ወጣ። 47በመሸም ጊዜ ጀልባዋ በባሕሩ መካከል ነበረች፤ እርሱ ግን ብቻውን በምድር ላይ ነበረ። 48ደቀ መዛሙርቱ ከወደፊታቸው በሚነፍሰው ነፋስ ምክንያት መቅዘፍ ተቸግረው ሲጨነቁ አያቸው፤ ከሌሊቱም ከዘጠኝ እስከ ዐሥራ ሁለት ሰዓት ባለው ጊዜ በባሕሩ ላይ እየተራመደ ወደ እነርሱ መጣ፤ አልፎአቸውም ሊሄድ ነበር። 49ነገር ግን እነርሱ በባሕሩ ላይ እየተራመደ ሲሄድ አይተው መንፈስ መስሎአቸው ጮኹ። 50ሁሉም ባዩት ጊዜ ደነገጡ።
እርሱ ግን ወዲያውኑ፦ “አይዞአችሁ! እኔ ነኝ! አትፍሩ!” አላቸው፤ 51ወደ ጀልባውም ገብቶ፥ ከእነርሱ ጋር በሆነ ጊዜ ነፋሱ ቆመ፤ ደቀ መዛሙርቱ በጣም ተደነቁ። 52ታዲያ፥ ልባቸው ደንዝዞ፥ የእንጀራውን ተአምር ሳያስተውሉ ቀርተው ነው እንጂ ይህ ነገር ባላስገረማቸውም ነበር።
ኢየሱስ በጌንሳሬጥ በሽተኞችን እንደ አዳነ
(ማቴ. 14፥34-36)
53ባሕሩን ተሻግረው፥ ወደ ጌንሳሬጥ ደረሱ፤ ጀልባዋን ወደ ምድር አስጠግተው አሰሩ፤ 54ከጀልባ እንደወረዱ ወዲያውኑ ሰዎች ኢየሱስን ዐወቁት፤ 55እነርሱም በዚያ አገር ዙሪያ እየተራወጡ ኢየሱስ ወዳለበት ስፍራ ሁሉ በሽተኞችን በአልጋ ተሸክመው ያመጡ ጀመር። 56በየሄደበትም ስፍራ ሁሉ በመንደር፥ በከተማ፥ በገጠርም በሽተኞችን ወደ አደባባይ እያወጡ በእርሱ ፊት ያቀርቡአቸው ነበር፤ የልብሱንም ጫፍ እንኳ እንዲነኩ ይለምኑት ነበር፤ የነኩትም ሁሉ ይድኑ ነበር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ