የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘኊልቊ 14

14
የሕዝቡ ማጒረምረም
1ሕዝቡም ሌሊቱን ሁሉ በመጨነቅ ሲጮኹ አደሩ፤ 2በሙሴና በአሮንም ላይ እንዲህ እያሉ አጒረመረሙ፥ “በግብጽ ሳለን ወይም በዚህ ምድረ በዳ ሞተን በቀረን መልካም በሆነ ነበር! 3እግዚአብሔር ወደዚያች ምድር የሚወስደን ለምንድን ነው? እኛ ሁላችን በጦርነት እናልቃለን፤ ሚስቶቻችንና ልጆቻችንም ይማረካሉ፤ ወደ ግብጽ ብንመለስ መልካም አይሆንምን?” 4ስለዚህም እርስ በርሳቸው “ኑ! መሪ የሚሆነን ሰው መርጠን ወደ ግብጽ እንመለስ!” ተባባሉ።
5በዚያን ጊዜ ሙሴና አሮን በሕዝቡ ሁሉ ፊት ወደ መሬት ተደፉ፤ 6ምድሪቱን እንዲያጠኑ ከተላኩት ሰዎች ሁለቱ የነዌ ልጅ ኢያሱና የየፉኔ ልጅ ካሌብ በሐዘን ልብሳቸውን ቀደዱ፤ 7ለሕዝቡም እንዲህ አሉ፦ “መርምረን ያጠናናት ምድር እጅግ ውብ የሆነች ምድር ናት፤ 8እግዚአብሔር በእኛ ደስ የሚለው ቢሆን ወደዚያ ይወስደናል፤ በማርና በወተት የበለጸገችውን ያቺን ለም ምድር ይሰጠናል፤ 9ስለዚህ በእግዚአብሔር ላይ አታምፁ፤ እዚያም የሚኖሩትን ሕዝቦች አትፍሩአቸው፤ እኛ በቀላሉ በጦርነት ድል እንነሣቸዋለን፤ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው፤ ጥላቸው ከላያቸው ተገፎአል፤ ስለዚህ ፈጽሞ አትፍሩአቸው።” #ዕብ. 3፥16። 10መላውም ማኅበር በድንጋይ ወግሮ ሊገድላቸው በእነርሱ ላይ ተነሣሣ፤ ነገር ግን በመገናኛው ድንኳን የእግዚአብሔር ክብር ለእስራኤላውያን ሁሉ ተገለጠ።
ሙሴ ስለ ሕዝቡ መጸለዩ
11እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ይህ ሕዝብ እኔን የሚንቀው እስከ መቼ ነው? ብዙ ተአምራትን በፊቱ አድርጌአለሁ፤ ታዲያ፥ በእኔ መታመንን እምቢ የሚለው እስከ መቼ ነው? 12እነሆ፥ እኔ ቸነፈር አምጥቼ በመቅሠፍት እደመስሳቸዋለሁ፤ አንተን ግን ከእነርሱ ይበልጥ ታላቅና ብርቱ ለሆነ ሕዝብ አባት አደርግሃለሁ።”
13ሙሴ ግን እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፤ “ይህን ሕዝብ በኀይልህ ከግብጽ አወጣህ፤ በሕዝብህ ላይ ያደረግኸውን ግብጻውያን በሚሰሙበት ጊዜ፥ #ዘፀ. 32፥11-14። 14የሆነውን ሁሉ በዚህ ምድር ለሚኖሩት ሕዝቦች ይነግራሉ፤ እነዚህ ሕዝቦች አንተ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር መሆንህንና ደመናህ በላያችን በረበበ ጊዜ በግልጥ እንደምትታይ፥ ቀን በደመና ዐምድ፥ ሌሊት በእሳት ዐምድ እፊት እፊታችን እየሄድክ እንደምትመራን ከሰሙ ቈይተዋል። 15ታዲያ አሁን ሕዝብህን በሙሉ ብትገድል ዝናህን የሰሙ አሕዛብ ሁሉ፥ 16‘ሊሰጣቸው ቃል ወደገባላቸው ምድር ሊያደርሳቸው ስላልቻለ አጠፋቸው’ ይሉሃል። 17ስለዚህ ጌታ ሆይ፥ ኀይልህን እንድታሳየን እለምንሃለሁ፤ ደግሞም እንዲህ ስትል የተናገርከውን የተስፋ ቃል ፈጽምልን፤ 18‘እግዚአብሔር በቶሎ አይቈጣም፤ ምሕረቱና ፍቅሩ የበዛ ነው፤ ኃጢአትንና ዐመፃን ይቅር ይላል፤ ነገር ግን እስከ ሦስት ከዚያም እስከ አራት ትውልድ ድረስ ልጆችንና የልጅ ልጆችን ስለ ወላጆቻቸው ኃጢአት እቀጣለሁ’ እንዳልከው፥ #ዘፀ. 20፥5-6፤ 34፥6-7፤ ዘዳ. 5፥9-10፤ 7፥9-10። 19አሁንም ጌታ ሆይ፤ ታላቅ በሆነውና በማይለወጠው ፍቅርህ ከግብጽ ከወጡበት ጊዜ አንሥቶ ምሕረት እንዳደረግህላቸው የዚህን ሕዝብ ኃጢአት ይቅር እንድትል እለምንሃለሁ።”
20እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “በጠየቅኸው መሠረት ይቅር እላቸዋለሁ፤ 21ነገር ግን ሕያው እንደ መሆኔና ክብሬም ምድርን የሞላ እንደ መሆኑ፥ 22ከእነዚህ ሕዝብ አንዱም ወደዚያች ምድር ለመግባት በሕይወት አይኖርም፤ በግብጽ ምድርና በምድረ በዳ ያደረግኋቸውን ተአምራት ሁሉ አይተዋል፤ ነገር ግን የትዕግሥቴን ብዛት ደጋግመው በመፈታተን ለእኔ መታዘዝ እምቢ አሉ። 23ስለዚህ ለቀድሞ አባቶቻቸው ልሰጣቸው ቃል ወደገባሁላቸው ምድር በፍጹም አይገቡም፤ እኔን ከናቁኝ ሰዎች መካከል አንድ እንኳ ወደዚያች ምድር ከቶ አይገባም። #ዕብ. 3፥18። 24ነገር ግን አገልጋዬ ካሌብ ልዩ አመለካከት ስላለውና ለእኔ ያለውንም ታማኝነት ስላጸና ሄዶ የመረመራትን ምድር እሰጠዋለሁ፤ ዘሮቹም ያቺን ምድር ይወርሳሉ፤ #ኢያሱ 14፥9-12። 25አማሌቃውያንና ከነዓናውያን በሸለቆዎቹ ውስጥ ስለሚኖሩ ነገ ተመልሳችሁ በቀይ ባሕር በኩል በሚወስደው መንገድ ወደ ምድረ በዳ ሂዱ።”
እግዚአብሔር አጒረምራሚዎችን መቅጣቱ
26እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦ 27“እነዚህ ክፉዎች የሆኑ ሰዎች በእኔ ላይ የሚያጒረመርሙት እስከ መቼ ነው? እነዚህ አጒረምራሚዎች እስራኤላውያን በእኔ ላይ ማጒረምረማቸውን ሰምቻለሁ። 28እነሆ! ይህን መልስ ስጣቸው፥ ‘በጠየቃችሁት ዐይነት እንደማደርግባችሁ ሕያው በሆነ ስሜ እምላለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ፤ 29ሁላችሁም ትሞታላችሁ፤ ሬሳችሁም በዚህ ምድረ በዳ ተበትኖ ይቀራል፤ በእኔ ላይ በማጒረምረማችሁ ምክንያት ከእናንተ መካከል ከኻያ ዓመት በላይ ዕድሜ ኖሮአችሁ የተቈጠራችሁት ሁሉ ከቶ ወደዚያች ምድር አትገቡም፤ #ዕብ. 3፥17። 30ወደዚያች ምድር ገብታችሁ እንደምትኖሩ ቃል ገብቼላችሁ ነበር፤ ነገር ግን ከየፉኔ ልጅ ከካሌብና ከነዌ ልጅ ከኢያሱ በቀር ከእናንተ አንዱ እንኳ ወደዚያች ምድር አይገባም። 31ልጆቻችን ምርኮኞች ሆነው ይቀራሉ ብላችሁ የተናገራችሁባቸውን እነርሱን እናንተ ወደናቃችኋት ምድር አገባቸዋለሁ፤ ርስታቸውም ትሆናለች። 32የእናንተ በድን ግን በዚህ ምድረ በዳ ይወድቃል፤ 33ልጆቻችሁም በእናንተ አለማመን ምክንያት ከእናንተ የመጨረሻው በድን በምድረ በዳ እስኪወድቅ ድረስ አርባ ዓመት ሙሉ ጽኑ መከራ እየተቀበሉ በዚህ ምድረ በዳ ይንከራተታሉ፤ #ሐ.ሥ. 7፥36። 34በኃጢአታችሁ ምክንያት አርባ ዓመት ሙሉ ትሠቃያላችሁ፤ ይህም ምድሪቱን ለማጥናት በቈያችሁበት አርባ ቀን ልክ አንዲቱ ዕለት አንድ ዓመት ትሆንባችኋለች፤ በዚያን ጊዜ እኔን መቃወም ምን እንደሚያመጣባችሁ ትገነዘባላችሁ። 35በእኔ ላይ አድመው በተነሡብኝ በእነዚህ ዐመፀኞች ላይ ይህን ሁሉ አደርግባቸዋለሁ፤ በዚህ ምድረ በዳ የሁሉም መጨረሻ ይሆናል፤ ሁሉም ይሞታሉ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።’ ”
36እነዚያ ምድሪቱን እንዲሰልሉ ሙሴ ልኮአቸው ከነበሩት ሰዎች፥ ሄደው ከተመለሱ በኋላ ስለምድሪቱ ክፉ ወሬ በማውራት ሕዝቡን እንዲያጒረመርም ያደረጉት 37እነርሱ በእግዚአብሔር ፊት ተቀሥፈው ሞቱ። 38ምድሪቱን ካጠኑት ሰዎች መካከል የተረፉት፥ የነዌ ልጅ ኢያሱና የይፉኔ ልጅ ካሌብ ብቻ ነበሩ።
ምድሪቱን ለመውረር የተደረገ የመጀመሪያ ሙከራ
(ዘዳ. 1፥41-46)
39ሙሴ እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ ለእስራኤላውያን በነገራቸው ጊዜ ምርር ብለው አለቀሱ፤ 40በማግስቱ ጠዋት ማልደው ተራራማይቱን አገር ለመውረር ተነሡ፤ እንዲህም አሉ፦ “እነሆ፥ እግዚአብሔር ሊያስገባን ወደነገረን ስፍራ ለመሄድ ተዘጋጅተናል፤ ኃጢአት መሥራታችንን ተገንዝበናል።”
41ሙሴ ግን እንዲህ አለ፤ “ታዲያ አሁንም ደግማችሁ ለእግዚአብሔር የማትታዘዙት ስለምንድን ነው? ያሰባችሁት አይሳካላችሁም! 42ስለዚህ ወደዚያ አትሂዱ፤ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ስላልሆነ ጠላቶቻችሁ ድል ይነሡአችኋል፤ 43ዐማሌቃውያንንና ከነዓናውያንን ፊት ለፊት ባያችሁ ጊዜ በጦርነት ትሞታላችሁ፤ እርሱን መከተል እምቢ ስላላችሁ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር አይሆንም።”
44እነርሱ ግን ሌላው ቀርቶ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦትም ሆነ ሙሴ ከሰፈር ሳይነሡ ወደ ተራራማይቱ አገር ለመዝመት ደፍረው ተነሡ። 45ከዚያም በኋላ በዚያ የሚኖሩት ዐማሌቃውያንና ከነዓናውያን በእነርሱ ላይ አደጋ ጥለው ድል አደረጉአቸው፤ እስከ ሖርማም ድረስ አሳደዱአቸው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ