የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማርቆስ ወንጌል 7

7
ስለ አባቶች ወግ
(ማቴ. 15፥1-9)
1ፈሪሳውያንና ከኢየሩሳሌም የመጡ አንዳንድ የሕግ መምህራን ወደ ኢየሱስ መጥተው በዙሪያው ተሰበሰቡ። 2ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አንዳንዶቹ በሥርዓት ባልነጻ ማለት ባልታጠበ እጅ እንጀራ ሲበሉ አዩአቸው።
3ፈሪሳውያንና የቀሩትም አይሁድ የሽማግሌዎችን ወግ በመጠበቅ እጃቸውን በሥርዓቱ ካልታጠቡ አይበሉም ነበር። 4እንዲሁም ከገበያ ሲመለሱ ካልታጠቡ አይበሉም ነበር፤ ዋንጫን፥ ማሰሮን፥ የናስ ዕቃዎችንና አልጋን፥ እንደማጠብ ያለ፥ ሌላም ብዙ ወግ ይጠብቁ ነበር።
5ስለዚህ ፈሪሳውያንና የሕግ መምህራን፥ “ደቀ መዛሙርትህ የሽማግሌዎችን ወግ በመጣስ፥ ስለምን እጃቸውን ሳይታጠቡ እንጀራ ይበላሉ?” ሲሉ ኢየሱስን ጠየቁት።
6እርሱ ግን እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እናንተ ግብዞች! ኢሳይያስ ስለ እናንተ፥
‘ይህ ሕዝብ በአፉ ብቻ ያከብረኛል እንጂ
ልቡ ከእኔ የራቀ ነው!
7ሰው ሠራሽ ሥርዓትን እንደ እግዚአብሔር ሕግ አድርገው እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል!’ ብሎ የተናገረው ትንቢት ትክክል ነው፤ #ኢሳ. 29፥13።
8“ስለዚህ እናንተ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትታችሁ የሰውን ወግ ትጠብቃላችሁ።”
9ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “ወጋችሁን ለመጠበቅ ስትሉ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትተዋላችሁ፤ 10ሙሴ፦ ‘አባትህንና እናትህን አክብር፤ ደግሞም በአባቱ ወይም በእናቱ ላይ ክፉ የሚናገር ሰው በሞት ይቀጣ፤’ ይላል። #ዘፀ. 20፥12፤ 21፥17፤ ዘሌ. 20፥9፤ ዘዳ. 5፥16። 11እናንተ ግን እንዲህ ትላላችሁ፤ ‘አንድ ሰው ለአባቱ ወይም ለእናቱ በመርዳት ፈንታ ለአባቱና ለእናቱ ማድረግ የሚገባውን ነገር ሁሉ ለእግዚአብሔር ያቀረብኩት መባ ነው፤’ ቢላችሁ፥ 12አባትና እናቱን ከመርዳት ነጻ ታደርጉታላችሁ፤ 13በዚህም ሁኔታ የራሳችሁን ወግ ለመጠበቅ ስትሉ የእግዚአብሔርን ቃል ትሽራላችሁ፤ እንዲሁም ይህን የመሳሰለ ብዙ ነገር ታደርጋላችሁ።”
ሰውን የሚያረክስ ነገር
(ማቴ. 15፥10-20)
14ሕዝቡንም እንደገና ወደ እርሱ ጠርቶ፥ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ ሁላችሁም በማስተዋል አዳምጡኝ፤ 15ሰውን የሚያረክሰው፥ ከሰው የሚወጣው ነገር ነው እንጂ ከውጪ ወደ ሰው የሚገባውስ አያረክሰውም! 16[እንግዲህ ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!”] #7፥16 አንዳንድ የብራና ጽሑፎች ቊ. 16 ይጨምራሉ፤ ቃሉም በ 4፥23 ያለውን ይመስላል።
17ኢየሱስ ሕዝቡን ትቶ ወደ ቤት በገባ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ስለ ምሳሌው ጠየቁት። 18እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እናንተም ደግሞ ይህን አታስተውሉምን? ከውጪ ወደ ሰው የሚገባ ነገር ሰውን ምንም እንደማያረክሰው አይገባችሁምን? 19በሆድ በኩል ተላልፎ ወደ ውጪ ይወጣል እንጂ ወደ ልብ አይሄድም፤”። በዚህም ኢየሱስ ምግብ ሁሉ ንጹሕ መሆኑን ገለጸ።
20ቀጥሎም እንዲህ አለ፦ “ሰውን የሚያረክሱት ከሰው ልብ የሚወጡት ነገሮች ናቸው። 21እነርሱም፦ ክፉ ሐሳብ፥ ዝሙት፥ ስርቆት፥ ሰውን መግደል፥ 22አመንዝራነት፥ ስግብግብነት፥ ክፋት፥ አታላይነት፥ ስድነት፥ ምቀኝነት፥ ሐሜተኛነት፥ ትዕቢት፥ ግዴለሽነት ናቸው። 23ይህ ሁሉ ክፉ ነገር ከሰው ልብ ይወጣል፤ ሰውንም ያረክሰዋል።”
የአንዲት ሴት እምነት
(ማቴ. 15፥21-28)
24ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ በጢሮስ ከተማ አጠገብ ወዳለው መንደር ሄደ፤ ወደ አንድ ቤትም ገብቶ እዚያ መኖሩን ማንም ሰው እንዳያውቅ ፈለገ፤ ይሁን እንጂ ሊሰወር አልተቻለውም። 25ልጅዋ በርኩስ መንፈስ የተያዘችባት አንዲት ሴት ስለ ኢየሱስ ሰምታ ወዲያውኑ መጣችና በእግሩ ሥር ወደቀች። 26ሴትዮዋም ከሲሮፊኒቃውያን ወገን የሆነች ግሪካዊት ነበረች፤ እርስዋ ከልጅዋ ጋኔን እንዲያወጣላት ኢየሱስን ለመነችው። 27ኢየሱስ ግን፥ “የልጆችን ምግብ ወስዶ ለውሾች መስጠት አይገባምና እስቲ ልጆቹ አስቀድመው ይጥገቡ፤” አላት።
28እርስዋም “እርግጥ ነው ጌታዬ፤ ግን ውሾችም እኮ በገበታ ሥር ሆነው ልጆች ሲበሉ የሚወድቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ፤” ስትል መለሰችለት።
29ስለዚህ ኢየሱስ፥ “በዚህ አነጋገርሽ ጋኔኑ ከልጅሽ ወጥቶአል፤ እንግዲህ ወደ ቤትሽ ሂጂ!” አላት።
30እርስዋም ወደ ቤትዋ በተመለሰች ጊዜ ልጅዋን ጋኔኑ ለቋት በአልጋ ላይ በደኅና ተኝታ አገኘቻት።
ኢየሱስ ደንቆሮና ድዳ የነበረውን ሰው መፈወሱ
31ኢየሱስ የጢሮስን አካባቢ ትቶ ሄደ፤ በሲዶና በኩልም አድርጎ ዐሥር ከተሞች በሚባለው አገር ወደ ገሊላ ባሕር መጣ። 32በዚያ አንድ ደንቆሮና ድዳ ሰው ወደ እርሱ አመጡ፤ እጁንም እንዲጭንበት ለመኑት። 33ኢየሱስም ሰውየውን ከሕዝቡ ለይቶ ለብቻው ወሰደና ጣቶቹን በሰውየው ጆሮዎች ውስጥ አገባ፤ ምራቁንም እንትፍ ብሎ የሰውዬውን ምላስ ዳሰሰ፤ 34ወደ ሰማይም አሻቅቦ አይቶ ቃተተና ሰውየውን “ኤፍታህ!” አለው፤ ፍቺውም “ተከፈት!” ማለት ነው።
35ወዲያውኑ ጆሮዎቹ ተከፈቱ፤ አንደበቱም ተፈታ፤ ያለአንዳች ችግርም አጥርቶ መናገር ጀመረ። 36ኢየሱስ ይህን ነገር ለማንም እንዳይናገሩ ሰዎቹን አዘዛቸው፤ ይሁን እንጂ፥ እንዳይናገሩ ባዘዛቸው መጠን በብዙ አብልጠው ያወሩ ነበር። 37የሰሙትም ሁሉ እጅግ በጣም በመደነቅ፦ “ሁሉን ነገር በመልካም አደረገ! ደንቆሮዎች እንዲሰሙ፥ ድዳዎች እንዲናገሩ ያደርጋል!” አሉ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ